'ለጉዞ ዝግጁ ይሁኑ' ወቅታዊውን የአውስትራሊያ መንግሥት የጉዞ ምክር እነሆ

የኮቪድ-19 እና የዝንጀሮ ፈንጣጣ ሉላዊ ተዛማችነት እየሰፋ መሔድ የዓለም አቀፍ ጉዞ ሁነትን ይበልጡን ውስብስብ ማድረጉን የውጭ ጉዳዮች እና ንግድ ዲፓርትመንት ያስገነዝባል።

AUSTRALIA-SYDNEY-COVID-19-BORDER REOPENING

Passengers at Sydney Airport in Australia. (file) Credit: Xinhua News Agency/Xinhua News Agency via Getty Ima

አንኳሮች
  • • ክትባት ያልተከተቡ አውስትራሊያውያን ለጉዞ 'በእጅጉ አይበረታቱም' የውጭ ጉዳዮችና ንግድ ዲፓርትመንት
  • • ምክትል ዋና የሕክምና መኮንን ማይክል ኪድ አውስትራሊያውያን ' የድንገተኛ አደጋ ጊዜ ዕቅድ' እንዲኖራቸው ያበረታታሉ
  • • የአውስትራሊያ የክትባት ቴክኒካዊ አማካሪ ቡድን አንድ የተወሰነ ቡድን ከጉዞ 4-6 ሳምንት በፊት ሁለት ዙር የዝንጀሮ ፈንጣጣ ክትባቶችን እንዲከተቡ ይመክራል
የሜልበርን ነዋሪዋ ኒሻ አንቲል በመስከረም ውስጥ ወደ ሕንድ ከቤተሰቧ ጋር ለመሔድ ዕቅድ ይዛለች።

ይሁንና በኮቪድ - 19 እና የዝንጀሮ ፈንጣጣ ወረርሽኝ መካከል ጉዞዋ ምናልባትም እንዳሰበችው ላይሳካ ይችል ይሆናል የሚል ፍርሃት አድሮባታል።

የፍራቻዋ መነሻ ከሁለት ዓመታት በፊት የኮቪድ - 19 ወረርሽኝ ንሮ በነበረበት ወቅት የአውስትራሊያ የሕንድን ጉዞ ከማገድ ውሳኔ ላይ መድረስን አስታውሶ ከማሰብ ነው። በወቅቱ ባለቤቷ በድንበር መዘጋት ሳቢያ ሕንድ ላይ ተገትቶ ቀርቶ ነበር።

የሁለት ልጆች እናት የሆነችው አንቲል "በጣሙን አሳሳቢው በጉዞ እገዳዎች ሳቢያ ወይም በሕንድና አውስትራሊያ በረራዎች መካከል ያሉ የትራንዚት ጉዳዮች ናቸው" ብላለች።

የወቅቱ ወደ ሕንድ ተጓዥ ለሆኑ አውስትራሊያውያን ያለው የጉዞ ምክር "ከፍተኛ ደረጃ ጥንቃቄ አድርጉ" የሚል ነው። የኮቪድ-19 ገደቦችን ይዞና ምናልባትም በአጭር ጊዜ ማስጠንቀቂያ ሊጣሉ የሚችሉ የአካባቢ የእንቅስቃሴ ገደቦችን፣ እንዲሁም የሰዓት ዕላፊዎችን አካትቶ።
Nisha.jpeg
Nisha Antil and her family Credit: Nisha Antil
የውጭ ጉዳዮችና ንግድ ዲፓርትመንት ቃል አቀባይ ለSBS እንደገለጡት ጉዞ ሁሌም ከተጋላጭነት ጋር የተያያዘ መሆኑን ሲያመላክቱ፤

"በአሁኑ ወቅት የዓለም አቀፍ ጉዞ ሁኔታ ይበልጡን የተወሳሰበ ነው። አውስትራሊያውያን ለጉዞ ዝግጁ ሆነው ግና ስለ ጉዟቸው ሙሉ መረጃዎች ያላቸው እንዲሆኑ እናበረታታለን" ብለዋል።

እናም፣ የጉዞ ዝግጁነት ማለት ምን ማለት ነው?

