ቋሚ ሲኖዶሱ ሰኞ የካቲት 4 ባወጣው መግለጫ፤ የተመሳሳይ ጾታ ጋብቻና ግብረ ሰዶማዊነትን አስመልከቶ እየተደረጉ ያሉ ሁለገብ ተጽእኖዎችንና መመሪያ የማስለወጥ ማግባባቶችን በጽኑ እንደሚቃወም ገልጿል።
“ይህ ግብረ ርኵሰት በዘመናችን ተቀባይነት እንዲኖረው የሚደረጉ ሁለገብ ማግባባቶች፣ ተጽዕኖዎችና ተያያዥነት ያላቸው ስምምነቶች በአገራችን መንግሥት ተቀባይነት አግኝተው እንዳይፈጸሙ” ሲልም ቋሚ ሲኖዶስ በጥብቅ አሳስቧል።
ከተለያዩ ምንጮች ያገኘውን መረጃ ዋቢ ያደረገው ቋሚ ሲኖዶሱ፤ ግብረ ሰዶማዊነትንና ተያያዥነት ያላቸውን ተግባራት የንግድ፣ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የፍትሕና የሰብዓዊነት ግንኙነቶች አካል በማድረግ በቃላትና በዓረፍተ ነገሮች ውስጥ አስርጎ በማስገባት አሣሪ ስምምነቶች እንዲፈጸሙ ለማድረግ ያለው ሂደት በአፋጣኝ እንዲፈተሽ ጠይቋል።
እንዲሁም፤ የሀገሪቷ መንግሥት ብሎም የአፍሪካ መንግሥታት የአህጉሪቷን ሃይማኖታዊ፣ ማኅበራዊና ሥነ ልቦናዊ ዕሴቶች አስጠብቀው እንዲቀጥሉ በማለትም ጥሪውን አቅርቧል።
በስምምነቱ ሰነድ ጤናማ መስለው የሠረፁ ዐረፍተ ነገሮች ውስጥ በጾታና ሥርዓተ ጾታ መብት፣ የሥርዓተ ጾታ ትምህርት ጋር በማያያዝ ጾታን በቀዶ ጥገና የመቀየር ውርጃ ልቅ የሆነ የተመሳሳይና ተቃራኒ ጾታ ግንኙነትን መፍቀድ፣ግለሰቦችን እና ማኅበረሰብን መረን በማድረግ ውስብስብ ለሆነ ሃይማኖታዊ፣ ማኅበራዊና ባህላዊ ችግሮች የሚዳርጉ ናቸውም ብሏል።
ይህን አስመልክቶ የሚደረጉ ስምምነቶች የሀገሪቷን ሃይማኖታዊ፣ ማኅበራዊና ሥነ ልቦናዊ ዕሴት የሚጥሱ መሆኑ ታውቆ የፈዴራል መንግሥትም ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እንዲከታተለው አሳስቧል።
ስለሆነም ግብረ ሰዶምን እና ተያያዥ የጾታ ሥርዓትን የሚበርዙ ተግባራት በሙሉ ሀገሪቷ በሃይማኖት፣ በሕግ፤ በማኅበራዊ ዕሴቶቿና በሥነ ምግባር መመሪያዎቿ የማትቀበላቸው ጉዳዮችና ልምምዶች ስለሆኑ በማናቸውም ይፋዊ ግንኙነቶች እንደማይቀበላቸውም ቋሚ ሲኖዶሱ አክሏል።
በምዕራቡ ዓለም የተመሳሳይ ፆታ ግንኙነቶች ከሰብዓዊ መብቶች ጋር ተያይዘው የሚታዩ ናቸው።