ብፁዕ አቡነ ማቲያስ - የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ የካቲት 24 / 2016 በተከበረላቸው 11ኛ በዓለ ሲመተ ክህነት ባደረጉት ንግግር የሃይማኖት አባቶችን መንፈሳዊ ተልዕኮ፣ የምዕመናን ሚና፣ ኢትዮጵያንና ቤተ ክርስቲያንን የገጠሟቸውን ፈተናዎች አንስተው አቅጣጫ አመላካች ብርቱ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ብፁዕነታቸው በርካታ ሁነኛ ጉዳዮችን አንስቶ ባስገነዘበው የበዓለ ሲመተ ክህነት ንግግራቸው፤
"የዘመናችን ትውልድ ከተግባር ይልቅ አስመሳይ ሆኖ መታየትን፣ ከቅድስና ይልቅ ነውረ ሃጢያትን፣ ከትህትና ይልቅ ትዕቢትን የተለማመደ" እንደሁ ገልጠዋል።
የቤተ ክርስቲያን አባቶችን ሚና በማስመልከትም ሕፀፆችን በመንቀስና መንፈሳዊ ኃላፊነትን የመወጣትን ተግባራት ሲያመላክቱም፤
" ኃላፊነቱን የተረከብነው ጥፋት ሲፈፀም ዝም ብሎ ለማየትና አዳማቂ ለመሆን አልነበረም። ከቅዱስ ወንጌሉ ፍንክች ሳንል የእውነት፣ የፍትሕ፣ የሰላም፣ የፍቅር፣ የይቅርታ፣ የአንድነትና የስምምነት ጠበቃ መሆናችንን ማሳየት ነበረብን።
"ሰውን ሁሉ በእኩልነት መቀበልና የሁሉም የእኩል አባቶች መሆናችንን በተግባር ማስመከር ይገባን ነበር። የተዛባውን በማረም ትውልዱን ለማዳን ያደረኘው ጥረት የሚያረካ እንዳልሆነ ታዛቢው ሁሉ አይቶብናል" ብለዋል።
አክለውም "ደመወዛችሁ ይብቃችሁ የሚለውን አምላካዊ መርህ ዘንግተን የእዚህ ዓለም ንዋይ እያሸነፈን ነው። ዓለምን ልናሸንፍ እንጂ፤ በዓለም ልንሸነፍ አልተጠራንም። በእዚህ ምክንያት የብዙ ምዕመናን ልብ ወደ ኋላ እንዲያፈገፍግ ምክንት እንዳንሆን ልንጠነቀቅ ይገባናል" ሲሉ አበክረው አሳስበዋል።
የሃይማኖት አባቶች አስተምህሮቶችንም አስመልክተው፤
"የእኛ አስተምህሮት አትግደል እንጂ ግደል ሊሆን አይችልም። የእኛ ተግሳፅ አትስረቅ፣ አትዋሽ፣ የሌላውን አትመኝ፣ አታመንዝር የሚል እንጂ፤ በተመሳሳይ የፆታ ጋብቻ ወደ ነውረ ሐጢያት ተሰማራ የሚል ትምህርት መቼውንም ሊኖር አይችልም፤ የለንምም።
"ከዘመኑ የወሬ ሱሰኛ መሳሪያን መሣሪያን እየተበደርን ከቅዱስ ወንጌሉ ጋራ የሚጣረስ ንግግርና አስተምህሮ ማስተላለፍ ለምን አስፈለገ?
"የእኛ ዘላቂ ፖለቲካ ቅዱስ ወንጌል ነው። ዘላለማዊውን ትተን ጊዜያዊውን፣ መለኮታዊውን ትተን ሰዋዊውን አንከተል። ይህ ለእኛ የሞራል ዝቅጠት ያስከትልብናል...አንዱ ጋ ተለጥፎ ሌላውን ሌላውን ዘልፎ መናገር የቆምንለት ቅዱስ ወንጌል አይፈቅድልንም" ሲሉ አፅንዖት ሰትተው አስገንዝበዋል።
ብፁዕነታቸው ፖለቲከኞችንም በተመለከተ፤
"ፖለቲከኞች በሌሉበትና ባልተፈቀደላቸው፤ ሌላው ቀርቶ የተቋቋሙበት ሕገ መንግሥት እንኳ የማይፈቅድላቸውን በቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ላይ ጣልቃ እየገቡ የግል ፍላጎትና ዓላማን ለማስፈፀም መሞከር ፍጹም ስህተት ነው። ተቀባይነትም የለውም።
"ለቤተክርስቲያን ብቻ ሳይሆን ለራሳቸውም ለፖለቲከኞቹም አይበጅም። ሁሉም ድንበሩን ጠብቆ በጋራ ጉዳዮች ላይ መምከር፣ በመከባበርና ተግባብቶ መሥራት ይሻላል። በእዚህ መንፈስ ቤተ ክርስቲያናችንና መንግሥት ተናብበው ቢሠሩ በሀገር ላይ ሰላም ይሰፍናል" ብለዋል።
በንግግራቸው ማጠቃለያም " በቤተ ክርስቲያናችን ላይ እጃቸውን የሚሰነዝሩ ወይም ጣታቸውን እየቀሰሩ የሚገኙ ሁሉ ቤተ ክርስቲያን ጠላታቸው አይደለችምና እጃቸውን እንዲያነሱ፤ መንግሥትም ለቤተ ክርስቲያን የሕግ ከለላና ጥበቃ እንዲያደርግ በእግዚአብሔር ስም ጥሪያችንን እናስተላልፋለን" ሲሉ ተናግረዋል።