የቪዛ ማሻሻያ ለውጥ
የአውስትራሊያ ፌዴራል መንግሥት ገበሬዎች የምርት ተግባራት አጋዥ ሠራተኞች እንዲያገኙ ጊዜያዊ የቪዛ ማሻሻያ ለውጥ አድርጓል።
በማሻሻያ ለውጡም መሠረት፤ የ 'Holiday Worker Program', የ 'Pacific Islander Program' እና የ 'Seasonal Worker Program' ቪዛ ተጠቃሚዎች እስከ 12 ወራት በግብርናና የምግብ ማምረቻ መስኮች ተሠማርተው ለመሥራት ቪዛዎቻቸውን ማራዘም ይችላሉ።
የሽርሽርና ሥራ ቪዛ ተጠቃሚዎች ሆነው በግብርናና የምግብ ማምረቻ መስኮች ያልተሠማሩ ግለሰቦች ቀደም ሲል ለአንድ አሠሪ ለስድስት ወራት እንዲሠሩ ግድ ይላቸው የነበረው ገደብ ተነስቶላቸዋል።
የግብርና ሚኒስትር ዴቪድ ሊትልፕራውድ - የቪዛ ለውጥ ማሻሻያ ማድረጉ ለአውስትራሊያ የምግብ ዋስትና ጠቃሚ መሆኑን ገልጠዋል።
በሌላ በኩል የሌበር ጤና ቃል አቀባይ ክሪስ ባወን - የግብርናና የምግብ ማምረቻ መስክ ሥራዎቹ ለጊዜያዊ ቪዛ ተጠቃሚዎች ከመሰጠታቸው በፊት በቅድሚያ ሥራቸውን ያጡ አውስትራሊያውያን መሥራት ይሹ እንደሁ ሊጠየቁ ይገባል ብለዋል። አያይዘውም፤ ሌበር ቀደም ሲል የሽርሽርና የሥራ ቪዛ ተጠቃሚ ነርሶች እንዲካተቱ ያቀረበው ሃሳብ ተቀባይነት አግኝቶ ሥራ ላይ መዋሉ ያስደሰተው መሆኑንም ገልጠዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም፤ ተጠባባቂ የኢሚግሬሽን ሚኒስትር አለን ታጅ - ጊዜያዊ ቪዛ ተጠቃሚዎች አውስትራሊያ ውስጥ ራሳቸውን ማገዝ ከተሳናቸው ወደ መጡባቸው አገራት እንዲሄዱ አሳስበዋል።
ሆኖም፤ የመጤ ሠራተኞች ማዕከል በበኩሉ - የሞሪሰን መንግሥት 1.1 ሚሊየን የጊዜያዊ ቪዛ ሠራተኞችን ከደመወዝና የሥራ አጥነት ድጎማዎች አግሏል፤ አገራት ድንበሮቻቸውን መዝጋታቸው እየታወቀና አብዛኛዎቹም የቲኬት መግዣ ገንዘብ የሌላቸው ሆነው ሳለ ወደ መጣችሁበት ተመለሱ ብሎ ማለቱ ዕውነታን አሌ ማለት ነው ሲል ምላሽ ሰጥቷል።
ቪክቶሪያ
የአውስትራሊያ በኮሮናቫይረስ ሳቢያ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 30 በደረሰበት ወቅት የተወሰኑ ከባሕር ማዶ ተመላሽ መንገደኞች ራሳቸውን በለይቶ መቆያ አለማቆየታቸው የቪክቶሪያ መንግሥት ላይ ቅሬታ አሳድሯል።
የቪክቶሪያ ጤና ሚኒስትር ጄኒ ሚካኮስ - ፖሊስ የ391 የባሕር ማዶ ተመላሽ መንገደኞች መኖሪያ ቤቶች ላይ ቁጥጥር አካሂዶ 99ኙ ቤታቸው ውስጥ አለመገኘታቸውን ጠቅሰዋል። ወ/ሮ ሚካኮስ - ይህ የተመላሽ መንገደኞቹ ተግባር በብርቱ ቅር ያሰኛቸው መሆኑንና ቪክቶሪያውያንንም ለአደጋ ያጋለጠ ነው ሲሉ በምሬት ተናግረዋል።
ሱፐርማርኬት
ግዙፎቹ ሱፐርማርኬቶች ኮልስና ዉልዎርዝስ የኮሮናቫይረስ መዛመትን ተከትሎ የማኅበራዊ ርቀት (አካላዊ መራራቅ) ድንጋጌዎችን ግብር ላይ ለማዋል የሸማቾችን ግብይት ቁጥር ለመገደብ ወስነዋል።
ሱፐርማርኬቶቹ ሸማቾች የፋሲካ በዓል ከመቃረቡ በፊት ቀደም ብለው የግብይት ዕቅድ በማውጣት እንዲሸምቱ አሳስበዋል።