ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ድርጅት አምነስቲ ኢንተርናሽል፤ ጃኑዋሪ 29 / ጥር 20 በአማራ ክልል መራዊ ከተማ በኢትዮጵያ መከላከያ ኃይል አባላት በሰላማዊ ሰዎች ላይ ተፈፅሟል ያለውን ግድያ አስመልክቶ የአፍሪካና ሉላዊ የሰብዓዊ መብቶች ድርጅቶች በገለልተኛነት እንዲመረምሩት ጥሪ አቀረበ።
ድርጅቱ ኤፕሪል 12 / ሚያዝያ 4 ባወጣው መግለጫ ለሰላማዊ ሰዎቹ ሕይወት መጥፋት አስባቡ በመከላከያ ሠራዊቱና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል የተካሔደ ውጊያን ተከትሎ እንደሁ አመልክቷል።
አምነስቲ ኢንተርናሽናል በዕለቱ በቅድስት ማርያም ክብረ በዓል ዋዜማ አስከሬኖችን ከቀበሩ ግለሰቦች መካከል አነጋግሬያቸዋለሁ ያላቸውን አራት ሰዎችና አንድ ተአማኒ ያለውን ምንጮች ጠቅሶ ከ50 በላይ ሰዎች መገደላቸውን እንደገለጡለት አስታውቋል። ሆኖም የሟቾቹን ትክክለኛ ቁጥር ድርጅቱ በግሉ እንዳላረጋገጠም ጠቅሷል።
በማያያዝም፤ የተባብሩት መንግሥታት መርማሪዎች ሪፖርት መሠረት ትግራይ ውስጥ ብቻ ከ2020 አንስቶ ከ48 በላይ መጠነ ሰፊ ግድያዎች መፈፀማቸውንም አመላክቷል።
***
በትናንትንው ዕለት ሚያዝያ 4 ቀን 2016 በመዲናይቱ አዲስ አበባ ቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3 ልዩ ቦታው ሚሊኒዬም አዳራሽ አካባቢ ከፖሊስ ጋር በተካሔደ የተኩስ ልውውጥ ሳቢያ ሶስት የፋኖ ቡድን አባላት መገደላቸውን የከተማይቱ ፖሊስ አስታወቀ።
የአዲስ አበባ ፖሊስ "የፅንፈኛው ቡድን አባላት" ካላቸው ታጣቂዎች የፋኖ መሪ "ናሁሰናይ አንዳርጌ ታረቀኝ ቆስሎ ወደ ሕክምና ከተላከ በኋላ ሲሞት ፅንፈኛው አቤኔዘር ጋሻው አባት በተኩስ ልውውጡ መሃል ተገድሏል፡፡ ሀብታሙ አንድአርጌ ተሰማ የተባለው የቡድኑ አባል ሳይቆስል በቁጥጥር ስር ውሏል" ሲል በይፋ መግለጫው አስታውቋል፡፡
ከፖሊስ ሠራዊ አባላቱም ሳጅን አራርሳ ተሾመ እና ኮንስታብል ማቲያስ ጴጥሮስ መቁሰላቸውንና የፋኖ ታጣቂ አባላቱ አቶ እንዳሻው ጌትነት የተባሉ ግለሰብ በመኪናቸው እንዲጭኗቸው ቢያስገድዷቸውም ግለሰቡ አልተባበር በማለታቸው ተገድለዋል በማለት ገልጧል፡፡
***
እንግሊዝ ከኢትዮጵያ ወደ አገሯ በሚገቡ የአበባ ምርቶች ላይ ከሚያዝያ 03/2016 ጀምሮ ታሪፍ መጣል ማቆሟን የብሪታንያ ንግድ ኮሚሽን አስታወቀ።
የብሪታንያ ንግድ ኮሚሽን ባወጣው መግለጫ፤ ብሪታንያ የአበባ ምርቶችን ወደ ሀገራቸው በሚያስገቡ ነጋዴዎች ላይ ጥላው የነበረውን 8 በመቶ ግብር ማንሳቷን ነው የገለጸው፡፡
ይህም ውሳኔ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት አበባ አምራች እና ነጋዴዎችን ተጠቃሚ ከማድረጉ በተጨማሪ፤ ከእንግሊዝ ጋር በሚደረግ ግብይት በአገሪቷ በቂ የአበባ ምርት አቅርቦት እንዲኖር ያስችላል ተብሏል።
በዉሳኔው መሠረት አበባ አምራቹ አገር በቀጥታም ይሁን በሶስተኛ ሀገር አበባዉን ወደ እንግሊዝ ቢያስገባም ምንም ዓይነት ታሪፍ እንደማይኖረዉ ተነግሯል፡፡
ይህም በአበባ ምርቶች ላይ የተወሰደው የግብር እፎይታ ውሳኔ ለሁለት ዓመታት የሚቆይ ሲሆን፤ ከሚያዚያ 11/2024 ጀምሮ እስከ ሰኔ 30/2026 ድረስ ተግባራዊ እንደሚደረግ ተገልጿል፡፡
እንግሊዝ ይህን ውሳኔ የወሰነችው ከአፍሪካ ጋር ያላትን ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ለማሻሻል ካላት ፍላጎት የተነሳ መሆኑን አስታውቃለች፡፡
ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ሩዋንዳ፣ ታንዛኒያ እና ኡጋንዳ ከምስራቅ አፍሪካ ሀገራት መካከል አበባ ላኪ ሀገራት ሲሆኑ፤ ኢትዮጵያ በ2023 ዓመት ብቻ 12 ነጥብ 6 ሚሊዮን ፓውንድ ዋጋ ያላቸው የአበባ ምርቶችን ወደ ብሪታንያ መላኳ ተገልጿል፡፡
ከኬንያ ቀጥሎ በአፍሪካ ሁለተኛ የአበባ አምራች የሆነችው ኢትዮጵያ፤ በአህጉሪቱ ከሚመረተው ጠቅላላ የአበባ ምርት ውስጥ 23 በመቶውን ድርሻ ትሸፍናለች፡፡