አንደ መግቢያ
ድንገቴው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መላው ዓለማችንን ተቆጣጥሯል። ሚሊዮኖች በበሽታው ተጠቅተው፣ መቶ ሺዎች ውድ ሕይወታችውን ተነጥቀው፣ በአስር ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች ቫይረሱ በኢኮኖሚው ላይ ባደረሰው ቀውስ ሳቢያ ለወራት በመኖሪያ ቤታቸው ተወሽበው አሉ። ወደፊት የሚሆነውን በርግጠኝነት ለመናገር ይቅርና አሁን ያለውን የቫይረሱን ጠባይ ገና በቅጡ መች ተረድተነው? ዛሬ ስለቫይረሱ የሚገኝው አዲስ መረጃ የትላንቱን መረጃ እየተቃረነ፤ ለጥንቃቄ የሚሰጠን ምክርም እንደ አየሩ ጸባይ እየተቀያየረ ነው።
ዶናልድ ራምዝፊልድ “ያወቅነው እውቀት አለ፤ አለመታወቁን የምናውቀው እውቀት አለ፤ ፈታኙ ግን አለመታወቁን የማናውቀው እውቀት ነው” [1] ያለው አባባል የዘመነ ኮሮና አንቆቅልሽን በመጠኑ ሊገልፀው ይችላል።
ኮቪድ19 እያገረሸ አብሮን ሊቆይ በመሆኑ የችግሩ ውስብስብነት አይቀሬ ነው። ክትባቱ ቢገኝ እንኳ ከሕዝብ ዘንድ ሊደርስ የሚችለው እጅግ ዘግይቶ ነው። ካለን የሆስፒታል፣ የህክምና ባለሙያ፣ የህክምና ቁሳቁስና መድሃኒት አቅርቦት አንጻር እንኳንስ ኢትዮጵያ በርካታ ያደጉ ሃገራትም ተፈትነው የወደቁበት ጉዳይ ነው። ዛሬ መንግሥት፣ የሃገር ውስጥ በጓድራጊዎችና ሕዝቡ እጅና ጓንት ሆነው እየተረባረቡ መሆናቸው ተስፋ ቢያጭርም የኮሮናን ዘርፈ-ብዙ ችግር ከህክምና አንፃር ብቻ መፍትሄ ልናበጅለት አንችልም።
ለምሳሌ ከሃገር ውስጥና ከሌሎች ያደጉ ሃገራት ከሚገኝ አርዳታ ጋር ተደማምሮ የሚገኘውን ውስን ሃብት በየቱ ሥፍራ ቀድመን ትኩረት ብናደርግ ከፍተኛ ውጤት (multiplier effect) እናመጣለን? አንደ ወሳኝ መፍትሄ የቀረበውን የማኅበራዊ ፈቀቅታን አንዴትስ ውጤታማ አናደርገዋለን? መፍትሄ የሚሹ ጥያቄዎች!
ትንቢተ ኮሮና?
በኢትዮጵያ ለኮሮና ወረርሺኝ የቀረቡ ትንበያዎችን በሁለት ልንከፍላቸው እንችላለን። አንደኛው ፍጹም የተጋነነ (ሟርት የመሰለ) “የራስጌ ግምት” ሲሆን በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በየዕለቱ እንደሚረግፉ የሚተነብይ ነው። የዚህ ምድብ አስቀድሞ በቻይና፣ በጣሊያን፣ እና በደቡብ ኮሪያ የተከሰተውን የኮሮና ሥርጭት ሥሌት ኮርጆ አንደወረደ ለኢትዮጵያ በመሸለም “አስቀድሜ ተናግሬ ነበረ” ብሎ ይጠባበቅ የነበረ ይመስላል።
የሁለተኛው ምድብ (አዘናጊ የመሰለ) ለኮሮና ወረርሺኝ የተቃለለ “የግርጌ ግምት” የሰጠ ነበር። ማስረጃውም ኢትዮጵያ የራሷ ባሕላዊ መድሃኒቶች ስላሏት፤ ፈጣሪ ሀገራችንን ከሌላው በበለጠ ስለሚጠብቃት፤ የዘመናችን ‘ነቢያት’ ኮሮና ኢትዮጵያን እንደማይደፍራትና ቢመጣም ድራሹ እንደሚጠፋ ስለተገለጸላቸው፤ ወዘተ። ሃገርኛው ኮሮና ያለው ግን በሁለቱ የተለጠጡ ግምቶች መሃል ነው።
ከሥፍራም ሥፍራ አለ?
