ከሚሊየን በላይ የቪክቶሪያ ነዋሪዎች በዛሬው ዕለት የክፍለ አገር መንግሥት ለማቋም ድምፃቸውን እንደሚሰጡ ይጠበቃል።
ውጤቱም ለሶስተኛ ጊዜ ለመመረጥ በተወዳዳሪነት የቀረበውን የፕሪሚየር አንድሩስ ሌበር መንግሥትን ወይም በማቲው ጋይ የሚመራውን የተቃዋሚ ቡድን ለቀጣዩ አራት ዓመታት ስልጣን ላይ የሚያስቀምጥ ይሆናል።
የምርጫ ጣቢያዎች በመላው ቪክቶሪያ ከ 8am ጀምሮ ክፍት የሆኑ ሲሆን 6pm ላይ ይዘጋሉ።
የቪክቶሪያ የምርጫ ኮሚሽን ለመምረጥ ብቁ ከሆኑ ነዋሪዎች ውስጥ ገሚሶቹ ከዛሬው ዋነኛ የምርጫ ቀን በፊት ድምፃቸውን እንደሰጡ ግምት አሳድሯል። .
የክፍለ አገሩ የጤና ሥርዓትን ማጎልበት፣ ለኑሮ ውድነት ብልሃትን ማበጀትና ለክፍለ ከተማና አካባቢ የባቡር መገናኛ መስመሮች ተጨማሪ ድጎማን ማድረግ የሌበር፣ የቅንጅቱና የግሪንስ ፓርቲዎች ዋነኛ የምርጫ መቀስቀሻ አጀንዳዎች ነበሩ።
ፕሪሚየር ዳንኤል አንድሩስ ከኔትዎርክ ዘጠኝ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ
የምርጫ ጣቢያዎቹ እስከሚዘጉ ድረስ የምረጡን ቅስቀሳቸውን እንደማያቋረጡ፣ ነፃ የአፀደ ሕፃናት አገልግሎት፣ ነፃ የቴፍ ኮሌጅ ኮርሶችን መጨመር፣ ታዳሽ ኃይል ማጎልበት፣ የኤሌክትሪክ ኃይልን ለትርፍ ሳይሆን ለሕዝብ ጠቀሜታ ማዋልን ተቀዳሚ አጀንዳዎቻቸው በማድረግ እንደሚቀሉ ተናግረዋል።
በሌላም በኩል የሊብራልና ናሽናልስ ፓርቲ ቅንጅት መሪ ማቲው ጋይ በበኩላቸው፤ መራጮች የእሳቸውን ቅንጅት በመምረጥ የጤና ሥርዓቱን ለመጠገን፣ ለኑሮ ውድነት ብልሃት ለማበጀት እንዲያስችሏቸው በኔትዎርክ ዘጠኝ በኩል ጠይቀዋል።
ሌበር ተቃዋሚ ቡድኑን 54.5 ፐርሰንት ለ 45.5 ፐርሰንት በሆነ የሕዝብ አስተያየት ስብስብ እየመራ ሲሆን፤ ቅንጅቱ ለመንግሥትነት ራሱን ለማብቃት አሁን ባሉት 27 የምክር ቤት ወንበሮች ላይ 18 ተጨማሪ ወንበሮችን ማሸነፍ ግድ ይሰኛል።
የራቁት ፎቶግራፍ
በፎቶግራፍ ዓለም ሁነኛ ሥፍራ ያላቸው ፎቶግራፍ አንሺ ስፔንሰር ቱኒክ የቆዳ ካንሰርን አስመልክቶ ግንዛቤ ለማስጨበጥ 2500 ሰዎችን ገናና በሆነው የሲድኒ ቦንዳይ ባሕር ዳርቻ ራቁታቸውን ሆነው ፎቶግራፎችን አንስተዋል።
አቶ ቱኒክ ኩነቱን በተመለከተ ለ SBS ሲገልጡ 'ታላቅ ስኬት' ብለውታል።