በጠና ሕመም ምክንያት ለሕልፈተ ሕይወት የበቁት የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ፖፕ ፍራንሲስ የቀብር ሥነ ሥርዓት በሮም ሳንታ ማሪያ ማጆሪ ቤተክርስቲያን ተከናውኗል።
ከአንድ ክፍለ ዘመን በላይ በሆነ ጊዜ ውስጥ የአንድ የካቶሊክ እምነት ዋና መሪ የቀብር ሥነ ሥርዓት ከቫቲካን ውጪ ሲከናወን ይህ የመጀመሪያ ጊዜ ነው።
በቀብር ሥነ ሥርዓቱ ላይ የአውስትራሊያን ጠቅላይ እንደራሴ አካትቶ በርካታ የተለያዩ ሀገራት መሪዎች ተገኝተዋል።
የፖፕ ፍራንሲስ መካነ መቃብር ከእሑድ ማለዳ አንስቶ ለጎብኚዎች ክፍት እንደሚሆንም ቫቲካን አስታውቃለች።
ተተኪያቸውን የመምረጡ ኃላፊነት በካርዲናሎች አብላጫ ድምፅ አሰጣጥ ይወሰናል።
ምርጫ 2025
የአውስትራሊያ ሌበር ፓርቲ ዳግም ከተመረጠ በማናቸውም ሰዓት ነፃ አገልግሎት ለሚሰጥ ቴሌሄልዝ ማከናወኛ የሚሆን $204.5 ሚሊየን መመደቡን በዛሬው ዕለት አስታውቋል።
ይህንኑ የሌበር ፓርቲ የጤና ፖሊሲ ይፋ ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር አንቶኒ አልባኒዚ በምዕራብ ሲድኒ የምረጡኝ ዘመቻቸው ወቅት ሲሆን፤ 1800MEDICARE የ24/7 በሜዲኬይር የሚሸፈንና አገልግሎቱም በመላ አውስትራሊያ መሆኑንም አክለው ገልጠዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም፤ የተቃዋሚ ቡድን መሪ ፒተር ዳተርበመጪው ሳምንት ቅዳሜ ሜይ 3 የምርጫ ቀን በፊት በ28 የተለያዩ የፌዴራል ምክር ቤት መቀመጫዎች በሚገሚገኙባቸው ሥፍራዎች ተዘዋውረው የምረጡኝ ዘመቻቸውን እንደሚያከናውኑ ተነግሯል።
በሌላም በኩል፤ የሌበር ፓርቲ በሕዝብ አስተያየት ስብስብ ውጤት መሠረት የመሪነት ሥፍራን ይዟል የሚሉትን ሪፖርቶች በተለይም ከABC እና Guardian የሚወጡ ሪፖርቶችን ሰዎች አምነው እንዳይቀበሉ ሲሉ አሳስበዋል።
የሕዝብ አስተያየት ስብስብ ውጤት ሪፖርቶች እየቀረቡ ያሉት በሁሉም ዋነኛ የብዙኅን መገናኛ አውታሮች ቢሆንም፤ በተለይ ABC እና Guardian ላይ ለምን እንዳተኮሩ አልገለጡም።
በደምሳሳው "የጥላቻ ሚዲያ" ከማለት በስተቀር።