ኮቪድ19 ከሰው ወደ ሰው በትንፋሽ የሚተላለፍ እንደመሆኑ የርስበርስ ቅርርብ ባህላችንና ትግበራችን የበሽታውን ሥርጭትና ቆይታ ይወስነዋል። በሰዎች መሃል ያለ የርቀት ዝንባሌ በተመለከተ ጥናቶች [2] ሁለት ባህሎችን ይቆጥራሉ። የቀረቤታ (ይጠጌ) እና የፈቀቅታ (አይጠጌ) ባሕሎች። ይጠጌ ባህል በተንሰራፋባቸው አካባቢዎች የኮሮና ሥርጭትን ለመዋጋት አዳጋች ሲሆን በአይጠጌው ባህል ግን የቀለለ ይሆናል። የደቡብ አውሮፓ፣ የደቡብ አሜሪካ፣ የአረቢያ ሕዝቦች ከይጠጌ ባህል ሲመደቡ በአመዛኙ በሞቃታማ የአየር ንብረት ክልል ይገኛሉ። ለምሳሌ ከአውሮፓ ጣልያንና ስፔይን ሲገኙበት፣ እኛ ደግሞ የድሬዳዋ፣ ናዝሬት፣ ሞጆ፣ ወዘተ ከተሞችን ማከል እንችላለን። እንዳለመታደል ሆኖ የይጠጌ ባህል አገራት ባመዛኙ የደኸዩ ናቸው። በሌላ በኩል በሰሜን አውሮፓ ያሉ ሃገራት ከአይጠጌ ባህል ሲመደቡ አየር ንብረታችው በጣም ቀዝቃዛ በኢኮኖሚያቸው ደግሞ ሃብታም የሚባሉ ናቸው።
እንደ ኢትዮጵያ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ሪፖርቶች ከሆነ የአዲሳባ ከተማ በኢትዮጵያ የኮቪድ19 እንቅጥቅጣፍ (epicentre) ናት። ምንም አንኳ በኢትዮጵያ የከተሜው መቶኛ ድርሻ ጥቂት ቢሆንም የወረርሽኙ መናኽሪያ በመሆኑ የከተሞችን የሥፍራ ባህሪ መመርመር ግድ ይላል። ወረርሺኙ በሁሉም ሥፍራ እኩል አይገንምና የሚብስባቸውም ሆነ የሚቀንስባቸው ቦታዎች ይኖራሉ። የቫይረሱ ፍጥነትም ሆነ ሥርጭት የሚወሰነው አንደ ቦታው (site) ጠባይ (ለምሳሌ የአየር ሙቀት፤ ርጥበት፣ ዝናብ፣ ንፋስ፣ ወዘተ) ብቻ ሳይሆን ቦታው ከአካባቢው ጋር ባለው ትስስር (situation) ጠባይ (መንገድ፣ የገበያ ቁርኝት የህክምና ጣቢያ አቅርቦት፣ ወዘተ) ላይ ተመርኩዞ ነው።
ሥፍራ ከሰው ልጅ መሰረታዊ ህይወት ጋር የተሳሰረ ነው፤ በተለይም ደግሞ ከጤና ጋር ያለው ጉድኝት ሲበዛ ቀጥተኛ ነው። በዘመናዊ መልኩ የማኅበረሰብ ጤናንና የሥፍራ ቁርኝትን ያስረዳው እንግሊዛዊው ዶ/ር ጆን ስኖው ነበር [3]። በ1854 (እኤአ) የለንደን ከተማ በኮሌራ ወረርሺኝ ሕዝቡ እንደ ቅጠል እየረገፈ በነበረበት ወቅት በሽታው ከምድር ወደ አየር በተንነት መልክ ይሰራጫል ተብሎ በስህተት ይታመን ነበር። ዶ/ር ስኖው ግን የተለየ መላምት ይዞ በኮሌራ ሳቢያ የሞቱትን ሰዎች መኖሪያ አድራሻና የውሃ ፓምፖች የሚገኙበትን መረጃ አሰባሰበ፤ በከተማው ካርታ ላይ አድራሻዎቻቸውን አነጠበ (plot)፤ የሟቾቹንና የውሃ ፓምፖችን ሥርጭቶች ልክ አንደ አነባበሮ ላይና ታች አድርጎ ካዛመደ (multi layering system) በኋላ የኮሌራ ወረርሽኝን መነሻና የሥርጭቱን ዘይቤ ለመተንበይ የሚያስችል ዘዴ ፈለሰመ።
