ውይይቱ የተካሔደው "ኢትዮጵያና ኮቪድ - 19 መረጃ ለትግበራ" በሚል የመወያያ አጀንዳ ነው። በውይይቱ ላይ ተጋባዥ እንግዶችን፣ የጥናትና ምርምር ግኝት አቅራቢዎችን አክሎ ከ357 በላይ ተሳታፊዎች ታድመዋል።
መድረኩን በእንኳን ደህና መጣችሁና ተጋባዥ እንግዶችን በማስተዋወቅ የመሩት በካንብራ ዩኒቨርሲቲ የሉላዊ ጤናና ምጣኔ ኃብት መምህርና ተመራማሪ የሆኑት ተባባሪ ፕሮፌሰር ዮሐንስ ክንፉ ናቸው።
ቀዳሚ ተናጋሪ የነበሩት በአውስትራሊያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ባለሙሉ ሥልጣን ሚኒስትርና ተጠባባቂ የሚሲዮን መሪ አቶ በሪሁን ደጉ፤ በአውስትራሊያ ነዋሪ ከሆኑ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ-ኢትዮጵያውያን ለኮቪድ - 19 መከላከያና መቆጣጠሪያ ተግባራት እንዲውል የተሰበሰበ $102,463 የአውስትራሊያ ዶላርስ ወደ ብሔራዊ አካውንት ገቢ መሆኑንና የሁለተኛ ዙር ገቢ ማሰባሰብ እየተካሔደ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
አክለውም፤ ኮሮናቫይረስን በገንዘብ ብቻ መከላከል ስለማይቻል በዕውቀትም ሊደገፍ እንደሚገባና በአውስትራሊያ የኢትዮጵያውያን ተመራማሪዎች በይነ መረብ ሚና ኢትዮጵያ ኮቪድ - 19ኝን ለመከላከል የምታደርገውን ጥረት ያጎለብታል፤ የጤና፣ ፖለቲካዊ፣ ምጣኔ ኃብታዊና ማኅበራዊ ችግሮችን ለመከላከል አስተዋፅዖ ይኖረዋል ብለው እንደሚያምኑ ገልጠዋል።
በቀጣይነትም፤ የኢትዮጵያ ሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ደኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሡ በበኩላቸው ለ "ኢትዮጵያና ኮቪድ - 19 መረጃ ለትግበራ" የውይይት መድረክ አዘጋጆችና በአውስትራሊያ የኢትዮጵያውያን ተመራማሪዎች በይነ መረብ አባላት ርቀት ሳይገድባቸው የሚያደርጓቸው አስተዋፅዖዎች ለኢትዮጵያ እጅግ ከፍተኛ እንደሚሆኑ በማመላከት ምሥጋናቸውን አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር፤ ለአውስትራሊያ የኢትዮጵያውያን ተመራማሪዎች በይነ መረብ አባላት ተምሳሌያዊ ሥራዎች ከፍተኛ ዕውቅናን እንደሚቸር፣ ከኢትዮጵያ ከፍተኛ የጥናትና ምርምር ተቋማት ጋር ይበልጥ ተቀናጅተው እንዲሠሩ አበረታተዋል። ኢትዮጵያም የጥናትና ምርምር ውጤታቸውን ለጥናትና የፖሊሲ ግብዓት እንደምትጠቀምበትም ጠቁመዋል።
በማያያዝም፤ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤታቸው የተለያዩ ዘርፈ ብዙ የምላሽ ሥራዎችን ግድ በሚለው የኮቪድ - 19 ተግባራት የድርሻውን በመውሰድ በትብብርና በቅንጅት ከተለያዩ የትምህርትና የጤና መካነ ጥናቶች ጋር በመሥራት ላይ እንደሚገኝ ገልጠዋል።
ከሚኒስትር ደኤታው ቀጥለው በአውስትራሊያ የኢትዮጵያውያን ተመራማሪዎች በይነ መረብ አስተባባሪና የውይይት መድረኩ መሪ ተባባሪ ፕሮፌሰር ዮሐንስ ክንፉ በበኩላቸው የተመራማሪዎቹ በይነ መረብ አባላት "ዕውቀታችንንና ልምዳችንን ብናሰባስብ አገራችንን ልንረዳ እንችላለን" በሚል መሰባሰብ እንደጀመሩና ከተከታታይ ስብሰባዎች በኋላም ይህንን መድረክ ለማዘጋጀት እንደበቁ፤ ለፖሊሲና ለትግበራ ግብዓት የሚሆኑ አስተዋፅዖዎችን ከማበርከት ደረጃ ላይ እንደደረሱ ተናግረዋል።
የውይይት መድረኩ በተያዘለት ፕሮግራም መሠረት የተመራማሪዎቹ በይነ መረብ አባላት በአራት የጥናት ዘርፎች ግኝቶቻቸውንና ምክረ ሃሳቦች በየተራ አቅርበዋል። ከተሳታፊዎችም የተለያዩ ጥያቄዎች ቀርበው ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል።
በውይይት መድረኩ ላይ የማጠቃለያ ንግግር ያደረጉት ፕሮፌሰር የማነ ብርሃን - የኅብረተሰብ ጤናና ተዛማች በሽታዎች ተመራማሪና የአዲስ ኮንቲኔንታል የኅብረተሰብ ጤና መካነ ጥናት ዳይሬክተር ከኢትዮጵያ ሲሆኑ፤ ተመራማሪዎቹ ከአገራቸው በአካል ቢርቁም በአገራቸው ጉዳይ ላይ ከመሳተፍ እንዳልራቁ ጠቅሰው አመስግነዋል።
ፕሮፌሰር የማነ በማከልም፤ ሳይንሳዊ ትንታኔዎች ለኅብረተሰቡ በሚገባ ቋንቋ በጣም የተመጠኑና የተመዘኑ ሥራዎችን ማቅረብ ይበልጥ ውጤታማ እንደሚሆን፣ ከቁጥር በላይ ጥልቀት ያላቸውን ትንታኔዎች ማቅረብ ከአዘናጊ በራስ መተማመን እንደሚገታ፣ በርካታ ተለዋዋጭ ሁኔታዎች ስለሚኖሩ በተለይም የረጅም ጊዜ ትንበያዎችን አዋኪ እንደሚያደርግና ምክረ ሃሳቦችን በገፍ ከማቅረብ ይልቅ በጣም ነጥረው የተመረጡ ጥቂት ምክረ ሃሳቦችን ለፖሊሲ ቀራጮች ማቅረቡ የተሻለ እንደሚሆን አሳስበዋል።
አያይዘውም፤ በውጪ እርዳታ እየተደጎመ ያለውን የኢትዮጵያ የጤና ሥርዓት ኮቪድ - 19ኝን ለመከላከል በሚያስችል ፍጥነት መለወጥ የሚቻል ካልሆነ ምን ሊከተል እንደሚችል በመጠይቃዊ ድምፀት አንስተዋል።
ሲልም "ኮቪድ - 19ኝን ለመከላከል የምንችለው ሕዝቡን በማስተማር ነው ወይስ የጤና ሥርዓቱን በማሻሻል? ያንንስ ለማድረግ ኮቪድ - 19 ጊዜ ይሰጠናል ወይ?" በማለት ወረርሽኙ የተመራማሪዎችን ሥራዎች ውስብስብና ድርብርብ እንደሚያደርገው ተናግረዋል።
ሲያጠቃልሉም "የኮቪድ - 19 ወረርሽኝ ዘላቂነት ያለው ግንኙነት መመስረቻና የማሰቢያ ጊዜ ነው" ብለዋል።