የአውስትራሊያ ፌዴራል ተቃዋሚ ቡድን ጠቅላይ ሚኒስትር ስኮት ሞሪሰን ከእንግሊዙ የመድኃኒት አምራች ኩባንያ አስትራዜኔካ ጋር የኮቪድ - 19 ክትባት ምርትን ለአውስትራሊያ እንዲያዳርስ ተፈራርሜያለሁ ያሉት ተአማኒነት እንደሚጎድለው ጠቁሟል።
ሆኖም የፌዴራል መንግሥቱ በስምምነቱ መሠረት የኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ክትባት ሙከራ ስኬታማ ከሆነ ለሁሉም አውስትራሊያውያን እንደሚዳረስ አስታውቋል።
የሌበሩ ክሪስ ባወን ግና የፍላጎት መግለጫ ደብዳቤ እንደ መልካም መነሻ ቢቆጠርም የመድኃኒት አምራች ኩባንያው አስትራዜኔካ ግና አንዳችም የውል ስምምንት እንዳልተፈጸመ በይፋ መናገሩን ጠቅሰዋል።
አክለውም፤
"ጠቅላይ ሚኒስትሩ አውስትራሊያውያን ክትባቱን በቀዳሚነት ያገኛሉ ብለው ማለታቸው እውነት አይደለም። ሌሎች መንግሥታት ቀድመው ከስምምነት ላይ ደርሰዋል። በመጀመሪያ ይህ ስምምነት ለፍርርም የበቃው በወርኃ ሜይ አጋማሽ ላይ ነው። የእሳቸው መንግሥት ግና ይህን አላከናወነም። ምንም ዓይነት ማሽሞንሞን ቢደረግ ዕውነታውን መለወጥ አይቻልም" ብለዋል።
የፌዴራል መንግሥቱ በምላሹ የመጨረሻው የውል ስምምነት ሲካሄድ ስለ ክፍፍል፣ ጊዜና የክትባቱን ዋጋ እንደሚያሳውቅ ገልጧል።
ኮሮናቫይረስ - ቪክቶሪያ
በዛሬው ዕለት በኮሮናቫይረስ 12 ቪክቶሪያውያን ሕይወታቸውን ሲያጡ 216 በቫይረሱ ተይዘዋል።
በዚህ ሳምንት የቫይረሱ መስፋፋት ማሽቆልቅል ይዟል።
ፕሪሚየር ዳንኤል አንድሩስ ከሟቾቹ ውስጥ ሶስት ወንዶች በ70ዎቹ፣ አራት ሴቶችና አንድ ወንድ በ80ዎቹ፣ ሶስት ሴቶችና አንድ ወንድ በ90ዎቹ ዕድሜዎች የነበሩ መሆናቸውን ገልጠዋል።
ሁሉም ሕይወታቸው ያለፈው ሰዎች የአገረጋውያን መጦሪያ ነዋሪዎች የነበሩ ናቸው።
ቪክቶሪያ ውስጥ በቫይረሱ ሕይወታቸው ያለፉ ሰዎች ቁጥር 363 ሲደርስ በአገር አቀፍ ደረጃ 450 ደርሷል።
ኮሮናቫይረስ - ኢትዮጵያ
ተባለፉት 24 ሰዓታት ኢትዮጵያ 1,386 ሰዎች በኮሮና ቫይረስ መያዛቸውንና 28 ለሕልፈተ ሕይወት መዳረጋቸውን የኢትዮጵያ ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።
በአጠቃላይ እስካሁን በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 32,722 ሲደርስ 12,938 ሰዎች ከበሽታው አገግመዋል።
በጠቅላላው 572 ሰዎች በኮሮናቫይረስ ተጠቅተው ሕይወታቸው አልፏል።