በተለይም አንዱ የውሃ ፓምፕ የሚገኝበት ሥፍራ ከበርካታ ሟቾች አድራሻ ጋር በእጅጉ በመቀራረቡ የተለየ ፍተሻ አደርጎ ከመኖሪያ ቤቶች የሚወጣው የፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦ ያፈስ እንደነበርና የጉድጓድ ውሃውም በፍሳሹ በመበከሉ ለኮሌራ በሽታ መንስዔ እንደነበር አረጋገጠ፤ የታመሙት ሰዎች ደግሞ የፓምፑን እጀታዎች ስለሚበክሏቸው ኮሌራው ወደ ሌሎች ተጠቃሚዎች እንደሚተላለፍ አበሰረ። ስለዚህ መላው የለንደን ከተማ አኩል የኮሌራ መነሻና መስፋፊያ ሥፍራ አልነበረም። ይህ ውጤት ዶ/ር ስኖውን ኤፒዲሚዮሎጂ (Epidemiology) ለሚባለው የጤና ዘርፍ “አባትነት” ያበቃው ብቻ ሳይሆን ጂ.አይ.ኤስ (GIS: Geographic Information System) ለሚባል የትምህርት ዘርፍ የማዕዘን ድንጋይ ሆኗል። በጣም ተበክሎ የነበረው የውሃ ፓምፕ ሥፍራም ለመታሰቢያ በብሮድዊክ ጎዳና ላይ ሃውልት ተሰርቶለት በአላፊ አግዳሚው እየተጎበኘ ይገኛል።
ፈቀቅታ ዋጋው ስንት ነው?
ማኅበራዊ ፈቀቅታ የሚጠይቀው የሥፍራ መጠን በቀላሉ የሚመተር ቁንጽል ነገር አይደለም። ይልቁንም በሰዎች የለተለት ሕይወት ጋር የተገመደ ነው። የአንድ ግለሰብ የሀብትና የሥልጣን ደረጃ እያደገ ሲመጣ ከሌላው ግለሰብጋ ሊኖረው የሚገባው አካላዊ ርቀት እየሰፋ ይመጣል። ለምሳሌ ተራ ባለጉዳይ ሆነን ቀርበናል አሉ። ከቀበሌ ሊቀመንበሩ ይልቅ ሚንስትሩን ስናነጋግር ሊፈቀድልን የሚችለው አካላዊ ርቀት የትየለሌ ነው። ገንዘብና ሥልጣን ካለ መጠነ ሰፊ አካላዊ ርቀት አለ። ለምሳሌ አውሮፕላን ገንዘብ ላለው ተጓዥ ሁሉ የተፈቀደ ቢሆንም ሁሉም ባለገንዘብ ግን እኩል አይገለገልበትም።
የጆርጅ ኦርዌልን [4] ድንቅ አባባል ለዚህ ጽሁፍ ስንል ብናሻሽለው “ሁሉም ተጓዦች እኩል ናቸው፣ ነገር ግን ጥቂት ተጓዦች ከሌሎች ይበልጥ እኩል ናቸው” እንዲል … የቢዝነስ ክላስ ተጓዥ እግሩን አንሰራፍቶ ሲንደላቀቅ የኢኮኖሚ ክላስ ተጓዥ ግን የሚመተርለት የሥፍራ መጠን ብዙ የሚያፈናፍን አይደለም። ስለሆነም የሁለት ሜትር የርስ በርስ መራራቅ ትግበራ ጥሩ ገቢ ላላቸው ግለሰቦች የምርጫ ጉዳይ ሲሆን ለደሃ (በደሳሳ ቤት ጠላ/ሻይ ለምትሸጠው፣ ጉልት ሽንኩርት ለምትቸረችረው፣ የከተማ አውቶቡስ ለሚጠቀመው፣ ወዘተ) ግን ቅንጦት ነው። ልክ ቻርለስ ዲክንስ [5] “space is a luxury” እንደሚለው።
ደሃ ሞት አይፈራም?
