ዛሬ ኦገስት 31 / ነሐሴ 25 የአውስትራሊያ ብሔራዊ ካቢኔ ባካሔደው ስብሰባ የኮቪድ - 19 ወረርሽኝ ወሸባ ገብቶ የመቆያ ጊዜ ከሰባት ቀናት ወደ አምስት ቀናት ዝቅ እንዲል ወስኗል።
ቀደም ሲል በአገር ውስጥ በረራ ወቅት የፊት ጭምብል ማጥለቅ ግዴታ ተነስቷል።
የወሸባ ቆይታው ጊዜ ከሰባት ወደ አምስት ቀናት ዝቅ ማለት አውስትራሊያን ከዩናይትድ ስቴትስና ካናዳ የወሸባ ጊዜ ገደቦች ጋር ተመሳሳይ የጤና መርህ ላይ ያካትታታል።
አዲሱ የወሸባ ቆይታ ጊዜና በአገር ውስጥ በረራ ወቅት የፊት ጭምብል ያለማጥለቁ ድንጋጌ ግብር ላይ የሚውለው ከሴፕቴምበር 9 / ጳጉሜን 4 ጀምሮ ነው።
ምንም እንኳ የድንጋጌ ለውጥ ቢደረግም ሰዎች ኃላፊነት በተመላው መንገድ ጥንቃቄዎችን ከማድረግ ወደ ኋላ እንዳይሉና የሰባት ቀናት የወሸባ ቆይታው አሁንም በአረጋውያን ክብካቤ፣ የግብረ አካል ጉዳተኞች ክብካቤና የቤት ውስጥ ክብካቤ ሠራተኞች ላይ የፀና እንደሚሆን ጠቅላይ ሚኒስትር አንቶኒ አልባኒዚ ገልጠዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም፤ የወርረሽኝ የቤት ውስጥ ቆይታ ክፍያን አስመልክቶ ለመምከርና ከውሳኔ ላይ ለመድረስ ብሔራዊ ካቢኔው ከሁለት ሳምንታት በኋላ ዳግም እንደሚገናኝ አስታውቀዋል።