የገንዘብ አስከፋይ ዕገታዎች ሥፍራና ስርጭት በኢትዮጵያ

አሁን አሁን በኢትዮጵያ በርካታ ዜጎች በማናቸውም ሰዓት በታጠቁ አካላት ይታገታሉ። በህይወት ተርፈው እንዲለቀቁ እስከ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ክፍያ ይጠየቅባቸዋል። ሌላው ይቅርና በስደተኛ ጣቢያዎች ተጠልለው የሚገኙ ህጻናት እንኳ የዕገታ ሰለባ ናቸው። ከዕገታው ሂደት በኋላ በህይወት የማይመለስም አለ። በኢትዮጵያ ኤኮኖሚያዊ አቅሙን ማጎልበት የቻለ ግለሰብም ሆነ ቤተሰብ በዕገታ ወረርሽኝ ሳቢያ ወደ ድህነት አረንቋ እየዘቀጠ ይገኛል።

KIDNAPPING.jpg

The trio -journalist Javier Ortega, photographer Paul Rivas and driver Efrain Segarra- had been kidnapped and slain while covering a story on violence along the remote border with Colombia, prompting both countries to send troops to hunt down the perpetrators. Credit: Luis ROBAYO / AFP) (Photo by LUIS ROBAYO/AFP via Getty Images

ዕገታ ቀድሞ ከመሃል አገር ርቆ በጥቂት የውጪ ሃገር ዜጎችና የእርዳታ ድርጅት ሠራተኞች ላይ ይከሰት ነበር። ዛሬ ሆኖ እንደ ሰደድ እሳት ቢዛመትም ሁሉም ሥፍራ በእኩል መጠን እየተለበለበ አይደለም።

ዕገታ በኢትዮጵያ ከመደበኛ ዜናነት ባሻገር አስጊ ደረጃ ላይ መድረሱን የሚያመላክተው የበለጸጉ አገራት (ለምሳሌ እና ) ዜጎቻቸው ወደ ኢትዮጵያ እንዳይሄዱ መምከራቸው ነው።

 ዕገታ የዘፈቀደ ክንውን አይደለም።

ዕገታ በረቀቀ ዕቅድ እና በተመረጡ ተዋንያን የሚተወን ነው። ቢያንስ “የተነቃቃና የታጠቀ አጋች”፣ “ገንዘብ አስገኚ ታጋች” እና “ምቹ የማገቻ ሥፍራ” ስለሚኖረው የሶስት ማዕዘናዊ የወንጀል ቅርጽ (crime triangle) ል። ሁሉም ሥፍራ ለማገቻነት እኩል አያመችም።

አካባቢው በተለይ በአማጺና በመንግሥት ኃይሎች ግጭት ስር ሲውል፤ የተቀናቃኝ ቡድኖች በአካባቢው ላይ የይገባኛል ጥያቄ ሲያነሱበት፣ ወይንም ሥፍራውን የባላንጣ ታጣቂዎች የሚያዘወትሩት ሲሆን ለዕገታ ወንጀል መበራከት አመቺ ይሆናል።

የዕገታ ዓላማም ሆነ አድራሻ ተለዋዋጭ ነው።

ኢትዮጵያ አልፎ አልፎ ለፖለቲካ እውቅና ሲባል የሚተገበሩ ዕገታዎችን ታስተናግድ ነበር። ባለፉት ግማሽ ምዕተ ዓመታት (እ.ኤ.አ. ከ1970 እስከ 2020) በርካታ የኢትዮጵያ አማጺዎች

በዝርዝሩም ሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ፓርቲ፣ የአፋር አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ ግንባር፣ የኦጋዴን ነፃ አውጪ ግንባር፣ አልሸባብ፣ የቴፒ ወጣቶች፣ የግንቦት ሰባት አርበኞች ግንባር፣ የሙራሌ ታጣቂዎች፣ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር፣ የሳምሪ ሚሊሻ፣ የአማራ ሚሊሻዎች ይገኙበታል።