በበርካታ የመድረክ ስዎች “ኮሮና ደሃ ና ሃብታምን እኩል አደረገ” ተብሎ ሲወደስ ይደመጣል። በጥልቀት ቢታይ ግን የኮቪድ19 ጥቃት ከሃብታሙ ይልቅ በድሃው ላይ በእጅጉ የሚያይል መሆኑን ነው። ለድሃ “መቀመጥ” ማለት “መቆመጥ” ነው እንዲሉ፤ ለክፉ ጊዜ ተብሎ የሚቀመጥ እርሾ ስለማይኖር፤ እንቅስቃሴ ሲቆም ህይወትም ትጨልማለች። የኒውዮርክ ታይምስ መጽሄት አንደዘገበው [6] በኒውዮርክ ከተማ ከበርቴዎች ከሚኖሩባቸው ሰፈሮች የኮሮና ወረርሺኝ በከተማቸው አንደተከሰተ ወደ 40% የሚሆኑት ኗሪዎች በሽታው ወዳልተንሰራፋባቸው አካባቢዎች መሸሽ ችለዋል።
መሸሽ ያላስፈለጋቸው ሀብታሞች ደግሞ ከቤታቸው ሳይወጡ የሚፈልጉትን በቀላሉ እያገኙ ሰንብተዋል። በተቃራኒው በኩል ደግሞ በኢኮኖሚ አቅማቸው ዝቅተኛ የሆኑት ጥቁሮችና እስፓኞች መኖሪያቸውን ሳይለቁ ወላፈኑን እየተጋፈጡት ይገኛሉ። ለምሳሌ በአሜሪካ የሚዘወተር አባባል አለ “አሜሪካ ስታስነጥስ ጥቁር ድሆቿ በኒሞኒያ ይያዛሉ”። በቅርቡ ይፋ የተደረገ ሪፖርት የሚያሳየው ከሌላው ማህበረሰብ ይልቅ ጥቁሮች በኮቪድ19 የበለጠ ተጠቅተዋል። አመዛኙ የሥራ ዘርፋቸው ጽዳት፣ ጤና፣ ጥበቃ፣ ሾፌር፣ እቃ አቅራቢ፣ ታክሲ አግልግሎት ወዘተ በመሆኑ ደግሞ ከኮሮና ጋር በሚደረገው ትግል የግንባር መስመር ተሰላፊና ተጋላጭ አድርጓቸዋል።
እንደ ሪቻርድ ፓንክረስት [7] በ1918 (እ.ኤ.አ.) አዲስ አበባ በወቅቱ ከነበራት 50,000 ኗሪ ወደ 10,000 የሚሆኑት (20%) በተለይም ወጣቱ፣ ባለሥልጣናቱና በጣት ከሚቆጠሩት ዶክተሮችም ጭምር በህዳር በሽታ ህይወታቸው ተቀጥፏል። የሃያ ስድስት ዓመቱ ራስ ተፈሪ መኮንን በመጀመሪያው ዙር ወረርሺኝ ተጠቅተው በህይወትና ሞት መሃል የነበሩ ሲሆን “በለጋ እድሜያቸው ሊሞቱ ነው” ተብሎ በዲፕሎማቶች መሃል የመረጃ ልውውጥ እየተካሄደ ነበር። ራሳቸው ወደ አዲስ አበባ እንደተመለሱ በወረሺኙ ሳቢያ ክፉኛ ታመሙ እንጂ ፊታውራሪ ሃብተ ጊዮርጊስ ዲነግዴ ለስራ ተልከው ከነበሩበት የወላይታ አውራጃ ባስቸኳይ ተመልሰው በተፈሪ መኮንን ሞት ሊፈጠር የሚችልን አለመረጋጋት እንዲያመክኑ ታቅዶ ነበር፡፡
በወቅቱ ወረርሺኙን ለመሸሽ አቅሙ የነበራቸውና ወደ ከተማው ዳርቻ በመሄድ ተወሽበው (ቀሣ ገብተው) ህይወታቸውን ያዳኑት ለምሳሌ ሊቀ ጳጳሱ አቡነ ማቴዎስ (አድዋ ድረስ ሄደው ግንባራቸውን ለጥይት ለመስጠት ያላመነቱት)፣ ከንቲባ ነሲቡ ዘአማኑኤል(ወዲያውኑ ወደ ከተማይቱ ተገደው ተመለሱ'ንጂ)፣ የበታች ሹማምንቶች፣ ወዘተ ነበሩ። ንግስት ዘውዲቱ ራሳቸው ወደ አንኮበር ለመሸሽ ተነስተው ነበር ተብሎ በወቅቱ ታምቷል፡፡ በዘመኑ ወደ አዲስ አበባ ከተማ ዳርቻ ባይሄዱም በርካቶች በሚኖሩበቸው ጊቢዎች ውስጥ ተራርቆ ለመቆየት የሚያስችል መተናፈሻ ነበራቸው። ለሥልታዊ ማፈግፈግም'ኮ ቦታና ፍራንክ ሊኖር ግድ ይላል።
ረሃብ ቀጠሮ ይሰጣል?
