ላይ እንደቀረበው ሪፖርት እስከ ሰኔ 19, 2012 ዓ.ም ድረስ ብቻ በመላው አገሪቱ 5,570 ሰዎች በቫይረሱ ሲጠቁ የ 94 ሰዎች ህይወትም ተቀስፏል፡፡ በሃገሪቱ ውስን የቫይረስ መመርመሪያ ጣቢያዎችና መቆጣጠሪያ የጤና አውታሮች በመኖራቸው ትክክለኛ ቁጥሩን ለማወቅ ቢያዳግትም መጠኑ ግን ከሪፖርቶቹ ይልቅ እጅግ እንደሚበልጥ መገመት ይቻላል፡፡
ምስል 1፡ የኢትዮጵያ የተቀናጀ የኮቪድ 19 መቆጣጠሪያ ስርዓት ናሙና ()

ለ 33 ቀናት የዘለቀውን የአዲስ አበባ ከተማ ጤና ቢሮ ዕለታዊ የኮቪድ19 በሽታ ሪፖርቶችን ስንዳስስ ኮቪድ19 ከፍተኛ የስጋት ምንጭ እየሆነ መምጣቱንና አዲስ አበባ ደግሞ በከፍተኛ ደረጃ እየተጠቃች መሆኑን በቀላሉ መገንዘብ ይቻላል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ ጤና ቢሮ በሰንጠረዥ ላይ የተመረኮዘ ዕለታዊ መረጃን (ምስል 2) ከግንቦት 17 ጀምሮ ለህዝብ ይፋ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡
ምስል 2፡ በፌስ ቡክ የሚለቀቅ ዕለታዊ የኮሮና ቫይረስ መግለጫ ናሙና (ምንጭ)

ተለምዷዊው ሰንጠረዥ እንደ ኮቪድ19 ያሉ ክስተቶች የሚያሳዩትን በጊዜና በሥፍራ የሚለዋወጥ ባህሪያት ለመግለጽ ያዳግተዋል፡፡ ካርታዊ ትረካ (Story Map) ደግሞ ከስፍራ ስፍራ ያለውን ልዩነትና ተመሳሳይነት ለመለየት ያስችላል፤ የመረጃ ተቀባዩን የመረዳት ክህሎት ያዳብራል፤ ለእቅድና ተግባራዊ እንቅስቃሴ ግብአት ይሆናል፡፡ የሰው ልጅ በተፈጥሮው በጽሁፍ ከሰፈሩ መረጃዎች ይልቅ በምስል የሚቀርቡ መረጃዎችን በፍጥነት የመረዳት ችሎታ ስላለው ካርታዊ ትረካን ለኮቪድ19 ወረርሺኝ መጠቀሙ የበለጠ አዋጭ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ከ75% በመቶ በላይ ቫይረሱ ተጠቂዎች የሚገኙት በአዲስ አበባ ከተማ እንደመሆኑና የአዲስ አበባ ከተማ ጤና ቢሮ መረጃውን በክፍለ ከተማ ደረጃ ሸንሸኖ በማቅረቡ ለዚህ ካርታዊ ትረካ ጥናት መነሳሳት ፈጥሯል፡፡ ዘገባው የሚሸፍነውም ከግንቦት 17 እስከ ሰኔ 19 ድረስ ይፋ የተደረገውን ዕለታዊ መረጃን በመመርኮዝ ብቻ ነው፡፡
የኮቪድ19 ሥርጭት በአዲስ አበባ
የዚህ ጥናት ዓብይ ዓላማ በአዲስ አበባ ከተማ ጤና ቢሮ አማካይነት ይፋ የሚደረጉ ሰንጠረዥ ተኮር የኮቪድ19 ስርጭት ሪፖርቶችን እንዲያዳብርና በመንግስት፣ በተመራማሪዎች፣ በሚዲያ፣ ብሎም በመላው ህዝብ መሃል ያለውን የወረርሺኙን መረጃ ቅብብሎሽ የበለጠ ለማቀልጠፍ ነው፡፡ ለምሳሌ ጤና ቢሮው በየዕለቱ የሚቀርቡትን ስንጠረዦች በመደርደር የበሽታውን የስርጭት ሂደት ለመረዳት አዳጋች ነው [1]፡፡ ባንጻሩ ደግሞ በየሶስት ቀን ልዩነት እንኳ አዲስ ቫይረሱ የተገኘባቸውን ቁጥር በካርታዎች ላይ ብናሰፍር ምስል 3 ላይ በጊዜና በስፍራ የሚታየውን አሳሳቢ የቁጥር ግሽበትን ለመታዘብ እንችላለን፡፡ በተለመዶ "ከአስር ሺህ ቃላት ይልቅ አንድ ምስል" አይደል የሚባለው?
ምስል 3፡ በየአምስት ቀናት ልዩነት የታየውን የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች ቁጥር እድገት የሚያሳይ ካርታ፡፡