የዕገታ ዓላማ በጊዜ ሂደት ተቀያያሪ ነው። በበርካታ ሀገራት ታጣቂ ቡድኖች ነፃነትን ወይንም የፖለቲካ ግብን ለማስገኘት የዕገታ ስትራቴጂን ያስቀድማሉ። በሂደት ግን ዕገታን እንደ ኤኮኖሚያዊ የጥቅም ምንጭነት ይጠቀሙበታል።

ለምሳሌ በ1970ዎቹ በናይጄሪያ አካባቢያዊ ብክለትን ለማስቆም ተቋቁመው የነበሩ ተዋጊ ቡድኖች በሂደት ዓላማቸውን ቀይረው ወደ ገንዘብ አስመጪ የዕገታ አይነት አሸጋግረውታል።

 ገንዘብ አስከፋይ ዕገታ (kidnapping for ransom) ሁሌም አንድ ቦታ አይረጋም። የታጋቹ ቁጥርና ሃብት መጠን ሲሟጠጥ፣ የአጋቾቹ መውጫና መግቢያ ምስጢራዊነት ሲያበቃ፣ እንዲሁም አዲስና አመቺ ሥፍራ ሲገኝ ዕገታው “ስልታዊ ሽግሽግ” ያካሂዳል።

መንግሥትና ኅብረተሰቡ ጸንተው በቁርጠኝነት ሲታገሉት ደግሞ ከናካቴው ይከስማል።

ዕገታው ምን ያህል ተሰራጭቷል?

በባለፉት 26 ዓመታት በዓለማችን የተከሰቱ ግጭቶችን ከሚሰንደው ከተሰኘ የመረጃ ተቋም መገንዘብ እንደሚቻለው በኢትዮጵያ 10,075 የግጭት ጥቃቶች ተከስተው ወደ 65,810 ዜጎች ለአደጋ ተጋልጠዋል።

ከዚህ ውስጥ 89 የሚሆኑት የዕገታ/አፈና ሰለባዎች ናቸው። እስከ 80% የሚሆኑ ዕገታዎች ለሚዲያም ሆነ ለመንግሥት የጸጥታ አካላት ይፋ አይደረጉምና ይህ ቁጥር ከነባራዊው ሁኔታ አንጻር እጅግ ያነሰ ነው።

 እ.ኤ.አ. እስከ 2020 ድረስ በኢትዮጵያ የተዘገበው የዕገታ ኩነት ኢምንት ነበር። ሆኖም ከ2020 ጀምሮ ዕገታ ከፍተኛ ዕድገት አስመዝግቧል፣ ከ2020 እስከ 2021 የ600% ከ2021 እስከ 2022 ደግሞ የ136% ዕድገት ተከስቷል (ምሥል 2)።

የ2023 ገና ያልተጠናቀቀ ቢሆንም በዓመቱ መጨረሻ ቁጥሩ በ 78% ሊያድግ እንደሚችል መተንበይ ተችሏል።

ለአብነት በሰሜን ሸዋ ፍቼ አካባቢ የሚከናወኑ ዕገታዎች ሶስት ቁልፍ ሥፍራዎች አሏቸው።

አንደኛው የግል፣ የዘመድ፣ ወይንም የተመዘበረ የመንግሥት/ የህዝብ ገንዘብ ይኖረዋል ተብሎ የተገመተ ግለሰብ የመኖሪያ አድራሻ ነው። ዒላማ የተደረገው ግላሰብ በታጣቂዎች ታግቶ በጭለማ ለሰዓታት በእግር እንዲጓዝ ይገደዳል።

ሁለተኛው ገንዘብ እስኪከፈል ለቀናት ወይንም ለሳምንታት ታጋቹ የቤት ውስጥ እስረኛ ሆኖ የሚቆይበት ሥፍራ ነው።

ሶስተኛው ሥፍራ ደግሞ የገንዘብ መቀባበያው ነው። የተጠየቀው ገንዘብ ተከፍሎ ታጋቹ ዕድለኛ ከሆነ በሕይወት ሊለቀቅ ይችላል።
Data 1.jpg
ምሥል 1፡ የኢትዮጵያ የዕገታ ቦታዎች ሥርጭት። ሶስቱ ክበቦች ከፍተኛ የዕገታ ክምችት የተስተዋለባቸው ሲሆኑ ሥርጭታቸው ግልጽ እንዲሆን ሲባል ጎልተው ቀርበዋል። Credit: DKW
ዕገታ የበረከተው የት ነው?