በኢትዮጵያ ሚዲያ የሚተላለፉትን መረጃዎችን ስንቃኝ የማኅበራዊ ፈቀቅታን ጣጣ በቅጡ ያለመረዳት ጉዳይ ይስተዋላል። የኮሮናና የማኅበራዊ ፈቀቅታ ግንዛቤ ሃዋርያ ሆነው የቀረቡት ከሃኪሞቹ ይልቅ አርቲስቶቻችን ናቸው። ጥረታቸው ይደነቃል። ሆኖም ግን ሁሉም ናቸው ባይባል አንዳንዶቹ ገና ራሳቸው በውል የተረዱት አይመስልም። ከዚህ ቀደም ገበሬው ዛፍ ቆርጦ ለተለያየ ግልጋሎት ሲጠቀም “ለምን” ብሎ የችግሩን ምንጭ ከመመርመር ይልቅ በየመድረኩና በየሚዲያው ልክ ገበሬው የዛፍን ጥቅም እንደማያውቅና አሉታዊ ውጤቱንም እንደማያስተወል፤ ወይንም አማራጭ ኖሮት ሳለ በግዴለሽነት እንደሚከውነው በመተርጎም- ልክ የወተትን ጥቅም ለድመት ማስተማር በመሰለ ምክር- በእርዳታ ሰጪዎች በጀት እየተደጎመ በራዲዮና የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች ይሰራጭ ነበር።
ሌላም አለ። “ከወንዶች ይልቅ ሴቶች ለኤች-አይ-ቪ ኤይድስ ተጋላጭ ናቸው” ሲባል ልክ ወንዶቹ የኤድስን አስከፊነት የተገነዘቡና ሴቶቹ ደግሞ ለሕይወት ዋጋ የማይሰጡ ይመስል “የግንዛቤ ማስጨበጫ ዲስኩሮች” እየተንቆለጳጰሰ ለህዝብ ይቀርብ ነበረ። አሁን ደግሞ ስለ ኮቪድ19 አስከፊነት ተነግሮ ሳለ ህዝቡ በከተማው ሲንቅሳቅስ ታየ ተብሎ አንዳንድ አርቲስቶቻችን “ዳቦ በነጻ ይታደላል የተባለ ይመስል ህዝቡ በከተማው ተተራመሰ” በማለት ሲናገሩ በድራማዎቻቸው እየታዘብን ነው። ህዝብን በደፈናው መኮነን አግባብ አይደለም። ጥቂቶች ለቅንጦት ሲሉ ያጠፋሉ። ለምሳሌ በሺሻና ጫት ቤቶች ታጉሮ በመገኘት ሊሆን ይችላል። አብዛኛው የሚንቀሳቀሰው ግን የሞት ሽረት ጉዳይ ሆኖበት ነው። ባለቅኔ ሎሬት ጸጋዬ ገ/መድኅን የረሃብን አስከፊነት አንዴት ነበር በግጥም የገለፀው?
ጠቅጥቅ ዝም ብለህ?
