የአሜሪካ ሕግ አስከባሪ አካል ባለስልጣናት ቀደም ሲል በበርባን ጎዳና ኒው ኦርሊየንስ የ2025 አዲስ ዓመት ቅበላ ታዳሚዎችን በቀላል የጭነት መኪና በገጨ አንድ አሽከርካሪ የ10 ሰዎች ሕይወት ማለፍንና ከ30 በላይ መቁሰልን ቢገልጡም፤ ከሰዓታት በኋላ የሟቾቹ ቁጥር 15 መድረሱን አስታውቀዋል።
የዩናይትድ ስቴትስ ፌዴራል ቢሮ ምርመራ ድርጊቱን በሽብር ጥቃት የፈረጀ ሲሆን፤ ጥቃቱም በአንድ ግለሰብ ቅንብር ብቻ የተካሔደ ሳይሆን ተጨማሪ እጆች ሊኖሩት እንደሚችል ያለውን ጥርጣሬ አክሎ ገልጧል።
ተሽከርካሪው ውስጥም በሽብር ድርጅትነት የተፈረጀው የእስላማዊ መንግሥት መለያ ባንዲራ መገኘቱንም አመላክቷል።
Witnesses say a white pick-up truck slammed through a barricade at high speed and hit pedestrians. Credit: AP / Gerald Herbert
ይህ በእንዲህ እንዳለም፤ ላስ ቬጋስ በሚገኘው ትራምፕ ሆቴል ፊት ለፊት አንድ ቴዝላ ሳይበርትራክ ፈንድቶ መጋየቱ ተመልክቷል።
የላስ ቬጋስ ሸሪፍ ኬቨን ማክማሂል የተሽከርካሪው ከሆቴሉ ፊት ለፊት መጋየት ሪፖርት የተደረገው 8:40 a.m. አካባቢ መሆኑን ጠቅሰው፤ በጋየው መኪና ውስጥም ለጊዜው ወንድ ይሁን ሴት መሆኑን ባያውቁም አንድ ሕይወት አልባ ግለሰብ መታየቱን ገልጠዋል።
አያይዘውም ሰባት ግለሰቦች ላይ "ቀላል" የመቁሰል አደጋ መድረሱን ተናግረዋል። ተሽከርካሪውም የኪራይ መሆኑ ታውቋል።
ፕሬዚደንት ጆ ባይደንም እንደ ኒው ኦሪሊየንሱ የላስ ቬጋሱም ቴዝላ ሳይበርትራክ ጉዳይ የዐቃቤ ሕግ ትኩረት እንደሚኖረው አስረድተዋል።
የሁለቱ ኒው ኦርሊየንስና የላስ ቬጋስ ጥቃቶች ተያያዥነት ይኖራቸው እንደሁ ለጊዜው ምርመራዎች እየተካሔደባቸው መሆኑን ከመግለጥ ባሻገር ይፋ መግለጫ አልተሰጠባቸውም።