በርክክብ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) ትውልድ ከታሪክ የሚማርበትን የኢትዮጵያ ጀግና የብርጋዲየር ጄነራል ለገሠ ተፈራን የክብር ቅርሶች የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም በቅርስነት መረከቡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን አንጋፋነትና ሀገራዊ ሀላፊነት ያመለክታል በማለት ገልፀዋል።
አሁን ያለውና ተተኪው ትውልድ ይማርበት ዘንድ የወንድሜን ታሪካዊ ቅርሶች ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም አስረክቤያለሁ ሲሉ ወ/ሮ ሙሉ ብርሃን ተፈራ የብርጋዲየር ጄነራል ለገሠ ተፈራ ፋውንዴሽን መስራች መናገራቸውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
የምንጊዜም ጀግና ሜዳይ ተሸላሚ የሆኑት የአየር ኃይል ጀት አብራሪው የብርጋዲየር ጄነራል ለገሠ የማዕረግ አልባሳት፣ ሜዳሊያዎች እና ልዩ ልዩ ታሪካዊ ቅርሶች፥ አርበኞች፣ ተጋባዥ እንግዶችና የጄነራል መኮንኑ ቤተሰቦች በተገኙበት ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ተሰጥተዋል።