ከመሃል አዲሳባ ተነስተን በሁሉም አቅጣጫ ወደ ከተማዋ ዳርቻ ብንጓዝ የሰዎች ቁጥር እየቀነሰ፣ በቤቶች መሃል ያለው ርቀት እየሰፋና የግቢዎች ስፋት እያደገ መሄዱን እንታዘባለን። እንዳሁኑ ከመጠን በላይ ከመተፋፈጉ በፊት በአዲሳባ በርካታ ባዶ ሥፍራዎች የነበሩ ቢሆንም ከጊዜ ወደ ጊዜ ተመናምነዋል። በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በሰባዎቹና በሰማንያዎቹ የተቀርፁ የሙዚቃ ክሊፖች የሚያስገነዝቡን ነገር ቢኖር መሃል አዲሳባ በሰውም ሆነ በተሽከርካሪ ብዛት እንዳሁኑ መተናፈሻ አላጣም ነበር። አሁን አሁን የሙዚቃ ክሊፖች እየተቀረጹ ያሉት በከተማዋ ዳርቻ ከሚገኙ ተራርቀው የተገነቡ ቅንጡ መንደሮች ላይ መሆኑ የግጥምጥሞሽ ጉዳይ ብቻ ይሆን? በተለይም መሃል አዲሳባ አካባቢ የነበሩ ማናቸውም ቤት ያላረፈባቸው ሥፍራዎች (በዛፍና በጓሮ እርሻ ተሽፍነው የነበረ ቢሆንም እንኳ) ለግንባታ ማስፋፊያ ውለዋል። ቀድሞ በየመንደሩ የነበሩ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ደብዛቸው ጠፍቷል።
ተጨማሪ የመኖሪያ ክፍሎችን ሰርቶ በማከራየት ኑሮን መደጎም ስለሚቻል በርካቶች በመኖሪያ ግቢያቸው የነበሯቸውን ባዶ ሥፍራዎች ገንብተውበታል። ባንዳንድ ሰፈሮች በከተማው ፕላን መሰረት ቀድሞ በቂ ሥፋት የተመደበላቸው መንገዶች ከአዋሳኝ ጊቢዎች በሚደረግ ህገወጥ ማስፋፊያ እየተሸራረፉ በእጅጉ ጠበዋል [8]። ችግሩ በበረታባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ጠባብ የመተላለፊያ መንገዶች ለልብስና ጌሾ ማስጫ፣ ለድንኳን መትከያ፣ ወዘተ ጭምር ስለሚያገለግሉ የእድር መኪና አንኳ የማይገባባቸው በርካታ መንደሮች አሉ። አያርገውን’ጂ እንዲህ አይነት መንደር ኮቪድ19 አንዴ ከገባ በቀላሉ አጅ ይሰጣል?
እል፟ፍ ሲሉ እልፍ ይገኛል?
አንድ የከተማ ኗሪ የኢኮኖሚ አቅሙ ሲጎለብት ፍላጎቱም ሆነ ስጋቱ ስለሚንር ወደ ከተማ ዳርቻ ሄዶ (suburbanization በሚባለው) አመቺ የመኖሪያ ቤት ይገዛል/ይከራያል። ባብዛኛው ይህ ሥፍራ ወንጀል የማይበዛበት፤ የትምህርት ቤት ክፍሎች የማይጣበቡበትና የመኪና ማቆሚያ እጥረት የማይኖርበት ነው። የሞላለት ኗሪ ወደ ዳርቻው በተዘዋወረ ማግስት በምትኩ ወደከተማው የሚመጣው አዲስ ኗሪ ይተካበታል። ከተማ ሲሰፋ በዙርያው ያሉ የእርሻ መሬቶችን ይበላል፤ በፍትሃዊነትም ይሆን በ-ኢፍትሃዊነት አርሶ አደሮችን ያፈናቅላል። ለአብነት ሕዝቡን አስተባብሮ በቀድሞው የኢሕአዲግ መንግሥት ላይ ከፍተኛ ጫና ካደረጉ አጀንዳዎች አንዱ የአዲሳባ ከተማ ቅጥ አልባ መስፋፋትና ማስተር ፕላኑ[9] ያስከተለው ጣጣ ነበር።
