“የአቦል አዳዲስ ይዘቶች ማስተዋወቂያና የአፋፍ ቴሌኖቬላ ማጠናቀቂያ” ልዩ ዝግጅት ተከናወነ

የሕንድ ኤምባሲ ለባለሙያዎች የፊልም ጥበብ የትምህርት ዕድል እንደሚሰጥ አስታወቀ

Abol1.png

Credit: Supplied

ጥቅምት 19 ቀን 2017 ዓም በኢትዮጵያ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መጻሕፍት አገልግሎት አዳራሽ ( ወመዘክር ) በተከናወነው “የአቦል አዳዲስ ይዘቶች ማስተዋወቂያና የአፋፍ ቴሌኖቬላ ማጠናቀቂያ” ልዩ ዝግጅት ላይ የተገኙት የባሕልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ነፊሳ አልመህዲ " ዲኤስቲቪ በኢትዮጵያ የፊልም ጥበብ እንዲጎለብት በፋይናንስና በስርጭት እያደረገ ያለው አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነው። በርካቶች የፊልም ጥበብ ባለሙያዎች ይህንን በመጠቀም እየተንቀሳቀሱ ነው" ሲሉ ተናግረዋል።
Nefisa Almahdi.png
Nefisa Almahdi, State Minister for Culture and Sport. Credit: Supplied
ሚኒስትር ዴኤታዋ አክለውም ለዚህ ማሳያ የሆነው " አፋፍ ተከታታይ ድራማ በፕሮዳክሽን ጥራትም በይዘትም ምሳሌ በሚሆን መልኩ ተዘጋጅቶ ሲቀርብ ነበር" ብለዋል።

በስኬት በመጠናቀቁም የይዘት ባለቤቱን ዲኤስቲቪ አቦል ቴሌቪዥንና አዘጋጁን ሚካኤል ሚሊዮንን ( ሰውኛ ፕሮዳክሽን ) እና አባላቱን እንኳን ደስ ያላችሁ ያሉ ሲሆን፤ ሚኒስትር ዴኤታዋ “ዲኤስቲቪ በስፖርቱ ነው የበለጠ የሚታወቀው ፣ በፊልምና መዝናኛ ይዘቶቹ እየሰራቸው ያሉ ስራዎችን እንደ ስፖርቱ ማስተዋወቅ ይጠበቅበታልም” ሲሉም አበረታተዋል።

የመልቲቾይዝ ( ዲኤስቲቪ ) ኢትዮጵያ የሬጉላቶሪና ኮርፖሬት ጉዳዮች ኃላፊ አቶ መታሰቢያ በላይነህ በበኩላቸው የኢትዮጵያን እሴትና ባሕል ጠብቀው የሚዘጋጁ ሀገርኛ የቴሌቪዥን ይዘቶች ከአቦል ቴሌቪዥን ስርጭት መጀመር በኋላ በጥራትና በብዛትም መበራከታቸውን ገልጸዋል።
Metasebya Belayneh.png
Metasebya Belayneh, Head of Multi-choice (DSTV) Ethiopia Regulatory and Corporate Affairs. Credit: Supplied
በአቦልና ማዲ አቦል በተሰኙ የኤምኔት ቻናሎች አማካኝነት በዲኤስቲቪ በአማርኛና አፋን ኦሮሞ የሚተላለፉ ይዘቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የተናገሩት መታሰቢያ በአፋፍ የታየው የቀረጻ መንደር ገንብቶ በጥራት ፕሮዳክሽን መስራት በሌሎችም እንደሚደገም እምነታቸውን ገልፀዋል።

መልቲቾይስ ለሀገርኛ ይዘቶች መጎልበትም አበክሮ ይሰራል ብለዋል። በመድረኩ የእሳት እራት፣ አሻራ፣ የልቤ፣ አላውቅም አናውቅም፣ እሹሩሩ፣ ምሕረት፣ ደማቆቹ፣ እንሞካከር፣ ስፍራሽ ብዙ፣ ሁለት ጓዳ፣ Ardaa Jilaa, Kiloolee እና Abbaa Karraa S3 ጨምሮ ሌሎችም እንዲተዋወቁ ተደርጓል።

