የቪክቶሪያ የእስልምና ምክር ቤት ሜልበርን ውስጥ የኮሮናቫይረስ መዛመትን አስመልክቶ ፍትሃዊነት በጎደለው መልኩ ሰሞነኛ የሚዲያ ዘገባዎች "ክፍፍል፣ ጥላቻና ፍርሃት"ን እያሳደሩ ነው ብሏል።
ምክር ቤቱ ባለፉት ጥቂት ቀናት ውስጥ የሔራልድ ሰን አምደኛ አንድሩ ቦልትና የስካይ ኒውስ ተንታኝ ፒታ ክሬድሊን የቫይረሱን መስፋፋት ከመድብለ ባሕል ማኅበረሰባት ጋር በማያያዝ በጣት መጠቆሚያነት ማመላከታቸውን ጠቁሟል።
የቪክቶሪያ እስልምና ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚደንት አዴል ሳልማን ምንም እንኳ ለቫይረሱ ማገርሸት ሙስሊሞች ምክንያት ስለመሆናቸው ይህ ነው የሚባል ማስረጃ ባይኖርም የተወሰኑ የሚዲያ ተቋማት በማኅበረሰቡ ላይ ከማነጣጠር እንዳልተገቱ በመግለጥ ቅሬታቸውን ገልጠዋል።
አያይዘውም፤
"ትርክቱ እኒህ እንዲህ ያለውን ትርክት በሚያምኑቱ ዘንድ ይወሰዳል 'ይኸው - ሙስሊሞች አስጊዎችቻን ናቸው፤ በጠብመንጃዎች፣ ቦምቦችና መኪናዎች ሊጎዱን ሲሞክሩ ነበር አሁን ደግሞ በቫይረስ እየመጡብን ነው ያሰኛል"
"ይህ በምንም አይነት ፍታሃዊ አይደለም። አንዳችም ማስረጃ የለም፤ አጋዥነትም የለውም። ደህንነታችንን አይታደግም፤ ችግሮችንም አይከላም። ማኅበረሰቡን ለሃፍረት ይዳርጋል፣ መከፋፈልን ይፈጥራል፣ ጥላቻና ፍርሃትን ያሳድራል። ከሁሉም በበለጠ ሁላችንንም ይጎዳል" በማለት ለ SBS ተናግረዋል።
ሰሞኑን ኮሮናቫይረስ ሜልበርን ውስጥ የተስፋፋባቸው ሥፍራዎች በርካታ የመድብለ ባሕልና ቁጥራቸው ከፍተኛ የሆኑ ሙስሊሞች የሚኖሩባቸው የሰሜንና ሰሜናዊ - ምዕራብ ቀበሌዎች ናቸው።
ቀበሌዎቹ በቪክቶሪያ መንግሥት የኮሮናቫይረስ ማዕከልነት ተፈርጀዋል። የቫይረስ ምርመራም በስፋት እየተካሄደባቸው ይገኛል።
አቶ ሳልማን በተለይ የአካባቢው የሙስሊም ነዋሪዎች ላይ ያነጣጣሩ የሚዲያ ዘጋቢዎች ወደ ሥፍራው እየተላኩ መሆኑን ጠቁመዋል።
አክለውም "ሙስሊሞችና የሙስሊም ማኅበረሰብ በወረረሽኙ ወቅት ሁሉ በአብዛኛው ኃላፊነትን በተመላበት ድርጊት ፈጻሚነት በምሳሌነት የተነሳን ነን" ብለዋል።
ባለፈው የወርኃ ረመዳን ጾም ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ስኮት ሞሪሰን "አውስትራሊያውያን ሙስሊሞች እንደ ሁሉም አውስትራሊያን በቅርብ ጊዜያት ውስጥ ታላቅ መስዋዕትነቶችን ከፍላችኋል… ይህንንም በፈቃደኝነት ተግብራችኋል፤ አንዳችን አንዳችንን በመታደጉ ረገድ፣ በፍቅርና እምነት አማካኝነት መስዋዕትነቶችን በተግባር ከፍላችኋል" ሲሉ አውስትራሊያውያን ሙስሊሞች ቫይረሱን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በተደረጉት አገራዊ ጥረቶች ላይ ያበረከቱትን አስተዋፅዖዎች አወድሰው ማንሳታቸው ይታወሳል።