የአውስትራሊያ መንግሥት ወደ ኢትዮጵያ ለሚጓዙ ወይም በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ ለሚገኙ ዜጎቹ የጉዞ ማስጠንቀቂያና የደኅንነት ማሳሰቢያ አውጥቷል።
ከወርኅ ማርች መጀመሪያ እስከ ዛሬ ማርች 13 ድረስ ፀንቶ ባለው ማስጠንቀቂያ መሠረት፤
አውስትራሊያውያን፤
- በሱዳን፣ ኤርትራ፣ ኬንያ፣ ደቡብ ሱዳን ወይም በጋምቤላ ክልልና በደቡባዊ ሶማሌ ክልል ድንበሮች አካባቢ፣
- የትግራይ ክልልና ሰሜናዊ የአማራ ክልል አካባቢዎችና የትግራይ አዋሳኝ የአፋር ክልል፣
- በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅና ምዕራብ ወለጋ እንዲሁም ቤንሻጉል ጉምዝ ክልል፣
- ከጂቡቲ ጋር ዓለም አቀፍ ድንበር ከሚጋሩት በስተቀር በሌሎች ዓለም አቀፍ ድንበር ተጋሪ አካባቢዎች እንዳይጓዙ አስጠንቅቋል።
በአዲስ አበባና ማዕከላዊ ኢትዮጵያ የሚዘዋወሩ ዜጎች ከፍ ያለ ጥንቃቄ እንዲያደርጉም አሳስቧል።
የአውሮፕላን በረራዎች ወደ ትግራይ መቀጠላቸውን ያነሳው የደኅንነት ማሳሰቢያ፤ የኢትዮጵያ የፀጥታ ሁኔታ ተለዋዋጭ በመሆኑ መንገዶች በማናቸውም ጊዜያት ሊዘጉ እንደሚችሉ አመላክቷል።
አያይዞም፤
- አሸባሪዎች ኢትዮጵያ ላይ ጥቃቶችን ሊሰነዝሩ እንደሚችሉ ሪፖርት መደረጉን ጠቅሶ፤ ጥቃቶቹ በአንስተኛ አለያም ያላንዳች ማስጠንቀቂያ ሊሰነዘሩ እንደሚችሉ አመልክቷል። የጥቃት ዒላማ ሊሆኑ የሚችሉትም ሆቴሎች፣ ገበያዎች፣ ሥርዓተ አምልኮ ማካሔጃ ሥፍራዎች፣ መንግሥታዊ ሕንፃዎች፣ የትራንስፖርትና አውሮፕላን ማዕከላት ሊሆኑ እንደሚችሉና በተለይም በብሔራዊ በዓላት ቀናት ዒላማ ሊሆኑ ይችላሉ ከሚባሉ ቦታዎች መገለል እንደሚገባ ጠቁሟል።
- የአመፅ ጥቃቶች ሊፈፀሙ ይችላሉ፤ በተለይም የውጭ አገር ዜጎች ዒላማዎች ሊሆኑ ይችላሉ። በመስቀል አደባባይ፣ ሃያት ሬጄንሲ፣ ሂልተንና ሸራተን ሆቴሎች፣ የካ ኮረብታዎች/እንጦጦና ቦሌ መንገድ ላይ ወይም በምሽት ዜጎች ብቻቸውን እንዳይጓዙ መክሯል።
- በሶማሌ ክልል ደቡባዊ ክፍሎችና በደቡብ ሱዳንና ኬንያ ድንበሮች አካባቢ የእገታ አደጋዎች ደረጃ ከፍተኛ ስለሆኑ፤ ከእኛ ምክር ውጪ እገታ ሊካሔዱባቸው በሚችሉባቸው አካባቢዎች የሚጓዙ ከሆነ ቢያንስ 'የፕሮፌሽናል ደኅንነት ምክርን' ያግኙ ብሏል።
- በኤርትራ፣ ሱዳንና ሶማሊያ ድንበሮች አካባቢ መሬት ላይ የተጠመዱ ፈንጂዎች አደጋ ስለሚያደርሱ ዜጎች ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አክሎ አሳቧል።