የአውስትራሊያን ዜግነት ለመቀበል እየፈጀ ያለው የቆይታ ጊዜ 'ተቀባይነት' የለውም

የመጤ ድጋፍ ሰጪዎች በኮቪድ - 19 ሳቢያ የአውስትራሊያን ዜግነት ለመቀበል የሚወስደው የተራዘመ ጊዜ አሳስቦናል እያሉ ነው።

Long waiting times for citizenship processing branded as 'unacceptable'

This year's pre-pandemic Citizenship Ceremony in Newcastle, NSW Source: AAP

የአገር ውስጥ ጉዳዮች ዲፓርትመንት አኃዝ እንደሚያሳየው ከሆነ የአውስትራሊያን ዜግነት በልዩ ሥነ ሥርዓት ላይ ተገኝተው ዜግነት ለመቀበል ማመልከቻዎቻቸው እስካሁን ይሁንታን ሳያገኝ 23 ወራት ያስቆጠሩ አመልካቾች 75 ፐርሰንት ደርሷል።

ባለፈው ዓመት ወርኃ ጁን በልዩ ሥነ ሥርዓት ዜግነት ለመውሰድ ቀርበው የነበሩ የዜግነት ማመልከቻዎች ይሁንታን ሳያገኙ 16 ወራትን አስቆጥረዋል።  

የአውስትራሊያን ዜግነት ለመውሰድ ካመለከቱት ዘጠና ፐርሰንቱ የዚህ ዓመት አመልካቾች 25 ወራት ይፈጅባቸዋል።

ከአንድ ዓመት በፊት 20 ወራትን ወስዷል።

 የአገር ውስጥ ጉዳዮች ዲፓርትመንት ቃል አቀባይ ወረርሽኙ የዜግነት ማመልከቻ ውሳኔ አሰጣጥ ላይ ያሳደረውን ተፅዕኖ አስመልክተው ለ SBS News ሲገልጡ፤

"በኮቪድ - 19 ወረርሽኝ ሳቢያ ቃለ መጠይቅና የዜግነት ፈተናዎችን የመሰሉ የፊት-ለፊት ቀጠሮዎች እንዲቆዩ ተደርገዋል። ይህም ሂደቱ ሊወስድ ከሚገባው ጊዜ በላይ እንዲራዘም አድርጎታል። ሁኔታዎች አስተማማኝ ሲሆኑ ዲፓርትመንቱ በአካል ቃለ መጠይቆችን ማድረግና ፈተናዎችን መፈተኑን ይቀጥላል። ይህም ሆኖ ዲፓርትመንቱ አዳዲስ ማመልከቻዎችን እየተቀበለ ነው" ብለዋል።   

ይሁንና የአውስትራሊያ መጤዎች ምክር ቤት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ካርላ ዊልሻየር ግና 'ወረርኙ ባለበት ሁነትም ቢሆን የቆይታ ጊዜዎቹ ተቀባይነት ያላቸው አይደሉም፤ በተቻለ መጠን አፋጣኝ እርምጃዎች ሊወሰዱ ይገባል' በማለት አሳስበዋል።

በመጤዎች ውክልና ሥራ ላይ ተሰማርተው ያሉት የሜልበርኑ ከርክ ያን በበኩላቸው 'የዜግነት ማመልከቻዎችን የማከናወኑን የጊዜ መራዘም አስመልክቶ በመንግሥት በኩል አጥጋቢና ተቀባይነት ያላቸውን ማብራሪያዎች አልተመለከትኩም፤ ደምበኞቼንም እያሳሰበ ነው' ሲሉ የበኩላቸውን አስተያየት ሰጥተዋል።

 ዲፓርትመንቱ በኦንላይን የዜግነት አሰጣጥና ቅበላ ሥነ ሥር ዓትን ከጀመረ እስከ 22 ሜይ ድረስ 750 አመልካቾች በየዕለቱ ዜግነት እየወሰዱ ይገኛሉ። እስካሁን በዚህ መልኩ ከ16,800 በላይ ሰዎች የአውስትራሊያ ዜግነትን ተቀብለዋል።

117,958 ማመልከቻዎች ይሁንታን ይጠብቃሉ።

 

 


Share

Published

Updated

By Nick Baker, Allan Lee
Presented by Kassahun Seboqa Negewo

Share this with family and friends