ለ33 ቀናት የዘለቀውን ዕለታዊ የኮሮና ቫይረስ መረጃ አጠቃላይ ቁጥርን በመደመር ቁጥር 4 ላይ የምንመለከተውን ጥቅል ምስል (ቁጥር 4) እናገኛለን፡፡ ካርታው በክፍለ ከተሞች መሃል ጉልህ የቫይረስ ስርጭት ልዩነት መኖሩን የሚያመላክት ብቻ ሳይሆን የአዲስ ከተማ ክ/ከተማ በተለየ መጠን በቫይረሱ መጠቃቱን ያሳያል፡፡ ይህ ካርታ ከሰንጠረዥ ይልቅ የተሻለ የመረጃ ማሳያ መንገድ ቢሆንም የራሱ ግድፈት አለው፡፡ በተለያዩ ክ/ከተሞች የሚኖረው ህዝብ ቁጥር እኩል ስላልሆነ በዚህ ካርታ ላይ ተመርኩዘን የክ/ከተሞችን የቫይረስ ስርጭት ለማወዳደር ያዳግተናል፡፡ ትርጉም ያለው ውድድር ማካሄድ የሚቻለው በአቻ ዘርፍ መሃል ሲሆን አይደል?
ምስል 4፡ በበሽተኛ ቁጥር ላይ ብቻ ተመርኩዞ የተዘጋጀ የኮቪድ19 ስርጭት ካርታ፡፡

ምስል 5 በየክፍለ ከተሞች የሚኖረውን አጠቃላይ ህዝብ ታሳቢ በማድረግ (Normalized COVID-19 Cases) የተዘጋጀ በመሆኑ ቫይረሱ በምን ያህል ደረጃ በህዝቡ ውስጥ ዘልቆ እንደገባ ይጠቁማል፡፡ ስለሆነም በክፍለ ከተሞች መሃል የሚገኘውን የቫይረስ ስርጭት ልዩነትን በቀላሉ ማወዳደር ይቻላል፡፡
የህዝብ ቁጥርን ታሳቢ የሚያደርገው ካርታ ሌላው ጥቅሙ ቀድሞ በምስል 4 ላይ ተመልክተነው የነበረውን የተዛባ ግንዛቤ እንድናሻሽል ማስቻሉ ነው፡፡ ለምሳሌ የቦሌ ክ/ከተማ ከልደታ ክ/ከተማ የላቀ የቫይረሱ ስርጭት እንዳለው ተመላክቶ ነበር፡፡ ሆኖም ግን በምስል 5 ላይ የየክ/ከተሞቹ ኗሪ ህዝብ ከስሌት በመግባቱ ሳቢያ የልደታ ክ/ከተማ ከቦሌ ክ/ከተማ ይልቅ በቫይረሱ የበለጠ እንደተጠቃ ነው፡፡
ምስል 5፡ ህዝብ ቁጥርን ታሳቢ የሚያደርግ የኮቪድ19 ስርጭት ካርታ፡፡

ምስል 6 በከተማይቱ የሚገኙ የህክምና ተቋማት ስርጭት በኮቪድ ቫይረስ ተጠቂዎች ስርጭት ላይ አነባብሮ ስለሚያሳይ በሁለቱ ስርጭቶች መሃል ያለውን ግንኙነት ለመመርመርና አዲስ መረጃ ለማግኘት ያስችላል፡፡ በንጽጽር ሲታይ ጉለሌ ከአዲስ ከተማ ለጥቆ የከፍትኛ የቫይረሱ ተጠቂ ክ/ከተሞች አንዱ ሆኖ ሳለ አንዳችም ሆስፒታል የሌለው መሆኑ የወረርሺኙ ጣጣ እንደሚበረታበት መገመት ይቻላል፡፡ በሌላ በኩል ቂርቆስ የቫይረሱ ስርጭት በንጽጽር አነስተኛ ሆኖ ሳለ በሆስፒታሎች አቅርቦት በኩል (ከሌሎች ክ/ከተሞች አንጻር) የተሻለ መስሎ ታይቷል [2]፡፡
ምስል 6፡ ህዝብ ቁጥርን ታሳቢ ባደረገ የኮቪድ19 ስርጭት ላይ የህክምና አቅርቦቶችን አነባብሮ የሚያሳይ ካርታ

