የኮሮናቫይረስ መስፋፋት የማዝገም ምልክት እያሳየ አይደለም።
አውስትራሊያ ውስጥ የመጀመሪያው የኮረናቫይረስ ከተከሰተ ስድስት ወራት ያህል አስቆጥሯል።
በቫይረሱ በፅኑ የታመሙትን ለመታደግም ለአንድ አዲስ ማከሚያ ይሁንታ ተቸሯል።
በጤና ባለ ሥልጣናት ፈቃድ የተቸረው ሬምደዛቪር እንክብል ከኮሮናቫይረስ ፈጥኖ ለማገገም የሚያግዝ መሆኑ ታምኖበታል።
የአውስትራሊያ ምክትል የጤና ኃላፊ ዶ/ር ኒክ ኮትስዎርዝ ሬምደዛቪር ተከስቶ ላለው የጤና ቀውስ መድኅን ብሎም በእጅጉ እየተጠበቀ ያለው ክትባት እንዳልሆነ አስታውቀዋል።
አያይዘውም፤
"ሬምደዛቪር በኮሮናቫይረስ ሳቢያ ሳምባቸው ለጉዳት በተዳረጉ የሆስፒታል ሕሙማን ላይ የተጠና ነው። ዋናው ልብ ሊባል የሚገባው ጉዳይ እኒህ ማከሚያዎች አንዳቸውም እንከን የለሽ ፈጥኖ ደራሽ አለመሆናቸውን ነው። በተካሄዱ ዓለም አቀፍ ሙከራዎች ሬምደዛቪር ከመጠነኛ እስከ ፅኑዕ የኮሮናቫይረስ ሕሙማን ላይ ማለፊያ ውጤት ያሳየ ቢሆንም ሙሉ በሙሉ የፈዋሽነት ውጤትን አላስመዘገበም" ብለዋል።
የሬምደዛቪር አምራች የሆነው ጊሊያድ ኩባንያ የሕክምና ዳይሬክተር ዶ/ር ፖል ስሌድ - በሬምደዛቪር 30 ፐርሰንት ሕሙማን ፈጥነው ማገገም መቻላቸውን ጥናቶቻቸው እንደሚያመለክቱ ገልጠዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም፤ የተወሰኑ የጤና ባለሙያዎች ዩናይትድ ስቴትስ አብዛኛውን የሬምደዛቪር ክምችቶችን ለራሷ በማድረጓ ለአውሮፓና ለተቀረው ዓለም የሚተርፈው አነስተኛ የመሆኑ ጉዳይ ሥጋት ያሳደረባቸው መሆኑን እየገለጡ ነው።
አምራቹ ኩባንያ ጊሊያድ በበኩሉ አውስትራሊያን ጨምሮ በመላው ዓለም 1.5 ሚሊየን ሬምደዛቪር መለገሱን አስታውቋል። በወርኃ ሴፕተምበርም በርካታ ክምችት እንደሚኖር ተነግሯል።
አውስራሊያ ውስጥ በኮሮናቫይረስ ከተያዙት 9,553 ሰዎች ውስጥ 7,724 ያገገሙ ሲሆን 107ቱ ሕይወታቸውን አጥተዋል።
ቪክቶሪያ ውስጥ 1,249 በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ሲኖሩ፤ 23ቱ ሕይወታቸው አልፏል።
በቋንቋዎ ስለ ኮሮናቫይረስ ወቅታዊ መረጃዎችን ካሹ sbs.com.au/coronavirus ድረ-ገጽን ይጎብኙ።