የቪክቶሪያ መንግሥት ተጨማሪ ገደቦችን አላላ

** ቤተሰቦች እስከ 20 ሰዎች መጠያየቅ - ምግብ ቤቶችና ካፌዎች እስከ 50 ደንበኞችን ማስተናገድ ይችላሉ

Statement of Victoria State Government

Victorian Premier Daniel Andrews Source: AAP

የቪክቶሪያ ፕሪሚየር ዳንኤል አንድሩስ በኮቪድ - 19 ወረርሽኝ የተነሳ የተጣሉ ገደቦች በተጨማሪ እንዲረግቡ መንግሥታቸው መወሰኑን አስታውቀዋል።

በዚህም መሠረት፦

ከማክሰኞ ሜይ 26 2020 ጀምሮ ትምህርት ቤቶች በመማሪያ ክፍሎቻቸው ውስጥ ተማሪዎችን ማስተማር ይጀምራሉ።

ከቤት ውጭ የመጫወቻ ሥፍራዎችና የጋርዮሽ የአካል እንቅስቃሴ መሥሪያዎች ክፍት ይሆናሉ።

ከ11:59 pm ሜይ 31 ጀምሮ ቪክቶሪያውያን ቤታቸው ውስጥ እስከ 20 የሚደርሱ ሰዎችን ማስተናገድ ይችላሉ። ያም ማለት፤ አምስት የቤተሰብ አባላት ያላቸው ተጨማሪ 15 ሰዎችን አክለው ማስተናገድ ይችላሉ። ከቤት ውስጥ ውጭ የመሰባሰብ ቁጥርም እስከ 20 ከፍ ብሏል።  

እንግዶች አስተናጋጃቸው ቤት ውስጥ ማደር ይችላሉ። የቱሪዝም ኢንዱስትሪ የመኝታ ክፍሎችም ለአዳር ግልጋሎት መስጠት ይጀምራሉ።

የሠርግ ሥነ ሥርዓት ላይ ከሙሽሮቹና የሥነ ሥርዓቱ መሪዎች በተጨማሪ እስከ 20 ታዳሚዎች፣ በቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ ከሥነ ሥርዓቱ አስኪያጆች ሌላ እስከ 50 ለቀስተኞች መገኘት ይችላሉ።   

የሃይማኖት ሥነ ሥርዓቶች ላይ ሥነ ሥርዓቱን ከሚመሩት በተጨማሪ እስከ 20 የእምነቱ ተከታዮች ሊገኙ ይችላሉ። 

ቤተ መጻሕፍት፣ የወጣቶች ማዕከላትና የማኅበረሰብ ግልጋሎት መስጫ ተቋማት ከግልጋሎት ሰጪዎቹ በታካይነት ከ20 ያልበለጡ ተገልጋዮችን ማስተናገድ ይቻላሉ።

ከ11:59pm ሜይ 31 ጀምሮ ጋለሪዎች፣ ሙዚየሞች፣ መኪና ውስጥ ሆኖ ሲኒማ መመልከቻዎችን የመሳሰሉ የመዝናኛና ባሕላዊ ተቋማት መስተንግዶቻቸውን መስጠት ይቀጥላሉ። እንዲሁም፤ መካነ አራዊት (zoo) እና የውጭ መጫዎቻ የሽርሽር ሥፍራዎች አካላዊ ርቀቶች በተጠበቁበት መልኩ በአንድ ጊዜ ከ20 ያልበለጡ ሰዎችን ያስተናግዳሉ። የቤት ውስጥ ግልጋሎት ተስተናጋጅ የሆኑ ሰዎችን ስም፣ አድራሻና የስልክ ቁጥሮችን መመዝገብም ግድ ይላል። 

የመዋኛ ሥፍራዎች የጥንቃቄ መመዘኛዎችን ባሟላ ሁኔታ እስከ 20 ለሚደርሱ ሰዎች ክፍት ይሆናሉ።

የማኅበረሰብ ስፖርቶች አካላዊ ርቀቶችን በጠበቀ መልኩ እስከ 20 ሰዎች ማጫወት ይፈቀድላቸዋል። ፕሮፌሽናል ስፖርቶች ላይ የተጣሉ ገደቦች ጸንተው ይቆያሉ። 

የውበት ሳሎንና እንደ ጥፍር ሳሎን፣ ስፓዎችና የንቅሳት የግል ክብካቤ ግልጋሎት መስጫዎች የርቀት ሥፍራን በጠበቀ ሁኔታ ደንበኞቻቸውን ማስተናገድ ይችላሉ። ግልጋሎት የሰጧቸውን ደንበኞች ስም፣ አድራሻና የስልክ ቁጥሮች ተቀብለው መያዝ ይጠበቅባቸዋል።

የጨረታና የግዢና ኪራይ ጉብኝቶች ክፍት ይሆናሉ። እስከ 20 ሰዎችን ማስተናገድ ሲችሉ፤ ስም፣ አድራሻና የስልክ ቁጥሮች ተቀብለው የማስቀመጥ ኃላፊነት አለባቸው።

ምግብና መጠጥ አልባ ገበያዎች እንዲሁ ከ11:59 pm ሜይ ጀምሮ ክፍት ይሆናሉ።

የማኅበረሰብ ቫይረስ ተጋቦቱ መጠን ቀንሶ ከቀጠለና የምርመራው ቁጥር እየጨመረ ከሔደ ከጁን 20 በኋላ ተጨማሪ ገደቦች ሊላሉ ይችላሉ።

ከዚያ በኋላም ምግብ ቤቶች፣ ካፌዎች፣ ጋለሪዎች፣ ሙዚየሞች፣ ሲኒማዎችና ቲያትር ቤቶች እስከ 50 ደንበኞችን ማስተናገድ ይፈቀድላቸዋል።

የበረዶ መንሸራተት ወቅትን ጓጉተው የሚጠብቁ ነዋሪዎች ከጁን 20 በኋላ የግልጋሎቱ ተጠቃሚ ሊሆኑ ይችላሉ።

ይህ በእንዲህ እንዳለም፤ የቪክቶሪያ መንግሥት የላሉትን ማኅበራዊ ግልጋሎቶች ለሚጠቀሙ ሁሉ ሁሌም ጥንቃቄ ከማድረግ እንዳይዘናጉና ማድረግ የሌለባቸውን ነገሮች እንዳያደርጉ አክሎ አሳቧል።




Share

Published

Updated

Presented by Kassahun Seboqa Negewo

Share this with family and friends