- የቪክቶሪያ ኮቪድ ኮማንደር ጄሮን ዌይማር የቤት ውስጥ ክትባት አገልግሎት መጠቀም የሚሹ ሰዎች በቅድሚያ ጠቅላላ ሐኪማቸውን ወይም የአካባቢያቸውን የሕዝብ ሕክምና ቡድን ማናገር እንደሚገባቸው አሳሰቡ
- በምሥራቅ አውስትራሊያ የፊት ጭምብልን በቤት ውስጥ መጠቀም ዛሬ ሲያከትም፤ ምዕራብ አውስትራሊያ ውስጥ ግዴታነቱ ተራዝሟል
- የኮቪድ ቅጣት ተጥሎባቸው መክፈል ላልቻሉ የዕዳ ስረዛ እንዲደረግ ጥሪዎች ቀረቡ
- ኒው ሳውዝ ዌይልስ ውስጥ ከዛሬ ጀምሮ በአብዛኛዎቹ የቤት ውስጥ ክንውኖች ወቅት የፊት ጭምብሎችን ማጥለቅ ግዴታ መሆኑ ተገትቷል። ይሁንና የሕዝብ ትራንስፖርት፣ ሆስፒታልና የአረጋውያን ክብካቤ ተቋማትን በመሳሰሉት የፊት ጭምብሎችን የማጥለቅ ግዴታ ፀንቶ ይቀጥላል
- እንዲሁም በእሥር ቤት ጉብኝት ወቅትና ከ1,000 በላይ ታዳሚዎች በሚገኙበት የቤት ውስጥ የሙዚቃ ፌስቲቫል ሥፍራዎች የፊት ጭምብሎችን ማጥለቅ ግድ ይላል
- የቪክቶሪያ ጤና ሚኒስትር ማርቲን ፎሊ መንግሥት በተቻለ መጠን ክትባቶች አያሌ ሰዎች ዘንድ ተደራሽነት እንዲኖራቸው ለማድረግ ትኩረት ያደረገ መሆኑን ገለጡ። የጤና ባለሙያዎች ተከታቢዎች መኖሪያ ቤት ድረስ ሔደው የመከተብ ፕሮግራም እንደሚስፋፋ፣ በቤተ እምነቶች፣ ስፖርት ክለቦችና ትምህርት ቤቶች የተንቀሳቃሽ ክሊኒኮች ማዕከላት ግልጋሎትም እንዲስፋፋ የሚደረግ መሆኑን ተናግረዋል
- ቪክቶሪያ ውስጥ ከሶስተኛ እስከ ስድስተኛ ክፍል ተማሪዎች፣ የሙዋዕለ ሕፃናትና አንደኛ ደረጃ ተማሪዎች የፊት ጭምብሎችን የማጥለቅ ግዴታ አለባቸው
- አቶ ፎሊ ግዴታው ላይነሳ የቻለበት ምክንያት የአንደኛ ደረጃ ተማሪዎች ገና የሁለተኛ ዙር ክትባቶችን ያልተከተቡ መሆኑን ጠቅሰዋል
- ደቡብ አውስትራሊያ በግል ልዩ ዝግጅቶች ወቅት የዳንስና ዘፈን ዝግጅቶችን ማካሔድ እንዲቻል ፈቀደች። እንዲሁም ከዚህ ሳምንት መጨረሻ ጀምሮ ከቤት ውጪ በሚካሔዱ ትላልቅ የስፖርት ክንውኖች ላይ የሚታደሙና በቁም መጠጦችን የሚጎነጩ ሰዎች ቁጥር ከ50 ፐርሰንት ሳይበልጥ እንዲስተናገዱ ፈቃድ ቸራለች
ኮቪድ-19 ስታቲስቲክስ፤
ኒው ሳውዝ ዌይልስ 7,583 ነዋሪዎቿ በቫይረስ የተጠቁ ሲሆን፤ የስድስት ሰዎች ሕይወት አልፏል። ሆስፒታል ከሚገኙት 1,144 ሕመማን 64 በፅኑዕ ሕሙማን ክፍሎች ይገኛሉ።
ቪክቶሪያ ውስጥ 6,580 በቫይረስ ሲጠቁ፤ 11 ሕይወታቸውን አጥተዋል። ሆስፒታል ከሚገኙት 301 ሕመማን 38 በፅኑዕ ሕሙማን ክፍሎች 4 በአየር መተንፈሻ መሳሪያ እየተረዱ ይገኛሉ።
ኩዊንስላንድ 5,440 ነዋሪዎች በቫይረስ ሲያዙ፣ 7 ሰዎች ለሕልፈተ ሕይወት ተዳርገዋል። ሆስፒታል ከሚገኙት 350 ሕመማን 30 በፅኑዕ ሕሙማን ክፍሎች ይገኛሉ።
ታዝማኒያ 851 ሰዎች በቫይረስ ሲጠቁ፤ ሆስፒታል ከሚገኙት 11 ሕሙማን መካክል ሁለት ግለሰቦች በፅኑዕ ሕሙማን ክፍል ይገኛሉ።
የአውስትራሊያ ካፒታል ቴሪቶሪ 773 ነዋሪዎች በቫይረስ ተይዘዋል። ሆስፒታል ከሚገኙት 41 ሕመማን 3 በፅኑዕ ሕሙማን ክፍል ይገኛል።
Find a COVID-19 testing clinic
Register your RAT results here, if you're positive