1. ስለ መዳረሻዎ ጥናት ያካሂዱ

አውስትራሊያውያን በ178 መዳረሻዎች ውስጥ ሊገጥማቸው ስለሚችሉ መሥፈረቶችና ተጋላጭነቶች ለመረዳት የሚያስችላቸውንና ወቅታዊ የጉዞ ምክር የሚቸረውን የመንግሥት ኧፕ መጠቀም ይችላሉ።

በፖርታሉ ላይ ከቆንሱላ ጋር ተያያዥ የሆኑ ተደራሽ መረጃዎች ይገኛሉ።

ተመላሽ መንገደኞች ወደ አውስትራሊያ ከመምጣታቸው በፊት የድንበር ገደቦችንና የአካባቢ መሥፈርቶችን አስመልክተው ሊያጣሩ ይገባል።

የ Smartraveller ዝርዝር ጭብጦች በእንግሊዝኛ፣ በታይ፣ በኢንዶኔዥያ፣ አረብኛ፣ የቬይትናምና ቀላልና ማዳዊ በሆነ የቻይና ቋንቋዎች ተፅፈው ይገኛሉ።  

2. ወቅታዊ የክትባት መረጃን ያግኙ

ክትባት ያልተከተቡ የአውስትራሊያ ዜጎች፣ ቋሚ ነዋሪዎችና ዓለም አቀፍ ጎብኚዎች አውስትራሊያን በማናቸው ጊዜ ለቅቀው መሔድ ይችላሉ።

ይሁንና የተወሰኑ አገራት አሁንም ድረስ መንገደኞች ወደ አገራቸው ከመምጣታቸው በፊት የኮቪድ -19 ክትባት ምስክር ወረቀት እንዲኖራቸው ግድ ይላሉ።

የውጭ ጉዳዮችና ንግድ ቃል አቀባይ የኮቪድ -19 ክትባትን ያልተከተቡ አውስትራሊያውያን "ከጤና ተጋላጭነት አኳያ ወደ ባሕር ማዶ ከመሔድ እንዲቆጠቡ በብርቱ እናሳስባለን" ብለዋል።


3. የድንገተኛ አደጋ ጊዜ ዕቅድ ይኑርዎት

የአውስትራሊያ ምክትል ዋና የሕክምና መኮንን ማይክል ኪድ አውስትራሊያውያን ባሕር ማዶ ሳሉ ጤናቸው ቢታወክና ለመገለል ግድ ቢሰኙ "የድንገተኛ አደጋ ጊዜ ዕቅድ ሊኖራቸው ይገባል"

"ለሁሉም አውስትራሊያውያን የአካባቢውን የሕዝብ ጤና ትዕዛዛትና ማሳሰቢያዎችን መከተል በጣም ጠቃሚ ነው" በማለት አስገንዝበዋል።

ጤና ባይሰማዎትና የጉዞ ዕቅድዎ ቢስተጓጎል፤ በየዕለቱ የተለያዩ ሥፍራዎች ከመጓዝ ይልቅ ወደ ተወሰኑ ሥፍራዎች መጓዝ ይበልጡኑ አስተውሎት የተመላበት ይሆናል።

4. የጉዞ ኢንሹራንስ ይኑርዎ

መንገደኞች የጉዞ ጤና ኢንሹራንሳቸው የኮቪድ-19 እና ተያያዥ የሆኑ አሰናካይ ሁነቶችን ያካተተ መሆኑን ልብ ሊሉ ይገባል። .

ለአውስትራሊያውያን የጉዞ ኢንሹራንስ ግዢን አስመልክቶ መምሪያ ለመቸር ከ CHOICE ጋር ሽርክና ገብቷል።

የዝንጀሮ ፈንጣጣን አስመልክቶስ?

የዝንጀሮ ፈንጣጣ ተጠቂዎች ቁጥር መጨመር የዓለም ጤና ድርጅትን ጁላይ 23 በሉላዊ ወረርሽኝነት ለማወጅ ግድ አሰኝቷል።

ከጃኑዋሪ 1 አንስቶ 83 አገራት ከ23,000 በላይ ሰዎች መጠቃታቸውንና ስምንት ሰዎች ሕይወታቸውንን ማጣታቸው በላቦራቶሪ ተረጋግጧል። አውስትራሊያ በአብዛኛው ተመላሽ መንገደኞችን ያካተተ 58 የዝንጀሮ ፈንጣጣ ተጠቂዎችን አስመዝግባለች።

የአውስትራሊያ የጤናና አረጋውያን ክብካቤ ቃል አቀባይ አውስትራሊያውያን የዝንጀሮ ፈንጣጣ አለባቸው ወደ ተባሉ አገራት ሲጓዙ ወይም ከተባሉ አገራት ሲመለሱ የበሽታውን ምልክቶች ልብ ሊሉ እንደሚገባ ለSBS ገልጠዋል።

አያይዘውም፤ .