ለአዲሳባ የህዝብ እድገት አንዱ መንስዔ ከሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች ወደ ከተማው የሚፈልሰው ቁጥር መበራከቱ ነው። ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ ከተሞች ላይ የተደረገ ጥናት አንደሚያሳየው ከከተሞች ርቀው በሚኖሩ ህዝቦች የሚዘወተር የጎሳዎች መሃል ጥርጣሬና ግጭት አለ። ይህ የደህንነት ሥጋት በርካቶቹን ወደ ከተሞች እንዲጎርፉ ያነሳሳቸዋል (push factorየሚባለው)። በበርካታ ክልሎች የሚገኙ ባለሃብቶች ካፒታል ሲያፍሩ በቀጣይ የሚያልሙት በአካባቢያቸው የሚገኝ ንግዳቸውን ወደላቀ ደረጃ ማሳደግ ሳይሆን ወደ አዲሳባ በመምጣት ቤት መግዛትና ኑሮን መመስረት ነው። ወደ አዲሳባ ከተማ የሚደረገው ፍልሰት እንዲጨምር ያስቻለው ከተማው በአማላይ የኢኮኖሚ አማራጮች (pull factorsየሚባሉት) ተንበሽብሾ ሳይሆን በከፊልም ቢሆን አንጻራዊ የኑሮ ዋስትና ስለተጎናጸፈ ጭምር ነው።
ችግሩ ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአዲሳባ ዳርቻ ያሉ መንደሮች በፖለቲካው ትኩሳት ሳቢያ የሰላምና የመኖር ዋስትናቸው ከጥያቄ ውስጥ መውደቁ ነው። ባንድ በኩል ወደ አዲሳባ በተናጠልም ሆነ በቡድን የሚተመው ሕዝብ እንደቀጠለ ነው፡፡ ለምሳሌ አማራው ከጉራ ፈርዳ፣ ኦሮሞው ከሶማሌ ክልል ሲፈናቀሉ መዳረሻቸው አዲሳባ እንደነበር ተመልክተናል፡፡ በሌላ በኩል አዲሳባ እንደቀድሞው ወደ ጎንዮሽ የመስፋት እድሏ ተመናምኗል። ይባስ ብሎ ቀድሞ በከተማው ዳርቻ መንደሮች የነበሩ አንዳንድ ኗሪዎች ወደመሃል አዲሳባ የሚደረግ የምልሰት አዝማሚያ (reverse suburbanization) እያሳዩ ነው።
እንደ መውጫ
የከተማ ኗሪ ለኮቪድ19 አጅግ ተጋላጭ ቢሆንም በደንብ ከተያዘ ስርጭቱን መቆጣጠር ይቻላል።ታይዋን፤ ደቡብ ኮርያና ሲንጋፖር ከተሞች ችምችም ያለ የሕዝብ ሥርጭት ኖሯቸው ሳለ አስቀድመው ርምጃ በመሰዳቸው ነው አስከፊውን የኮሮና እልቂት ያስቀሩት። የኮቪድ19 ክትባት አስኪገኝ ድረስ ማኅበራዊ ፈቀቅታን በአግባቡ መተግበር ወሳኝ የቫይረሱ መከላከያ ሆኖ ይቆያል። በህዳር በሽታ ወቅት ተተግብሮ የነበረው አገር በቀል የማኅበራዊ ፈቀቅታ በርካታ ኢትዮጵያውያንን አትርፏል። ይህ ትውልድ ደግሞ የራሱ መፍትሄ ያሻዋል። ከሌሎች ሃገራት መኮረጅ ካለበትም ከአገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር እየተገናዘበ መሆን ይኖርበታል። የችግሮች መጠንና ውስብስብነት ከሥፍራ ሥፍራ እንደመለያየቱ ሁሉ መፍትሄውም ያልተማከለ መሆን ይኖርበታል። ለዚህ ስኬት እንዲረዳ ደግሞ በሃገሪቱ ያሉ የፕሮፌሽናል አሶሴሽኖች የዘንድሮውን አመታዊ ኮንፈረንሶቻቸውን (ቨርቹዋሊም ቢሆን) በኮቪድ19 ላይ አትኩረው አባላቶቻቸው የመፍትሄው አካል እንዲሆኑ ይተጉ ይሆን?
በሌሎች ሃገራት የኮሮና ቫይረስ ቅድሚያ ስለባዎች በበሽተኛ መንከባከቢያ ጣቢያዎች (Nursing Homes) የሚገኙ ታካሚና ነርሶች ነበሩ። ይህ እንዳይደገም በአዲስአበባ ከተማ ያሉ በርካታ የአረጋውያን ማዕከላት መላ እየዘየዱ ይሆን?በተለይም የምስራቁን ድንበራችን በባህሪው ወንፊታማ በመሆኑ በድንበር ተሻጋሪ የሰዎች ዝውውር ላይ የቁጥጥር ሥርዓት ተዘርግቶ ይሆን?
