ሶስቱ የብዙኀን መገናኛ ባለሞያዎች፣ በአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁ ዐውድ ውስጥ በቁጥጥር ሥር ውለው በወራት ለሚቆጠር የተለያየ የጊዜ መጠን፣ በአዋሽ አርባ እና በአዲስ አበባ ታስረው መቆየታቸውን፣ ከጠበቆቻቸው አንዱ ጠበቃ እና የሕግ አማካሪ ዐዲሱ ጌታነህ ለአሜሪካ ድምፅ ገልጸዋል፡፡
ከሶስቱ መካከል፣ በቃል አላምረው እና በላይ ማናዬ፣ ትላንት ሰኞ፣ ሲፈቱ ቴዎድሮስ ዘርፉ ባለፍነው ቅዳሜ መፈታቱን ጠበቃቸው አቶ ዐዲሱ ጌታነህ ገልጸዋል፡፡
ሶስቱን የብዙኀን መገናኛ ባለሙያዎች ጨምሮ አራት እስረኞች፣ በጠበቆቻቸው አማካይነት፣ ባለፈው ማክሰኞ ሰኔ 4 ቀን፣ አካልን ነጻ የማውጣት ክስ መሥርተው ነበር፡፡
ፖሊስ፣ እስረኞቹን ዛሬ ማክሰኞ፣ ሰኔ 11 ቀን እንዲያቀርባቸው፣ የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት ትእዛዝ ሰጥቶ ነበር፡፡
ባለፈው ዓመት፣ ሐምሌ 30 ቀን 2015 ዓ.ም. በቁጥጥር ሥር የዋለው በቃል አላምረው፣ ከ10 ወራት በላይ የታሰረ ሲኾን፣ ቴዎድሮስ ዘርፉ ለ10 ወራት ያህል፣ በላይ ማናዬ ደግሞ ከሰባት ወራት በላይ፣ ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ቆይተው ነው የተለቀቁት፡፡
በሌላ በኩል፣ “ሁከት እና ብጥብጥ በማሥነሳት ወንጀል ጠርጥሬአቸዋለኹ” በሚል ፖሊስ በቁጥጥር ሥር አውሎ ምርመራ እያደረገባቸው የሚገኙት፣ የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ(ኢሕአፓ) ሊቀ መንበር ዝናቡ አበራን ጨምሮ ዘጠኝ ታሳሪዎች፣ በገንዘብ ዋስ እንዲፈቱ፣ የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት፣ ትላንት ሰኞ፣ ሰኔ 10 ቀን 2016 ዓ.ም. ወስኗል፡፡