የኮሮናቫይረስ ተጋቦት በሜልበርን እየናረ መምጣት ሳቢያ የቪክቶሪያ ጤና ባለሥልጣናት ነዋሪዎች ቢያንስ ሕዝብ በሚበዛባቸው ሥፍራዎች ጭምብል እንዲያጠልቁ ምክረ ሃሳብ እያቀረቡ ነው።
ሜልበርናውያንን ግዴታ አልባ ጭምብል የማጥለቅ ጥያቄ
ቪክቶሪያ ውስጥ ጭምብል ማጥለቅ ግዴታ አይደለም። ይሁንና የኮሮናቫይረስ ገደቦች የተጣሉባቸው የሜልበርንና ሚችል ሻየር አካባቢ ነዋሪዎች በውዴታ ፊትና አፍንጫዎቻቸውን በጭምብል እንዲሸፍኑ ተጠይቀዋል።
ፕሪሚየር ዳንኤል አንድሩስ - ትናንት ዓርብ ሜልበርናውያን ጭምብል እንዲያጠልቁ ምክረ ሃሳባቸውን ሲለግሱ፤
"ይህ ግዴታ አይደለም፤ ጥያቄ እንጂ። እየጠየቅናችሁ ያለው ማኅበራዊ ርቀትን መጠበቅ በማትችሉበት ሁነት ጭምብል እንድታጠልቁ ነው"
"ይህ አነስተኛ አስተዋፅዖ ነው። ሆኖም ትልቅ ለውጥን ሊፈጥር የሚችል ነው" ብለዋል።
አክለውም በቅርቡ መንግሥት ሁለት ሚሊየን ዳግም ታጥበው ጥቅም ላይ መዋል የሚችሉ ጭምብሎችን ገደቦቹ ለተጣሉባቸው አካባቢዎች እስኪያዳርስ ድረስ አንድ ሚሊየን ለአንድ ጊዜ ብቻ ጥቅም ላይ የሚውሉ ጭምብሎችን እንደሚያቀርብ ተናግረዋል።
የቪክቶሪያ ዋና የጤና ኃላፊ ብሬት ሳተን በበኩላቸው ጭምብል የቫይረሱን መስፋፋት ከመግታት አኳያ እገዛ እንደሚያደረግ ዓለም አቀፍ መረጃዎች ያሉ መሆናቸው ሲጠቁሙ፤

Masks could be a helpful additional measure in situations where social distancing was not possible, Premier Daniel Andrews said. Source: AAP
"ሰዎች የ 1.5 ሜትር ርቀቶችን በማይጠብቁበት ሁኔታዎች ውስጥ በርካቶች ጭምብሎችን ካጠለቁ ትልቅ አስተዋፅዖ ያደርጋሉ። ተጋቦቱን በሁለት - ሶስተኛ እንዲቀንስ ማድረግ ይችላሉ" በማለት ምክረ ሃሳባቸውንና ፋይዳዎችን ገልጠዋል።
የቪክቶሪያ የጤና ዲፓርትመንት እንደምን ጭምብል ቤት ውስጥ ማዘጋጀትና ለበርካታ ሳምንታት አጥቦ መጠቀም እንደሚቻል መረጃዎችን መስጠት ጀምሯል።
በሌላም በኩል፤ በኒው ሳውዝ ዌይልስ ዩኒቨርሲቲ የተላላፊ በሽታዎች መረጃ ፕሮግራም ዳይሬክተር ዶ/ር አብራር ቹግህታይ ጭምብል ማጥለቁ ጠንክሮ ግብር ላይ እንዲውል ያላቸውን አተያይ ሲያጋሩ፤
"እንደ እኔ ሃሳብ ከሆነ ሜልበርን ውስጥ በተለይም ከፍተኛ ተጋቦት ያሉባቸው ክፍለ ከተማዎች፣ በርካታ ሰዎች የሚገኙባቸው ሥፍራዎችና አደባባዎች አካባቢ ጭምብል ማጥለቅ ውዴታ ሳይሆን ግዴታ መሆን ይገባዋል" ብለዋል።