በመግለጫቸው “በወርኃ ሜይ 2021 ብፁዕ ፖፕ ፍራንሲስ ጋር ለመገናኘት መልካም ዕድል ገጥሞኝ ነበር" ያሉት የዘውድ ምክር ቤቱ ፕሬዚደንት “ፖፕ ፍራንሲስ ወደ ሰላም የሚያመራ ርሕራሔንና ድፍረትን የተላበሰ ተግባርን አዋድደዋል። ተልዕኳቸው በእኛ ግብር፣ በእኛ አገልግሎት፣ በእኛ ዕሴቶቻቸውን ኢትዮጵያ ውስጥና በመላው ዓለም በማራመድ ውሳኔ ሕያው ሆኖ ይኖራል” ሲሉ የፖፕ ፍራንሲስን ውርሰ አሻራዎችን የማስቀጠል ኃላፊነት የሁሉም ሰብዓዊ ድርሻ መሆኑን አበክረው አሳስበዋል።
ከአሥራ አምስተኛው ክፍለ ዘመን አንስቶ በኢትዮጵያና ቫቲካን ያለው ግንኙነት ክፍለ ዘመናትን ያስቆጠረ መሆኑን ያወሳው መግለጫ፤ አያታቸው ግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ በወርኅ ኖቬምበር 1970 ከፖፕ ፖል ስድስተኛ ጋር እንደተገናኙ ሁሉ የልዑል ኤርሚያስንም በ2021 ከፖፕ ፍራንሲስ ጋር መገናኘት አመልክቷል።
የታሪካዊ ግንኙነቱን መታደስ በማስመልከትም ከፖፕ ፍራንሲስ ጋር በተገኛኙበት ወቅት የኢትዮጵያውያን ጳጳሳት ኮሌጅን በመጎብኘታቸው "ክብር ተሰምቶኛል" ያሉ ሲሆን፤ "የፖፕ ፍራንሲስን ካለፉት ትውስታዎቻችን ይልቅ የወደፊት የጋራ ዕድሎቻችን ላይ እናተኩር" ዕሳቤ በውል የሚረዱ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
ልዑል ኤርሚያስ፤ የፖፕ ፍራንሲስን የአፍሪካ ቀንድ የሰላምና ዕርቅ ፍለጋ ግላዊ ሚና እንደሚረዱና ለደቡብ ሱዳን ሰላምና መረጋጋት ልባዊ ፀሎት ማድረግ አንስተው “በ2019 ብፁዕነታቸው ተንበርክከው የደቡብ ሱዳን ፕሬዚደንት ሳልቫ ኪር እና ምክትል ፕሬዚደንት ሪክ ማቻርን እግሮች የሳሙበትን ወቅት ከቶውንም አንዘጋም፤ የ2021 ግንኙነታችንን ተከትሎም ለኢትዮያ እንደፀለዩ እናውቃለን" ብለዋል።
በማከልም፤ "የኢትዮጵያ መንፈሳዊና ዓለማዊ መሪዎች የፖፕ ፍራንሲስን አርአያ ተከትለው ለሀገራችን ሰላም እንዲፀልዩና እንዲሠሩ" ሲሉ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።