የሜልበርንና ሚችል ሻየር ነዋሪዎች ጭምብል እንዲያጠልቁ ግዴታ ተጣለባቸው

ጭምብል ሳይለብሱ ከቤታቸው በሚወጡ ነዋሪዎች ላይ ፖሊስ የ $200 ዶላርስ መቀጮ ይጥላል።

FACE COVERINGS MANDATORY FOR MELBOURNE AND MITCHELL SHIRE

Victoria has now made it mandatory to wear masks in public within coronavirus hotspots. Source: AAP

ቪክቶሪያ ዛሬ እሑድ 363 አዲስ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎችን ባስመዘገበችበት ዕለት፤ የቪክቶሪያ ፕሪሚየር ዳንኤል አንድሩስ ቫይረሱ ሰፍኖ ያለባቸው የሜልበርንና ሚችል ሻየር ነዋሪዎች ጭምብል አጥልቀው እንዲንቀሳቀሱ ግድ የሚያሰኝ ድንጋጌን መንግሥታቸው መጣሉን አስታውቀዋል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁም እስከ ኦገስት 16 እኩለ ለሊት ድረስ ጸንቶ ይቆያል።

ጭምብል የማጥለቅ ድንጋጌውም ከጁላይ 22 ረቡዕ 11.59 pm ጀምሮ ግብር ላይ ይውላል።

ድንጋጌውን ተላልፈው ጭምብል ሳያጠልቁ ከቤታቸው የሚወጡ ሰዎች ላይ ፖሊስ $200 መቀጮ ይጥላል። 

የሜልበርንና ሚችል ሻየር ነዋሪዎች ጭምብል ሳያጠልቁ መንቀሳቀስ የሚችሉባቸው አስባቦች እንዳሉም መንግሥት ገለጧል።

እነሱም፤ በሕክምና ምክንያት፣ ዕድሜያቸው ከ12 ዓመት በታች የሆኑ ልጆች፣ ለአካላዊ እንቅስቃሴ ሩጫ በሚደረግበት ወቅት (ከሩጫ በፊትና በኋላ ጭምብል መልበስ ግድ ይላል) ናቸው።

ትምህርት ቤቶች ውስጥ መምህራን በሚያስተምሩበት ወቅት ጭምብል ማጥለቅ ግድ አይሰኙም።

ሆኖም ከ11ኛ እስከ 12ኛ ክፍልና የ VCE እና VCAL ተማሪ የ10ኛ ክፍል ተማሪዎች ጭምብል ማጥለቅ ይጠበቅባቸዋል።

መሥሪያ ቤቶችን አስመልክቶ መንግሥት ከቪክቶሪያ ኢንዱስትሪና ሠራተኛ ማኅበራት ጋር መክሮ በመጪዎቹ ቀናት ውሳኔውን ያስታውቃል። 

ፈቃድ ባለው ጉዳይ ወደ ሜልበርናን ሚችል ሻየር የሚዘልቁ የገጠር አካባቢ ነዋሪዎች በእንቅስቃሴያቸው ወቅት ጭምብል የመልበስ ግዴታ አለባቸው።

የቪክቶሪያ መንግሥት ለሚቀጥሉት ሁለት ሳምንታት የኮሮናቫይረስ ዳታን በመገምገም ወደ ደረጃ 4 ገደቦች መሸጋገር ያስፈልግ ወይም አያስፈልግ እንደሁ ከውሳኔ ላይ ይደርሳል።

የኮሮናቫይረስ መመርመሪያ ጣቢያዎችን ለማወቅ ካሹ  coronavirus.vic.gov.au ድረ-ገጽን ይጎብኙ አለያም 1800 675 398 ደውለው ይጠይቁ።

 


Share

Published

Presented by Kassahun Seboqa Negewo

Share this with family and friends