በተወዳጅነት ለ281 ክፍሎች በሳምንት ለ5 ቀናት ሲተላለፍ የቆየው የአፋፍ ቴሌኖቬላ ሾው ራነር፣ ዳይሬክተርና ተዋናይ ሚካኤል ሚሊዮን በበኩሉ ዲኤስቲቪ በአቦል ቻናል ለኢትዮጵያ የፊልም ባለሙያዎች የፈጠረውን ዕድል አመስግኗል።
Actor Michael Million.png
Actor Michael Million. Credit: Supplied
አፋፍ በፕሮዳክሽንና በይዘት ጥራት፣ አንጋፋና ወጣቶችን ማቀናጀቱ፣ በሲኒማ ደረጃ ፕሮዲዩስ መደረጉና የቀረፃ ፊልም መንደር ተገንብቶ መሰራቱ ዓይነተኛ ማሳያዎች እንደነበሩ የተናገረው አርቲስቱ በይዘትም በፕሮዳክሽንም ጥራቱንና ተወዳጅነቱን እንደጠበቀ በመጠናቀቁም የቴሌኖቬላውን አባላትና ድጋፍ ያደረጉ አካላት አመስግኗል።

የአቦል አዳዲስ ተከታታይ ድራማዎች አዘጋጆች በመድረኩ ልምዳቸውንና የአቦልን አስተዋፅኦ ያጋሩ ሲሆን ይዘቶቻቸውንም አስተዋውቀዋል። አንተህ ኃይሌ ስለ “የእሳት እራት” ቴሌኖቬላ፣ ኑር አክመል ስለ “አሻራ” ቴሌኖቬላ፣ ፌቨን ከተማ ስለ “የልቤ” ድራማ እንዲሁም ኡስማን አወል ስለ ማዲ አቦል ይዘቶች ገለፃ አድርገዋል።

የተጠናቀቀው አፋፍ ቴሌኖቬላ አባላትም ስለ ትወና፣ ፕሮዳክሽን ማኔጅመንትና አጠቃላይ ይዘት ልምዳቸውን አጋርተዋል።

የዘንድሮ የጉማ አዋርድ የቴሌቪዥን ተከታታይ ምርጥ ተዋናይት ዘርፍ አሸናፊዋና የአፋፍ መሪ ገፀባሕሪይና ፕሮዲዩሰር መዐዛ ታከለ ( እስከዳር ) በዚሁ መድረክ ተመስግናለች።

በመድረኩ የተገኙት በኢትዮጵያ የሕንድ ኤምባሲ ም/ሰክረተሪ የሆኑት ሺሪ ራንጅት ኩማር ሕንድ ለኢትዮጵያ ፊልምና ባህል ዕድገት በተለያየ መልኩ ድጋፍ እያደረገች መሆኑን አስታውሰው በአቦል ቴሌቪዥን አማካኝነት እየተዘጋጀ ሲቀርብ ለነበረውና በሰውኛ ፕሮዳክሽን በላቀ ጥራት ለተሰራው አፋፍ ቴሌኖቬላ አድናቆታቸውን ገለፀዋል።
Abol IV.png
Credit: Supplied
በአፋፍ ለተሳተፉ ባለሙያዎችም በሕንድ የትምህርት ዕድል ለመስጠትም ቃል ገብተዋል።

ደማቅ ሆኖ በተጠናቀቀው በዚህ ልዩ ዝግጅት የታደሙት የአዲስ አበባ ባህል፣ ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ኃፍታይ ገ/እግዚአብሔር ዲኤስቲቪ /አቦል የኢትዮጵያ ፊልሞች እንዲዘጋጁና የላቀ ተደራሽነት እንዲኖራቸው እያደረገ ያለውን አስተዋፅኦ አድንቀዋል።

ሰውኛ ፕሮዳክሽንም የአፋፍ ቴሌኖቬላን የቀረፃ መንደር ገንብቶ ማዘጋጀቱ ለፊልም ኢንዱስትሪው ትልቅ ትምህርት ነው ያሉ ሲሆን መስሪያ ቤታቸውም ለዘርፉ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

መርሃግብሩ አስተዋፅኦ ላደረጉና በአፋፍ የዝግጅት ሂደት ለተሳተፉ ባለሙያዎች የዕውቅና የምስክር ወረቀት በመስጠት ተጠናቋል።

Share
Published 3 November 2024 10:45pm
Updated 4 November 2024 8:43am
By Demeke Kebede
Source: SBS

Share this with family and friends