አካላዊ ርቀቶቻቸውን ጠብቀው ምሥጋናቸውን ለነርሶች ካቀረቡቱ ውስጥ አያሌ የአረጋውያን መጦሪያ ቤቶች ተጠዋሪዎች ይገኙበታል።
'ያለመታከት በየዕለቱ ላደረጋችሁልን ልባዊ ክብካቤ ልባዊ ምስጋናችንን እነሆን' ብለዋል።
ከዩጎዝላቪያ በ1992 መጥተው ለነርስ ዳይሬክተርነት የበቁት ኢቫ ቤልላይ በተለይም በአረጋውያን መጦሪያ ላሉ ነርሶች ከኮቪድ - 19 ጋር ተፋልሞ እያካሄዱ የአረጋውያኑን ሕይወት የመታደጉ ተግባር እጅጉን ፈታኝ እንደነበር ተናግረዋል።
የአውስትራሊያ ዋና የነርስና አዋላጅ መኮንን - ኤሊሰን ማክሚላን አውስትራሊያውያን ማኅበራዊ ርቀታቸውን በመጠበቅ ለነርሶች ምሥጋናቸውን እንዳቀረቡት ሁሉ፤ 'በዚሁ በመቀጠል ደህንነታችንን እንዲጠብቁልን በመላው የአውስትራሊያ የጤና ሠራተኞች ስም መልዕክቴን ማስተላለፍ እሻለሁ' ሲሉ አደራ ብለዋል።
በየዓመቱ ሜይ 12 የዘመናዊ ነርስ መሥራቿን ፍሎረንስ ናይቲንጌልን ዕለተ ልደት በመዘከር የሚከበረው ዓለም አቀፉ ዝክረ በዓል ዛሬ 200ኛ ዓመቱን አስቆጥሯል።
የቀድሞዋ ነርስና የአሁኗ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ዶ/ር ሄለን ሃይነስ - ፍሎረንስ ናይቲንጌል ለመላው የጤና ሠራተኞች የማለፊያ ተግባር አብነት ናት ሲሉ በውዳሴ ቃላቸው የዝክረ መታሰቢያውን ፋይዳ አመላክተዋል።

Florence Nightingale Source: Courtesy of PD
ዶ/ር ሃይነስ እንደ ፍሎረንስ ናይቲንጌል ሁሉ በየአረጋውያን መጦሪያዎች፣ ሆስፒታሎችና የማገገሚያ ማዕከላት ሁሉ ግልጋሎታቸውን በአይታክቴነት የሚያበረክቱት 390,000 አውስትራሊያውያን ነርሶች ፍሎረንስ ናይቲንጌል እንደሆኑ የሙያ ተወራራሽነትና የመልካም ግብር ተምሳሌነታቸውን አሰናስለው ነቅሰዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ስኮት ሞሪሰንም ምሥጋናቸውን ሲገልጡ፤
"እናንት ለሕሙማን ደራሽ፤ ለእኛ አለሁ ባዮች ናችሁ። በዚህ ወቅት፤ የአገራችንን ሕይወት ታድጋችሁ እዚህ እንድንደርስ ያበቃችሁን ናችሁና - እናመሰግናለን" ብለዋል።
የዓለም ጤና ድርጅትም በበኩሉ 2020ን 'ዓለም አቀፍ የነርስና አዋላጅ' ዓመት ሲል ሰይሟል።
የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን አስመልክቶ መረጃ ካሹ sbs.com.au/coronavirus ድረ - ገፃችንን ይጎብኙ።