ለገጠሪቱና ከተሜይቱ ቪክቶሪያ ሁለት የኮቪድ-19 ገደብ ማርገቢያ ፍኖተ ካርታዎች ሊዘረጉ ነው

*** የኒው ሳውዝ ዌይልስ - ቪክቶሪያ ወሰኖች ከዓርብ ጀምሮ በገደብ ክፍት ይሆናሉ

Amharic News 01 September 2020

Victorian Premier Daniel Andrews Source: AAP

በዛሬው ዕለት ቪክቶሪያ ውስጥ 70 ሰዎች በኮሮናቫይረስ መያዝንና የዓምስት ሰዎች ሕይወት ማጣትን ተከትሎ ፕሪሚየር ዳንኤል አንድሩስ ለቪክቶሪያ ገጠርና ከተሞች ሁለት ፍኖተ ካርታዎችን እሑድ ሴፕቴምበር 6 ይፋ እንደሚያደርጉ ገለጡ።

የፍኖተ ካርታዎቹ ለየፊና መሆንም በገጠርና በከተማ ያሉት "ተግዳሮቶች የተለያዩ ስለሆኑ ነው" ብለዋል።

አክለውም ተጥለው ያሉትን ገደቦች የማላላቱ ውሳኔ "ዕለታዊ የቫይረሱ መስፋፋት ቁጥሮችን፣ ሳይንሳዊ መሠረትን የተመረኮዘ ጭብጥና የሕክምና ምክርን" ተከትሎ እንደሚደሚሆን ተናግረዋል።  

በዛሬው ዕለት በኮሮናቫይረስ ሳቢያ ለሕልፈተ ሕይወት ከተዳረጉት ውስጥ ሁለት ሴቶች በ70ዎቹ፣ ሁለት ሴቶች በ80ዎቹና አንድ ሴት በ90ዎቹ የነበሩ ናቸው።

በአሁኑ ወቅት 421 ቪክቶሪያውያን ሆስፒታል ተኝተው ሕክምና እየተከታተሉ ሲሆን 20 ሕሙማን በፅኑ ሕመምተኞች ክፍሎች እንዲሁም ሰባት በሰው ሠራሽ መተንፈሻ የሕክምና እርዳታ እያገኙ አሉ። 

እስካሁን በቪክቶሪያ 2519 ሰዎች በኮሮናቫይረስ ተይዘው ያሉ ሲሆን 352 የጤና ሠራተኞች 139ኙ የገጠር ነዋሪዎች ናቸው።

ፕሪሚየር አንድሩስ Geelong, Great Bendigo እና Ballarat ከቫይረሱ መስፋፍት ጋር በተያያዘ "በጣሙን አሳሳቢ" ክፍለ ከተሞች እንደሆኑ ጠቅሰዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለም ፕሪሚየር አንድሩስ የቪክቶሪያን አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንደወጠኑት በ12 ወራት ማራዘም ባይቻላቸውም ሶስት ተጨማሪ የድጋፍ ድምጾችን በማግኘት ለስድስት ወራት ለማራዘም ይሁንታን አግኝተዋል።

እስካሁን ተጥሎ ያለው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ገደብ ሴፕቴምበር 13 ያበቃል።

ቫይረስ - ወሰን

የኒው ሳውዝ ዌይልስ - ቪክቶሪያ ወሰኖች አካባቢ ነዋሪዎች ከዓርብ ሴፕቴምበር 4 ጀምሮ ተጥለው የነበሩ የጉዞ ገደቦች ይነሱላቸዋል።

የኒው ሳውዝ ዌይልስ መንግሥት በሁለቱም ከፍለ አገራት እስከ 50 ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ የመንቀሳቀሻ ዞን አበጅቷል።

ፈቅድ ያላቸው ተጓዦች በእነዚህ ሪጅን ውስጥ የንግድ እንቅስቃሴዎችን ማከናወን ሲችሉ ነዋሪዎችም አዘቦታዊ ኑሮአቸውን መቀጠል ይችላሉ።  

ከዚህ ውሳኔ ላይ መድረስ የተቻለው ቪክቶሪያ ውስጥ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መስፋፋት ማሽቆልቆልን ምክንያት በማድረግ መሆኑን ፕሪሚየር ግላዲስ በርጂክሊያን አስታውቀዋል።  

በዛሬ ዕለት ኒው ሳውዝ ዌይልስ ውስጥ 13 ሰዎች በኮሮናቫይረስ ተጠቅተዋል።

 

 

 

 


Share
Published 1 September 2020 5:17pm
Updated 1 September 2020 5:21pm
By NACA
Presented by Kassahun Seboqa Negewo

Share this with family and friends