ከዛሬ ከምሽቱ 6pm ጀምሮ እስከ ጁላይ 9 እኩለ ለሊት ድረስ ጸንቶ የሚቆይ የኮሮናቫይረስ ገደቦች በመላ ሲድኒ ከተማ፣ ብሉ ማውንቴንስ፣ ማዕከላዊ ኮስትና ዎሎንጎግ ላይ ተጥሏል።
ገደቡ ሪጂናል ኒው ሳዝ ዌይልስንም ያካትታል።
ለሁለት ሳምንት የሚቆየው ገደብ የተጣለው የኒው ሳውዝ ዌይልስ ካቢኔ አስቸኳይ የቀውስ ስብሰባ ካካሔደ በኋላ ነው።
ዓርብ ዕለት የተገለጠውን የ17 ሰዎች በቫይረሱ መጠቃት ጨምሮ ባለፉት 24 ሰዓታት 29 ሰዎች በቫይረሱ ተይዘዋል።
ገደቡን ተከትሎ ከቤት ለመውጣት የሚቻለው ለገበያ ሸመታና ግልጋሎቶች፣ የሕክምና ክብካቤ፣ ለኮሮናቫይረስ ክትባት፣ አካላዊ እንቅስቃሴ ለማድረግ (በቡድን ከ10 ሰዎች ያልበለጡ) ከቤት ሆኖ ለመሥራት ወይም ለመማር ለማያስችሉ አስፈላጊ ለሆኑ ሥራዎችና ትምህርት ይሆናል።
ከእሑድ ጁን 27 ከምሽቱ 11:59pm ጀምሮ የሠርግ ሥነ ሥር ዓት ማካሔድ የማይቻል ሲሆን፤ ቀብር ላይ ለአንድ ሰው በአራት ስኩየር ሜትር በተወሰነ ርቀት ከ100 ያልበለጡ ለቀስተኞች ሊታደሙ ይችላሉ። በቤት ውስጥ የፊት ጭምብል ማጥለቅን ግድ ይላል።
የማኅበረሰብ ስፖርት የተጣሉት ገደቦች እስኪነሱ አይካሄድም።
ሕጻናት ጨምሮ ቤተሰብን ለመጎብኘት ቁጥራቸው ከአምስት መብለጥ አይችልም። ከመኖሪያ ቤት ውጪ መሥሪያ ቤቶችን ጨምሮ በውጪ የሚካሔዱ ኩነቶችን አክሎ የፊት ጭምብል ማጥለቅ ግዴታ ይሆናል።