የቅርብ ጊዜ የኢትዮጵያ ታሪክ የሚያሳየን ታላላቅ አደጋዎች የቀድሞ መንግስታት መሰረትን ሲያናጉና በቀጣይ አመታትም መንግሥታቱ እንደሚወድቁ ነው። በንጉሡ ጊዜ የወሎ ረሃብን፣ በደርግ ጊዜ የሰባ ሰባቱ ረሃብን መጥቀስ ይቻላል። አሁን በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ይህን ወረርሽኝ ቀዳሚ አጀንዳው አድርጎ፤ ዜጎችን አስተባብሮ፤እውቀት-መር በሆነ መንገድ ትኩረት የሚሹት ላይ በመረባረብ ሕዝቡን ይታደጋል? ወይንስ ችግሩን በማለባበስ ለውድቀቱ ጉድጓድ ይምሳል? የተቃዋሚ ፓርቲዎችስ? አጀንዳቸውን ፈታኝ በሆነው የኮቪድ19 ወረርሺኝ ላይ አተኩረው ከሕዝቡ ጋር ይረባረባሉ? ወይንስ አንደወትሮው ስቱዲዮና መድረክ ላይ ከትመው በታዛቢ ማሊያ ይጫወታሉ?
በመጨረሻም፡ ፈተናው ይከብድ ይሆን አንጂ ሁሉም ያልፋል፤ ኮሮና ቢሆንም’ኳ፡፡
ምንጭ/የግርጌ ማስታወሻ
[1] ዶናልድ ራምዝፊልድ የአሜሪካ መከላከያ ሴክሬታሪ (2001-2006) በነበረበት ወቅት “አሜሪካ የኢራቁ ፕ/ት ሳዳም ሁሴን የደበቀው ጅምላ ጨራሽ መሳሪያ አለ” ብላ የወነጀለችበትን ማስረጃ እንዲያቀርብ ሲጠየቅ በተናገረው “known knowns, known unknowns, and unknown unknowns” ጥቅስ ይታወቃል።
[2] Sorokowska, A., Sorokowski, P., ... & Blumen, S. (2017). Preferred interpersonal distances: a global comparison. Journal of Cross-Cultural Psychology, 48(4), 577-592.
[4] በ1945 (እ.ኤ.አ.) በታተመው የጆርጅ ኦርዌል “አኒማል ፋርም” መጽሃፍ “ሁሉም እንስሳት እኩል ናቸው፣ ነገር ግን ጥቂት እንስሳት ከሌሎች ይበልጥ እኩል ናቸው” የተሰኘ አባባሉ የበለጠ ይታወቃል።
[5] የሁለት ከተሞች ወግ እና ሌሎች በርካታ ልቦለድ መፃሕፍትን የደረሰው ቻርለስ ዲክንስ በጽሁፎቹ ድሃን የማማከል ሁኔታ የሚታይበት ሲሆን የራስ የሆነ ሥፍራ መኖርን (personalspace) ከምቾትና ድሎት ጋር ያቆራኘዋል።
[6] May 15, 2020.
[7] Pankhurst, R. (1990). An introduction to the medical history of Ethiopia. New Jersey
[8] በገጠርም ይሁን በከተማ የሚገኝ የጋራ ሃብት ላይ የግድየለሽነት ብክነት ሲከሰት “tragedy of the commons” ይባላል።
[9] ከአራት አመት በፊት የተቀናጀ የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን በመንግስት ሲቀርብ በከተማው ዙሪያ የሚገኝ ከ1.1 ሚሊዮን ሄክታር የኦሮሚያ መሬትን ይቀራመታል በሚል ክስ ተቃውሞ ቅስቅሶ፣ ወደ 140 የሰው ህይወት ቀጥፎ፣ በሺህ የሚቆጠሩ የአካል ጉዳት፣ በአስር ሺህ የሚቆጠሩትን ደግሞ ለእስራት ዳርጓል። ከሁለት አመታት የተቃውሞ እንቅስቃሴ በኋላ መንግስት የማስተሩን ፕላን እንደሰረዘው ይፋ ቢያደርግም አመጹ ግን ቀጥሎ ነበር።