ተሰናባቹ የዲክሰን ፌዴራል ምክር ቤት አባል፣ የሊብራልና የተቃዋሚ ቡድን መሪ ፒተር ዳተን ምንም እንኳ ለ2025 የፌዴራል ምርጫ ለድል አድራጊነት ተስፋ አድርገው የነበረ ቢሆንም ድል መነሳታቸው አምነው ተቀብለዋል።
አቶ ዳተን "በእዚህ ምርጫ በመልካም አልተወጣንም፤ ለእዚያም ዛሬ ምሽት ሙሉ ኃላፊነቱን እወስዳለሁ። ቀደም ሲል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዘንድ ስለ ዛሬ ምሽቱ ስኬታማነታቸው እንኳን ደስ አለዎት ለማለት ደውያለሁ። ለሌበር ታሪካዊ ወቅት ነው፤ ለእዚያም ዕውቅናችንን እንቸራለን" ብለዋል።
አክለውም ተቀናቃኛቸውና ድል ነስተው የምክር ቤት ወንበራቸውን የተረከቧቸው የሌበር ዕጩ አሊ ፍራንስ ዘንድም ደውለው እንኳን ደስ ያለዎት ማለታቸውንና ወ/ሮ ፍራንስ ማለፊያ ሥራን እንደሚሠሩ ተናግረዋል።
ወ/ሮ ፍራንስ ለ24 ዓመታት የዲክሰንን ምክር ቤት ይዘው ቆይተው የነበሩትን ፒተር ዳተንን ለማሸነፍ የበቁት ለሶስተኛ ጊዜ ባደረጉት ጥረት ነው።
የሊብራል ፓርቲ ተሰናባቹን የፓርቲ መሪ ፒተር ዳተንን ለመተካት አዲስ መሪ ማፈላለግ መጀመሩንና አንገስ ቴይለርና አንድሩ ሄስቲ ስም ለጊዜው የተጠቀሰ ሲሆን፤ በቀጣይ ቀናት ውስጥ ይፋ የሚሆን ይሆናል።