የቪክቶሪያ ተጠባባቂ ፕሪሚየር ጄምስ ሜሊኖ ሜልበርንና ሪጂናል ቪክቶሪያ ላይ ተጥለው የነበሩት የኮሮናቫይረስ ገደቦች ከነገ ሐሙስ ጁን 10 ከምሽቱ 11.59pm ጀምሮ እንደሚነሳ ዛሬ አስታውቀዋል።
በዚህም መሠረት፤
ማኅበራዊ
ከዚህ ቀደም ከቤትዎ ለመውጣት ምክንያት የነበሩ አምስት ጉዳዮች ተነስተዋል።- መሠረታዊ ለሆኑ የገበያ ሸመታ
- ለሌሎች ክብካቤ ለማድረግ
- ፈቃድ ያለው የሥራ ገበታ ላይ ለመሠማራት
- እስከ ሁለት ሰዓት የሚደርስ የአካል እንቅስቃሴ ለማድረግና
- ክትባት ለመከተብና ልዩ ፈቃድ
የኪሎ ሜትሮች ገደብ
ቀደም ሲል ከመኖሪያ ቤትዎ ርቀው መሔድ የሚችሉ እስከ 10 ኪሎ ሜትሮች ርቀት ድረስ ብቻ የነበረው ከሐሙስ እኩለ ለሊት ጀምሮ እስከ 25 ኪሎ ሜትሮች ርቀው መጓዝ ይችላሉ።
የንግሥት ኤልሳቤጥን ልደተ በዓል ተከትሎ ባለው ረጅም የሳምንቱ መጨረሻ ወደ ሪጂናል ቪክቶሪያ መጓዝ የተከለከለ ነው።
የፊት ጭምብሎች
በቤትዎ ውስጥ የ1 ነጥብ 5 ሜትሮች ርቀትን ለመጠበቅ በማይቻልባቸው ሁኔታዎች ካልሆነ በስተቀር የፊት ጭምብል ለማጠለቅ ግዴታ አይኖርም።
ትምህርት ቤቶች
ከዓርብ ጁን 11 ጀምሮ ትምህር ቤቶች ተማሪዎቻቸውን በመማሪያ ክፍሎች ውስጥ ማስተማር ይጀምራሉ።
የምግብና መስተንግዶ ሥፍራዎች
የምግብና መስተንግዶ ግልጋሎት ሰጪዎች ግልጋሎቶቻቸውን እስከ 100 ለሚደርሱ ደንበኞች መስጠት ሲችሉ ከ50 ላልበለጡ ተስተናጋጆች ተቀምጠው እንዲስተናገዱ ማድረግ ይችላሉ።
ሌሎች አካላዊ እንቃስቃሴ ማካሄጃ፣ የዳንስ ሳሎንና የምሽት ክለቦች ዝግ ሆነው ይቆያሉ።
ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ ከተካሄዱ 28,000 የቫይረስ ምርመራዎች ውስጥ አንድ ግለሰብ ብቻ በቫይረሱ ተይዟል።
የቪክቶሪያ ተጠባባቂ ፕሪሚየር ጄምስ ሜሊኖ በገደቡ ሳቢያ ጉዳት ለደረሰባቸው ንግዶች ተጨማሪ የ$8.36 ሚሊየን ድጎማ እንደሚሰጥ አስታውቀዋል።