የዩናይትድ ስቴትስ ባለስልጣናት እሥራኤል የኢራን ከተማ በሆነችው ኢስፋሃን ወታደራዊ ጥቃት መፈፀሟን ገለጡ።
ባለስልጣናቱ እሥራኤል የባይደን አስተዳደርን ወታደራዊ ጥቃቷን ከመፈፀሟ ቀደም ብላ ትናንት ኤፕሪል 18 / ሚያዝያ 10 በመጪዎቹ 24 ወይም 48 ሰዓታት ውስጥ ጥቃት ልትፈፅም ማሰቧን እንዳስታወቀች ጠቁመዋል።
ወታደራዊ ጥቃቱን ተከትሎም አውስትራሊያውያን አመቺና ደህንነታቸውን ለአደጋ የማያጋልጥ ሁኔታ ካለ ኢራንና እሥራኤልን ለቅቀው እንዲወጡ የአውስትራሊያ ፌዴራል መንግሥት የጉዞ ማሳሰቢያ ሰጥቷል።
አውስትራሊያ ሁለቱም አገራት ከቀጣይ ወታደራዊ እርምጃዎች እንዲቆጠቡም አሳስባለች።
ጥቃቱን አስመልክቶ ከእሥራኤል በኩል የማረጋገጫም ሆነ ማስተባባያ መግለጫ አልተሰጠም።
ይህ በእንዲህ እንዳለም፤ የኢራን ፋርስ የዜና ኤጄንሲ "ሶስት ፍንዳታዎች" መሰማታቸውን ሲያመለክት፤ የአገሪቱ የሕዋ ኤጄንሲ ቃል አቀባይ ሁሴን ዳሊሬይን በበኩላቸው "በርካታ" ድሮኖች "ስኬታማ በሆነ ሁኔታ መክነዋል" ሲሉ ተናግረዋል።

Credit: SBS News
ኢራን የድሮንና ሚሳይሎች ጥቃትን እሥራኤል ላይ ያደረሰችው፤ እሥራኤል ኤፕሪል 1 / መጋቢት 23 በሶሪያ የቆንስላ ጽሕፈት ቤቷ ላይ የአየር ጥቃት ሰንዝራ ሁለት ጄኔራሎቿን አክሎ የ12 ሰዎች ሕይወት መጥፋትን አስባብ በማድረግ እንደሁ ተዘገቧል።