ዕገታዎች በመላው ኢትዮጵያ በእኩል መጠን አልተሰራጩም። በኦሮሚያ 58%፣ በአማራና ሶማሌ 10%፣ በትግራይ እና አፋር 6% የዕገታ ክምችት ተከስቷል። በኦሮሚያም ቢሆን ዞኖች እኩል የዕገታ ተጋላጭነት የላቸውም።

በምሥል 1 እንደሚታየው የዕገታ ክምችት የተከሰተው በአዲስ አበባ ከተማ አቅራቢያ፣ በምዕራብ ኦሮሚያ፣ እና በማዕከላዊው ሰሜን የኢትዮጵያ ክፍል ነው። በተጠቀሱት ሶስት ሥፍራዎች ዕገታ የመከማቸቱ ጠባይ “የወንጀል ክምችት ህግን” () ያመላክታል።

 ምሥል 2 በማያሻማ መልኩ (statistically significant) ዕገታ የተፋፋመባቸውን ሥፍራዎች ያሳያል። ቦታዎቹ የከፍተኛ ዕገታ ቁጥርን ከሚሸፍኑት ሥፍራ ጋር አቆራኝቶ ነው።

ለምሳሌ በምዕራብ ወለጋ አካባቢ በርካታ ዕገታዎች ቢመዘገቡም ዕገታ የተፋፋመበት ሥፍራ ሆኖ አልተገኘም። ምክንያቱም በዕገታዎቹ ቦታዎች መሃል ያለው ክፍተት በሰሜን ሸዋ ከታየው በዕገታዎች ክፍተት መጠን በላይ የሰፋ ነውና።
Data 2.jpg
ምሥል 2፡ በኢትዮጵያ የዕገታ ሥርጭት የተፋፋመባቸው (hotspot) ሥፍራዎች። Credit: DKW
በሌሎች ሐገራት እንደታየው ዕገታ በክልል ድንበሮች አካባቢ ይበረክታል። በኢትዮጵያ ወደ 80% የሚሆኑት ዕገታዎች ከክልል ድንበር ወሰኖች በ 50 ኪ.ሜ ርቀት ውስጥ ተከስተዋል።

በምሥል 3 ዕገታ እንዴት በሂደት ወደ መሃል ኢትዮጵያ እየተከማቸ መሆኑን ለመገንዘብ ይቻላል።

በ2020 ምንም ዕገታ በክበቡ ውስጥ ሳይዘገብ በ2023 78% የሚሆነው ዕገታ ተከማችቶበታል። ዕገታ ወደ መሀል ሀገር የመበርከቱ ጉዳይ ወረርሺኙ ወደ መላው ኢትዮጵያ በቀላሉ ለመስፋፋት የሚኖረውን ሰፊ ዕድል ያመላክታል።

ለዕገታ መበራከት በርካታ መንስዔዎች አሉ።

ለዕገታ መበራከት የህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ድንበር ኬላዎችን እያለፈ በገፍ ወደ አገሪቱ መግባቱ፣ ከፍተኛ የስራ አጥነት ችግር መኖሩ፣ በበርካታ ሥፍራዎች የመንግሥት መዋቅርና ቁጥጥር ደካማ መሆኑ፣ አንዳንድ የመንግሥት የጸጥታ አካላትና ባለስልጣናት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከወንጀለኞቹ ጋር መጣመራቸው፣ ክልሎች ሚሊሻና ልዩ ኃይልን በገፍ እየመለመሉ ማሰልጠናቸውና ጥቂት የማይባለው ምሩቅ ደግሞ ከነታጠቀው መሳሪያ ክህደት (defection) በመፈፀም ወደ ዘራፊነት ወይንም አጋችነት መቀየሩ፣ ወዘተ መጥቀስ ይቻላል።

