አንኳሮች
- የመድብለ ባሕል ክለሳ ማዕቀፍ ከ29 ምክረ ሃሳቦቹ ጋር ይፋ ሆኗል
- በፍጥነት እንዲከወኑ ካመላከታቸው 10 ምክረ ሃሳቦች ውስጥ የዜግነት ፈተና ሥርዓተ ደንቦች አንዱ ነው
- የአውስትራሊያ ስደተኞች ምክር ቤት የዜግነት ፈተና ምክረ ሃሳብን በመልካም ጎንነት ተቀብሎታል
ባለ 200 ገጹ በሁሉም ደረጃዎች ያሉ የመንግሥት አካላት "የተሰነጣጠቀ" ፖሊሲ በሚል የሚገለጠውን እንዲያሻሽሉና ወቅታዊ እንዲያደርጉ ጥሪ በሚያቀርቡ ተሟጋች ድምፆች ዘንድ በመልካምነት ታይቷል።
ለመጠናቀቅ ከሁለት ዓመታት በላይ የፈጀው ክለሳ፤ የፌዴራል መንግሥቱ 10 በአፋጣኝ ሊከወኑ ይገባቸዋል ያላቸውን ጨምሮ 29 ምክረ ሃሳቦችን ግብር ላይ እንዲያውል ጥሪ አቅርቧል።
ለመጠናቀቅ የበቃውም በመላው አውስትራሊያ ከ1,400 በላይ ግለሰቦችንና 750 ድርጅቶችን በማነጋገር ነው።
ዶ/ር ቡለንት ሃስ ዲላል፤ የአውስትራሊያ መድብለ ባሕላዊ ፋውንዴሽንና የክለሳ ፓናል ሊቀመንበር "አውስትራሊያ ልዩነታችንን የምናከብርበት ሁሉን አካታች የሆነ የመፃኢ ዕድል ታላቅ መልካም ዕድልን ለመቅረፅ እንዲሁም፤ ከጋራ ዕሴቶቻችን ተነቅሰው ብሔራዊ ማንነትን የምንገነባበት ልዩ የሆነ መስቀለኛ መንገድ ላይ ቆማለች” ብለዋል።
የክለሳው አንዱ ቁልፍ ምክረ ሃሳብ ከእንግሊዝኛ በተጨማሪ ሌሎች ቋንቋዎችን አካታች የሆነ የዜግነት ፈተና ሥርዓተ ደንብ ነው።

Dr Bulent Hass Dellal AO was the chair of the review launched in 2023. Credit: SBS
አያይዘውም "ከፈተናው ዘርፍ ከሚነጠለው አንስተኛ ሙከራ ሌላ፤ የተቀረው ፈተናውን በእንግሊዝኛ መከወንን ግድ ባይ ነው፤ ያም ለተወሰኑ ቡድናት በእጅጉ አዋኪ ነው፤ በተለይም በአናሳና ስደተኞች ዘርፎች እንዲሁም የተወሰኑ የቤተሰብ ቪዛ ባለቤት ለሆኑቱ" ይላሉ።
ሌላው ምክረ ሃሳብ ራሱን የቻለ፤ የመድብለ ባሕል ጉዳዮች ኮሚሽንና ኮሚሽነር እንዲሁም በቋሚ ሚኒስትር የሚመራ የመድብለ ባሕል ጉዳዮች፣ ኢሚግሬሽንና ዜግነት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት እንዲቆም ነው።
አንድ የሀገር ውስጥ ጉዳዮች ቃል አቀባይ ሲናገሩ መንግሥት "ከክለሳው ቁልፍ ክፍሎችን ነቅሶ በማዋደድ ... በመላው የጋራ ብልፅግናው ኤጄንሲዎችና እንቅስቃሴዎች አሁንና ለመጪዎቹም ጊዜያት ግብር ላይ እንዲውሉ ያደርጋል" ብለዋል።
የዜግነት ፈተና አዲስ ዜጎች "የእንግሊዝኛና አውስትራሊያን የመረዳት መሠረታዊ ዕውቀት እንዲኖራቸው" ውሁድ ሚና እንደሚኖረው ቃል አቀባዩ ተናግረዋል።
አክለውም፤ መሠረታዊ የእንግሊኛ ቋንቋ ዕውቀት ከማኅበረሰቡ ጋር ለመዛነቅና ተሳትፎም ለማድረግ አጋዥ ስለመሆኑ ሲያመላክቱ፤
“እንግሊዝኛ እንደ ብሔራዊ ቋንቋነቱ ማኅበረሰብን ወደ ኅብረት በማምጣት የሚያንፀባርቀውና ለአዲስ ዜነት የሚበቁትን በአውስትራሊያ ማኅበረሰብ ውስጥ ሙሉ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ከማድረግ አኳያ የሚጫወተው ሚና ስላለ የዜግነት ፈተና በእንግሊዝኛ ብቻ ሆኖ የሚሰጥ ሆኖ ይቀጥላል"
“የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የፈተናውን ሂደት በቅርበት መከታተሉን ይቀጥላል፤ ማናቸውም ማስተካከያና አስፈላጊ ድጋፍ የሚያሻ ከሆነ ከግምት ውስጥ ያስገባል” ብለዋል።
የአውስትራሊያ ስደተኞች ምክር ቤት ግና በበኩሉ የክለሳው ምክረ ሃሳብ የሆነውን የዜግነት ፈተና በመልካም ጎኑ ስለ መቀበሉ የምክር ቤቱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፖል ፓወር ሲገልጡ፤
“በበርካታ ጉዳዮች፤ ቤተሰቦች ፈተናውን ባለፉትና ማለፍ ባልቻሉት መካከል ክፍፍል ሲፈጠር አይተናል"
“እኒህ ዝቅተኛ ደረጃ የእንግሊዝኛ ቋን ችሎታ ያላቸውን በመቅጣቱ ፈንታ፤ ሁሉም ግለሰቦች ዜጎች ሆነው ለአውስትራሊያ ሕብረተሰብ አስተዋፅዖዎችን እንዲያበረክቱ በማበረታታት ልንታደጋቸው ይገባል። መንግሥት የፓናሉን ሁሉን አቃፊ የዜግነት ፈተና ምክረ ሃሳብ ተቀብሎ ግብር ላይ እንዲያውለው እናበረታታታለን” ብለዋል።
ምንም እንኳ መንግሥት በአንድ በኩል አንዳችም ለይቶ የተቀበላቸውን ምክረ ሃሳቦች እስካሁን አለማስታወቁን የሥነ ማኅበራዊ ፕሮፌሰር አንድሩ ጃኩቦዊክዝ ሲያመላክቱ፤
"በርካታዎቹ የክለሳው ምክረ ሃሳቦች የመንግሥት አዲስ ነገሮችን ከመሥራት ጋር የተገናኙ ናቸው፤ የመድብለ ባሕል ኮሚሽን እስኪቋቋም ድረስም አንዳችም ግብረ ማዕቀፍ የለም፤ ከተቋቋመ ግና እኒህ ነገሮች ግብር ላይ የሚውሉ ስለመሆናቸው አረጋጋጭ ሊሆን ይገባል" ይላሉ።
በተጨማሪም ከምክረ ሃሳቦቹ ጋር ተሰናስሎ የአውስትራሊያን ባሕላዊ ዝንቅነት ለማክበር የሚያስችል ብሔራዊ ዕቅድ ስንዱ እንዲሆን በአማላካችነት ተሰነዷል።