ምስል 7 በከተማይቱ ያለውን የኮቪድ ቫይረስ ተጠቂዎች ስርጭት ከክ/ከተማዎቹ ኗሪ ህዝብ የእድሜ ስብጥር ጋር ያለውን ትስስር ለመገንዘብ ያስችላል፡፡ ንፋስ ስልክ ላፍቶ፣ ኮልፌ ቀራንዮ፣ እና የካ ዝቅ ያለ የቫይረሱ ስርጭት ቢኖራቸውም የአዛውንቶቹ ቁጥር ከአዋቂና ከልጆች ቁጥር ጋር ሲተያይ እጅግ በጣም ዝቅተኛ በመሆኑ ከሌሎች ክ/ከተሞች ይልቅ የስጋቱን መጠን ይቀንስላቸዋል [3]፡፡ በተቀሩት ክ/ከተሞች ደግሞ በርከት ባለ የአዛውንቶች ቁጥር ሳቢያ የወረርሺኙ ጫና ሊበረታባቸው እንደሚችል እሙን ነው፡፡
ምስል 7፡ ህዝብ ቁጥርን ታሳቢ ባደረገ የኮቪድ19 ስርጭት ላይ የእድሜ ስብጥርን አነባብሮ የሚያሳይ ካርታ

ላለፉት 33 ቀናት በየክ/ከተሞቹ የተመዘገበውን የቫይረሱ ስርጭትን በመንተራስ በቀጣዩ 5 ቀናት የሚኖረውን የቁጥር እድገት አቅጣጫ ብንተነብይ ምስል 8 ላይ ያለውን ሁነት እናገኛለን፡፡ የአዲስ ከተማ ከተቀሩት ክ/ከተሞች ያለው ልዩነት እየሰፋ በቀጣዩ ቀናት በእጅጉ የሚንር የቫይረሱ ተጠቂዎች ቁጥር እንደሚኖረው መገመት ይቻላል፡፡ የአዲስ ከተማ ክ/ከተማን ባህሪን ለይተን ብንመረምር ለኮሮና ቫይረስ መስፋፋት አመቺ ስፍራ ስለመሆኑ ማወቅ እንችላለን፡፡ ምክንያቱም ቦታው የኮሮና ቫይረስን ሊያባብሱ የሚችሉ የሚከተሉትን ሁነቶች አጣምሮ ስለያዘ ነው፤ ሥር የሰደደ ድህነት፣ የመኖሪያ ቤቶችና የንግድ እንቅስቃሴ ከፍተኛ ጥግግት፣ የሰዎች ከፍተኛ መጨናነቅ ሳቢያ ማህበራዊ ፈቀቅታን መተግበር የሚያዳግትበት ስፍራ መሆን፣ እና በአራቱም አቅጣጫ የሚኖረው ኢትዮጵያዊ የሚተላለፍበት መስቀለኛ ስፍራ መሆን፣ ወዘተ፡፡
ምስል 8፡ በጊዜ ሂደት የታየው የኮሮና ቫይረስ ስርጭትና የቀጣይ 5 ቀናት ትንበያ

አዲስ ከተማ ክ/ከተማን ትተን እንኳ የተቀሩት ክ/ከተሞች በምስል 8 ላይ ያሳዩትን የጊዜ ለውጥ ሂደት ላይ ብናተኩር አዲስ መረጃ ይከሰትልናል፡፡ በምስል 9 መገንዘብ የሚቻለው በክ/ከተሞች መሃል ያለውን የቁጥር ልዩነት ብቻ ሳይሆን የስርጭት ፍጥነትን ጭምር ነው:፡ እስከ ግንቦት 30 ድረስ የቦሌ ክ/ከተማ ከጉለሌ፣ የካ፣ እና ልደታ ክ/ከተሞች ያነሰ ቁጥር የነበረው ቢሆንም ከስኔ መባቻ ጅምሮ ግን ማርሽ ቀይሮ የስርጭቱ እድገት (በንጽጽር) በከፍተኛ ደረጃ መናሩን ያሳያል፡፡ ይህን መሰል ድንገቴ ለውጥ ጉዳዩን ቀርቦ መመርመር ለሚሻ አጥኚ ከፍተኛ መነሳሳትን ይፈጥራል፡፡ በተያያዥነት ጉለሌ እንደ ቦሌ ክ/ከተማ ደንገቴ ለውጥ ባያሳይም ከተቀሩት ክ/ከተሞች አንጻር የስርጭቱ ፍጥነት እየጨመረ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል፡፡
ምስል 9፡ የቦሌ ክ/ከተማ ያሳየው የተለየ የኮቪድ19 ስርጭት የፍጥነት ሂደት