"ምናልባትም ለቫይረሱ ተጋላጭ ሆነው እንደነበር ካሰቡ የሕክምና እርዳታ እንዲጠይቁ ይበረታታሉ" ብለዋል።

ወደ ባሕር ማዶ ከመጓዝዎ በፊት የዝንጀሮ ፈንጣጣ ክትባት መከተብ ያሻዎታል?

የዓለም ጤና ድርጅት ዳታ እንደሚያሳየው 98 ፐርሰንት የዝንጀሮ ፈንጣጣ ተጠቂዎች ከወንዶች ጋር ወሲብ የሚፈፅሙ ወንዶች ሆነው ተገኝተዋል።

በአሁኑ ወቅት ያለው የሁለተኛው - ትውልድ ፈንጣጣ ክትባት ACAM-2000 የዝንጀሮ ፈንጣጣን ለመከላከል እምብዛም አመርቂ አይደለም። እንዲሁም ደካማ የሰውነት ተፈጥሯዊ መካላከያና HIV ላለባቸው ሰዎች እንዲሰጥም አይመከረም። .

አውስትራሊያ ውጤታማነቱ ይበልጡን ከፍ ያለውን ሶስተኛ ትውልድ ክትባት JYNNEOS አቅርቦት በአስተማማኝ መልኩ አዝዛ አግኝታለች። ተጋላጭ የሆኑ ቡድናት ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ ሊያገኙት ይችላሉ።

የአውስትራሊያ ክትባት ቴክኒካዊ አማካሪ ቡድን JYNNEOS በ28 ቀናት ልዩነት ከቆዳ ስር ሁለት ዙር ክትባት መስጠት እንደሚቻል ገልጧል።

አማካሪ ቡድኑ ከተጋላጭነት ምርመራ በኋላ የሰውነት የመከላከል አቅማቸው ደካማ ለሆነ፣ ለልጆች ወይም በእርግዝና ወቅትም ሊሰጥ እንደሚችል አስታውቋል።

አማካሪ ቡድኑ በአሁኑ ወቅት JYNNEOS ለሚከተሉት ሊሰጥ እንደሚችል ምክረ ሃሳቡን ለግሷል፤

1. ባለፉት 14 ቀናት ውስጥ በሕዝብ ጤና ባለስልጣናት በዝንጀሮ ፈንጣጣ ንኪኪ ከፍተኛ ተጋላጭ ተብለው የተፈረጁ

2. ግብረሶዶማዊ፣ የሁለት ፆታዎች (ከእንዶችና ከሴቶች) እና ሌሎች ከወንዶች ጋር ወሲብ ፈፃሚ ወንዶች

3. የወሲብ ሠራተኞች፣ በተለይም ደንበኞቻቸው በፈርጁ ከፍተኛ ተጋላጭ የሆኑ

4. ማናቸውም ከላይ በከፍተኛ ተጋላጭነት ተፈርጀው በሽታው በከፍተኛ ደረጃ ተዛምቶበት ወዳለ አገር ለመጓዝ ዕቅድ ይዘው ያሉ ከመጓዛቸው ከ 4-6 ሳምንታት በፊት እንዲከተቡ ይመከራል

5. የ ACAM2000 ፈንጣጣ ከትባት ከታቢዎች

SBS ማናቸውንም የኮቪድ-19 ወቅታዊ መረጃ ለአውስትራሊያ መድብለ ባሕልና መድብለቋንቋ ማኅበረሰባት ያለማሰለስ ያቀርባል። የ መረጃን በማግኘት ይዝለቁ።
.

Share
Published 24 August 2022 11:10pm
By Yumi Oba, Kassahun Seboqa Negewo
Source: SBS


Share this with family and friends