ጠቅላይ ሚኒስትር አንቶኒ አልባኒዚ "ማራቶን ለነባር ዜጎች፤ ለእኛ አጭር ርቅት" ብለው የጠሩት የአውስትራሊያ ነባር ዜጎች ድምፅ ለፓርላማ ሕዝበ ውሳኔ ቅዳሜ ኦክቶበር 14 / ጥቅምት 3 እንድሚካሔድ አስታወቁ።
አቶ አልባኒዚ በስድስት ሳምንታት ውስጥ እንዲካሔድ ቀን የቆረጡለትን ሕዝበ ውሳኔ ይፋ ያደርጉት ዛሬ ረቡዕ ነሐሴ 24 ከአደላይድ ከተማ ደቡብ አውስትራሊያ ነው።

Anthony Albanese announced 14 October as the date when Australia's first referendum in a generation will be held. Credit: AAP / Mark Brake
የድምፅ ለፓርላማ አማካሪ አካሉ ምክረ ሃሳቦችን አቅራቢ እንጂ ውሳኔ ሰጪ ወይም ድምፅን በድምፅ የመሻር መብት ያለው አይደለም።
የድምፅ ለፓርላማ ደጋፊዎችና ተቃዋሚዎች የይሁንና አይሁን አተያይ ምንድን ናቸው?
የይሁን ካምፕ አተያዮች - ድምፅ ለፓርላማ
- የአውስትራሊያ ነባር ዜጎችን በማድመጥ ስለ እነሱ ፖሊሲዎች ሲቀረፁ ውጤት አስገኚ እንዲሆኑ ያግዛል
- ወደ ፊት ስልጣን ላይ የሚወጡ መንግሥታት እንዳይከሉት ሕገ መንግሥታዊ ጥበቃ ይኖረዋል
- ነባር ዜጎች በኡሉሩ መግለጫ ከልብ አማካይነት ምን እንደሚሹ ያቀርቡት ጥያቄ ነው
የአይሁን ካምፕ አተያዮች - ድምፅ ለፓርላማ
- አውስትራሊያውያንን በዘር ይከፋፍላል፤ ዘርን ሕገ መንግሥቱ ላይ ያክላል፣ የተለያየ የዜግነት መደቦችን ይፈጥራል
- ሕጋዊ ተጋላጭነት ስላለው የሕግ ተግዳሮትን ይፈጥራል
- በአውስትራሊያ ነባር ዜጎችና በተቀሩት አውስትራሊያን መካከል ያለውን ልዩነት አያጠብም፤ ዕርቅንም አያሰፍንም የሚሉ ናቸው።
ተመድ
የተባበሩት መንግሥታት ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ትናንት ነሐሴ 23 ባወጣው መግለጫ በአማራ ክልል በፌዴራል መንግሥቱና በአካባቢው ፋኖ ሚሊሺያ መካከል ተቀስቅሰው ባሉት ወታደራዊ ግጭቶች ሳቢያ የደረሱ የሕይወት ጥፋቶች እንዳሳሰቡት አመለክቷል።
የኮሚሽኑ ጽሕፈት ቤት ከሐምሌ 28 አንስቶ የተጣለውን አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተከትሎ ሁኔታዎች ተባብሰው የከፉ መሆኑንና 183 ያህል ሰዎች ሕይወታቸውን ያጡ መሆኑን አስታውቋል።
መግለጫው አክሎም፤ ከአንድ ሺህ በላይ ሰዎች በመላው ኢትዮጵያ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሕግ ተመርኩዞ ዘብጥያ መውረዳቸውንና በርካታ የአማራ ዝርያ ያላቸው ወጣቶች በፋኖ ደጋፊነት ተጠርጥረው ለእሥር መዳረጋቸውን የሚያመልክቱ ሪፖርቶች የደረሱት መሆኑን ገልጧል።
እርምጃዎቹን አስመልክቶም ባለ ስልጣናት ጅምላ እሥራትን እንዲገቱ፣ አልግባብ የታሠሩ እንዲለቀቁ፣ የተመድ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በሁሉም የዕገታ ሥፍራዎች መደበኛና ያልተገደበ ተደራሽነት እንዲኖራቸው እንዲደረግ ጥሪ አቅርቧል።
የተመድ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን አያይዞም፤ በፌዴራል ኃይሎች ጫና የፋኖ ሚሊሺያዎች ወደ ገጠራማ ሥፍራዎች ማምራት ጋር ተከትሎ ሁሉም ወገኖች ከግድያዎችና ሌሎች የአመፅ ድርጊቶች እንዲቆተቡ አሳስቦ፤ ቅሬታዎች በንግግርና ፖለቲካዊ ሂደቶች እንዲፈቱም አመላክቷል።
አክሎም፤ በአወዛጋቢው ምዕራባዊ ትግራይ 250 የትግራይ ዝርያ ያላቸው ግለሰቦች ታጣቂ የወልቃይት ወጣቶችን ጨምሮ፤ በአማራ ፖሊስና የአካባቢ ባለስልጣናት ለእገታ ተዳርገው እንደነበረና ከዚያም በመከላከያ ኃይሉ ስር እንደገቡ ታጋቾቹ ወደ ምዕራብ ትግራይ እንዲመለሱ ወይም በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ስር ወዳለው አካባቢ እንዲሆዱ አማራጭ የተሰጣቸው መሆኑን አንስቷል።
እንዲሁም፤ በኦሮሚያ ቀጥለው እንዳሉ የሚመለከቱት የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችም አሳስበውኛል ብሏል።
መግለጫው በማጠቃለያው፤ ሁሉም በተለያዩ ክልሎች የሚደርሱ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች በፍጥነት ገለተኛና ውጤታማ ምርመራ እንዲካሔድባቸውና ተጠያቂዎቹም ኃላፊነቱን እንዲወስዱ እንዲደረግ አሳስቧል።