"ሕገመንግሥታዊ ኃላፊነቱን ለመወጣትና በውጊያ ላይ ላሉት ኃይሎች የጋራ ድልድይ ሆኖ ለማነጋገርና ለማስማማት ያለውን ዝግጁነት ያስታውቃል" የኢትዮጵያ ዘውድ ምክር ቤት

የኢትዮጵያ ዘውድ ምክር ቤት ኢትዮጵያውያን 128ኛውን የአድዋ በዓል በአንድነት መንፈስ እንዲዘክሩና "ከገባንበት ወጥመድና ዝቅጠት ለመውጣት የሚረዳን፤ በሐምሌ 30 ቀን 1966 ዓ.ም የተነደፈውን ሆኖም ግን በሥራ ላይ ለመዋል ዕድል ያላገኘውን ሕገ መንግሥት አሁን ተቀብለን፤ የዲሞክራሲ አሠራርና የሕግ የበላይነት በሀገሪቱ እንዲሰፍኑ ስንጥር ነው" ሲል ባወጣው መግለጫ አሳሰበ።

Prince Ermias.jpg

HIH Prince Ermias Sahle-Selassie Haile-Selassie, President of the Crown Council of Ethiopia. Credit: SBS Amharic

በልዑል ኤርሚያስ ሳህለሥላሴ ኃይለሥላሴ ፕሬዚደንትነት የሚመራው የኢትዮጵያ ዘውድ ምክር ቤት ዘንድሮ የሚከበረውን 128ኛውን የአድዋ ድል በዓልና ወቅታዊውን የኢትዮጵያ ሁኔታ ትኩረቱ አድርጎ ሰሞኑ ባወጣው መግለጫ የድርድር፣ አገራዊ አንድነትና የሕገ መንግሥታዊ ትግበራ ጥሪ አድርጓል።

ምክር ቤቱ በመግለጫው "የኢትዮጵያ እጣፈንታ አሁን በእጃችን ላይ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ህዝቦችና የዘውድ ምክርቤቱ በአንድ አላማ እጅ ለእጅ ተሳስረው ለመስራት ዝግጁ መሆን አለባቸው" ብሏል።

አክሎም "ቸሩ አምላክ ረድቶን በ1888 ዓ.ም የኢትዮጵያ ጀግኖች፤ በዳግማዊ ምኒልክና በእቴጌ ጣይቱ መሪነት፤ የጣልያንን ጦር ድል ያደረጉበትን ቀን እያከበርን ስለሆነ ነው፡፡

"ታላቁ የአድዋ ድል፤ ለኢትዮጵያውያን የነፃነት ጮራ ያንጸባረቀና ክብራቸውንም ለአለም ህዝብ ያበሰረ በመሆኑ፤ የዘውድ ምክርቤቱ እስካሁን ድረስ፤ ይህንን የአንድነታችን ምልክት የሆነውን ቀን፤ ምን ጊዜም ከአእምሮአችን እንዳይጠፋ ሲታገል ቆይቷል፡፡

"በዛሬው ፀሎታችንም በ1933 ዓ.ም የኢትዮጵያ አርበኞች የጣልያንን ሁለተኛ የግፍ ወረራ ድል የተቀዳጁበትን ወቅት እንድናስታውስ የዘውድ ምክርቤቱ ይጠይቃል" በማለት አሳስቧል።

በማያያዝም "የዛሬው ፀሎታችን፤ በወቅቱ የሀገራችንን ህልውና ከባድ አዳጋ ላይ በመጣል ላይ ያለውን ጦርነትና ግጭት፤ ቸሩ አምላካችን መፍትሄ እንዲሰጥልን የምንማጸንበት ነው፡፡

"ነገርግን አንድ እውነት ግልጽ እንዲሆን እንፈልጋለን፡፡ ከገባንበት ወጥመድና ዝቅጠት ለመውጣት የሚረዳን፤ በሐምሌ 30 ቀን 1966 ዓ.ም የተነደፈውን ሆኖም ግን በስራ ላይ ለመዋል እድል ያላገኘውን ህገመንግስት አሁን ተቀብለን፤ የዲሞክራሲ አሰራርና የህግ የበላይነት በሀገሪቱ እንዲሰፍኑ ስንጥር ነው፡፡

"ዘውዱ፤ በኢትዮጵያ ዘውድ ምክርቤት አማካኝነት፤ ህገመንግስታዊ ሃላፊነቱን ለመወጣትና በውጊያ ላይ ላሉት ሃይሎች የጋራ ድልድይ ሆኖ ለማነጋገርና ለማስማማት ያለውን ዝግጁነት ያስታውቃል፡፡ በ1966 ዓ.ም በተነደፈው ህገመንግስት መሰረት፤ የኢትዮጵያ ዘውድ፤ በፓርላማ ምርጫ ሂደትና በመንግስት የእለት ስራ ውስጥ ጣልቃ መግባት አይችልም፡፡ ሆኖም ግን፤ ህገመንግስቱን ማስከበርና የኢትዮጵያዊያኖችን ህጋዊ መብትና ነፃነት ማስጠበቅ ግዴታው ነው፡፡

"ስለሆነም፤ በወቅቱ በውጊያ ላይ ያሉ የኢትዮጵያ ሃይሎች ሁሉ፤ ዘውዱ የሰላም ማውረድ አላማ እንዳለውና ይህንንም እርቅ ለማምጣት ዝግጁ መሆኑን እንዲረዱ እናሳስባለን" ብሏል።


Share

Published

Updated

By Kassahun Seboqa Negewo
Source: SBS

Share this with family and friends