ማጠቃለያ
የአዲስ አበባ መስተዳድር የተሻለ ውጤትን ማግኘት የሚሻ ከሆነ የሚከተሉትን ምክሮች ቢተገብር መልካም ነው፡
- ቢሮው የጀመረው አርአያነት ያለው ተግባር የሚበረታታ ሲሆን ጥረቱን አጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል፡፡ ሌሎች ከተሞችና ክልሎችንም ስለሚያነቃቃ በሃገሪቱ የዳበረ የመረጃ ቋት እንዲፈጠርና ተጠቃሚዎችም በቀላሉ እንዲያገኙት ያስችላል፡፡ የዕለታዊ ሪፖርቶች ሳይቋረጥ ከቀጠለ የስርጭቱን ሁለንተናዊ ገጽታ መረዳታችንም የዳበረ ይሆናል፡፡
- ዕለታዊ ሪፖርቶቹ የክ/ከተማ ብቻ ሳይሆን የወረዳ አድራሻዎችንም ቢያክሉ እጅግ ትኩረት የሚሹ ቦታዎችን (hot spots) ሆነ ፋታ የሚሰጡ ቦታዎችን (cold spots) በበለጠ ሁኔታ ለመለየት ያስችላል፡፡ ይህን መስል መረጃ ደግሞ የቫይረሱን ስርጭት ለመቆጣጠር የሚደረገውን ጥረት በእጅጉ ያግዛል፡፡ የከተማው አስተዳደርና ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ያሏቸውን ውስን የሆነ የገንዘብ፣ የሰው ሃይል፣ እና የማቴሪያል አቅርቦቶቻቸውን ለማቀዳደምና ለማቀላጠፍ መንገድ ይከፍትላቸዋል፡፡
የግርጌማስታወሻዎች፡
- የዚህ ሪፖርት መነሻ ሃሳብ "ኮቪድ19 - ማኅበራዊ ፈቀቅታና አዲስ አበባ" በሚል ርዕስ በአዘጋጁ በቅርቡ ለንባብ ያበቃው መጣፍን ወይንም ድረ ገጾች ላይ ማግኘት ይቻላል፡፡
- ይህ ካርታዊ ትረካ የአካዳሚያዊ ጥናት መስፈርትን አሟልቶ፣ በአቻ ባለሙያዎች ተፈትሾና ጸድቆ ለአካዳሚያዊ ታዳሚ የቀረበ ሳይሆን ቀለል ባለ መልኩ ተዘጋጅቶ በርካታ አንባቢ አንብቦት እንዲረዳ የተዘጋጀ ነው፡፡
- አስተያየት ለመስጠት [email protected] መጠቀም ይቻላል፡፡
[1] 15 ቀናትን ብቻ ያካተተው የመጀመሪያ ካርታዊ ታሪክ ይፋ ከሆነ በኋላ የአዲስ አበባ መስተዳድር ጤና ቢሮ ለመጀመሪያ ጊዜ የከተማውን የቫይረስ ስርጭት በወረዳ ደረጃ አዘጋጅቶ በፌስ ቡኩ ላይ በሰኔ 10 ለሕዝብ ይፋ አድርጓል፡፡ ጥረቱ የሚደነቅ ሆኖ በካርታው ላይ ካርቶግራፊያዊ ማሻሻያዎች ቢታከልበት ተነባቢነቱ የበለጠ ውጤት ይኖረዋል፡፡
[2] ልብ ሊባል የሚገባው ንጽጽሩ በክ/ከተምች መሃል የሚገኘውን የሆስፒታሎች ቁጥርን ብቻ እንጂ በመላው ሃገሪቱ እጅግ አነስተኛ የህክምና አቅርቦት እንዳለ እሙን ነው፡፡ በቅርቡ ይፋ የሆነ ሪፖርት የሚያሳየው በኢትዮጵያ በየ 10,000 ናሪ ሶስት የሆስፒታል አልጋዎች ብቻ እንዳለና ይህ ቁጥር ደግሞ ከገረቤት ሃገራት አንጻር እንኳ በዝቅተኛ ደረጃ የሚገኝ መሆኑን ነው፡፡
[3] አዛውንቶች በኮቪድ19 በሚያዙበት ወቅት ከሌሎች ነባር ህመሞቻቸው ጋር ሲለሚወሳሰብ የመዳን ዕድላቸው ባመዛኙ የተመናመነ ነው፡፡
የግርጌ ማስታወሻዎች፡
- አቅም በፈቀደ ይህ ካርታዊ ትርክት (የእንግሊዝኛው ቅጂ እየተዘጋጀ ነው) በየጊዜው ስለሚከለስ በጊዜ ሂደት የሚከሰተውን የቫይረሱ ስርጭትን የለውጥ አቅጣጫ መከታተል ያስችላል፡፡
- በተያያዥነት፣ አዘጋጁ "ኮቪድ19 - ማኅበራዊ ፈቀቅታና አዲስ አበባ" በሚል ርዕስ በቅርቡ ለንባብ ያበቃው መጣጥፉ (ወይንም ድረ ገጾች ላይ ማግኘት ይቻላል) ለዚህ ካርታዊ ትርክት እንደመነሻ ሆኖ ሊያገለግል ይችላል፡፡
- አስተያየት ለመስጠት [email protected] መጠቀም ይቻላል፡፡