የተጠቀሱት ምክንያቶች በርክተው የታዩባቸው አንዳንድ የኦሮሚያ ክልል ዞኖች “የሞት ቀጣና” ለመባል በቅተዋል።

 
Data 3.jpg
ምሥል 3፡ እ.ኤ.አ. ከ2020 በኋላ በመሐል ኢትዮጵያ የተከሰተ ዓመታዊ የዕገታ ሥርጭት። ቢጫ ቀለም ያላቸው ክበቦች ከአዲስ አበባ ድንበር በመነሳት 125 ኪሎ ሜትር ርቀትን ይሸፍናሉ። በክበቦቹ ዙሪያ የሚታየው ቁጥር በያመቱ ከአጠቃላይ የዕገታ ውስጥ ስንት መቶኛው በተጠቀሰው ራዲየስ ውስጥ እንደሚገኝ ያሳያል። Credit: DKW
ለዕገታ ተጋላጭ የሆኑትን አካባቢዎች መለየት ይቻላል።

የድንበር ወዝግብ ያለባቸውን አካባቢዎች፤ ከሰራዊት ተቀናሽና ከዳተኞች የሚበዙበትን አካባቢዎች፣ የመንግሥት ተቋማት የተዳከሙባቸውን አካባቢዎች፤ የጦር መሳሪያ ዝውወር የሚበረክትባቸውን አካባቢዎች “ለዕገታ ተጋላጭ አካባቢ” ብሎ መሰየም ይቻላል።

አካባቢዎቹ ቅድመ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ እንቅስቃሴ መጀመር የነበረበት ትክክለኛ ጊዜ ትላንት ሲሆን፣ ዘገየ ከተባለ ደግሞ ዛሬ ነው። ነገን መጠበቅ ግን ትልቅ ስህተት ነው።

ምን ይደረግ?

ለዕገታ መስፋፋት አመቺ ሁኔታዎች እየበረከቱ በመሆኑ ችግሩ ወደ ባሰ ቀውስ መሸጋገሩ አይቀርም። ብሔር፣ ሃይማኖትና ዕድሜ ሳይለይ ሁሉም ዜጋ ይጎዳል። የሀገሪቱ ገጽታ፣ የውጭ ኢንቨስትመንት፣ ቱሪዝም፣ ወዘተ በእጅጉ ይላሽቃል። ሌላው ይቅርና የመንግሥት ባለስልጣናትም የዕገታ ሰለባ ይሆናሉ።

የዕገታ ወረርሽኝን ለመግታት መንግሥትና ማኅበረሰቡ በቅንጅት መስራት ቢኖርባቸውም በተለይም መንግሥት አወዛጋቢ የክልል ድንበር የተከሰተባቸው አካባቢዎች ለዕገታ መስፋፋት አመቺነታቸው ታውቆ ውዝግቡ በፍጥነት ሊፈታ ይገባል፣ የአገሪቱ ድንበር ኬላዎች ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ ይኖርበታል፣ ዘላቂ በመጨሻም የራሱን ባለስልጣናት ንጽህና መፈተሽ ይኖርበታል።

ሕግና ሥርዓት እንዲተገበር ቆፍጠን ብሎ ካልተንቀሳቀሰ ችግሩ እየከረረ ከመጣው የዘርና ኃይማኖት ውጥንቅጥ ጋር ተወሳስቦ ኮሎምቢያም ሆነ ናይጄሪያ ካስተናገዱት የዕገታ ሰቆቃ የከፋ ነው የሚሆነው።
 
============

ዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር)

 


 




Share
Published 29 August 2023 12:57am
By Daniel Kassahun (PhD)
Source: SBS

Share this with family and friends