ለባንኮቹ እገዛ ሰበብ የሆነውም ወረርሽኙን ተከትሎ በተፈጠረው ማኅበራዊ መገለል ሳቢያ ሪፖርት ያልተደረጉ አያሌ ጥቃቶች ሳይካሄዱ አይቀርም የሚል ስጋትን ተመርኩዞ ነው።
ሊዛ ማክዶናልድስ ከቤት ውስጥ ጥቃት ሸሽታ ቤቷን ለቅቃ በወጣችበት ወቅት ለባንክ አካውንት አልባነት ጭምር በመዳረጓ ራሷን በገንዘብ የምትደግፍበት አማራጮችን በማጣት እንደምን ተቸግራ እንደነበር ስትናገር፤
"ቤቴን ለቅቄ በወጣሁ ወቅት ኪሴ ውስጥ የነበረኝ ገንዘብ $33 ዶላርስ ብቻ ነበር። እኖርበት የነበረውን የመኖሪያ አድራሻ መጠቀም ስላልፈልግሁ የባንክ አካውንት መክፈት አልቻልኩም። ለጊዜው ተጠልዬ ያለሁት የቤት ውስጥ ጥቃት ሰለባዎች መጠለያ ውስጥ ነው። ያንንም አድራሻ መስጠት አልወደድኩም። አድራሻ አልባ ሆንኩ። ባሕር ማዶ ያሉ ጓደኞቼ ገንዘብ እንላክልሽ ቢሉኝም ገንዘቡን የሚልኩበት አድራሻ አልነበረኝም። የባንክ አካውንቴ ገና አውስትራሊያ ከገባን ጀምሮ ከእሱ ጋር የተያያዘ የጋራ አካውንት ነው። ሴንተርሊንክም ይሁን ማን ገንዘብ ተቀማጭ ሊያደርጉልኝ የሚችሉበት አንድም መንገድ አልነበረም። ገንዘብ የሌለው ሰው፤ አማራጮች አይኖሩትም" ስትል ገልጣለች።
ይሁናን ከሐሙስ ሜይ 28 ጀምሮ ባንኮች የቤት ውስጥ ጥቃት ሰለባዎች የባንክ አካውንት መክፈት እንዲችሉ የመታወቂያ መስፈርቶቻቸውን ለውጠዋል።
በአዲሱ መሥፈርት መሠረት ተጠቂዎች የሚጠየቁት ማስረጃ ከሐኪማቸው ወይም ተጠልለውብት ካሉበት የመጠለያ ሥራ አስኪያጅ ተጠቂነታቸውን የሚገልጽ አንድ ማስረጃ ብቻ ማቅረብ ይሆናል።
ቀደም ሲል ተጥቂዎች ቢሆኑም እንኳ የባንክ አካውንት ለመክፈት 100 ፐርሰንት የመታወቂያ ነጥቦችን የሚያሟሉ መሥፈረቶችን ለማቅረብ ግድ ይባሉ ነበር።
የአውስትራሊያ ባንኮች ማኅበር ዋና ሥራ አስፈጻሚ - አና ብላይ የባንኮቹን የአሠራር ለውጥ ለተጠቂዎች ያለውን ጠቀሜታና ድጋፍ ሲገልጡ፤
"የራስ የባንክ አካውንት መኖር ለማንኛውም ሰው የፋይናንስ ነፃነት ለማግኘት ወሳኝ ነው። ከቤት ውስጥ ጥቃት ሸሽተው ለሚወጡቱ ከሥነ ልቦና አኳያ በጣሙን ጠቃሚ ነው። ለነፃነት የመጀመሪያው መወጣጫ ደረጃ ነው" ብለዋል።
ይህ በእንዲህ አንዳለም፤ የኒው ሳውዝ ዌይልስ የወንጀልና ምርምር ስታቲስቲክስ እንዳመላከተው፤ በወርኃ ኤፕሪል በፖሊስ የተመዘገቡ የቤት ውስጥ ጥቃቶች ቁጥር ካለፈው ዓመት ጋር ሲንጻጸር ዝቅተኛ ሆኖ ተገኝቷል።
ይሁንና ዋና ዳይሬክተር ጃኪ ፊትዝጄራልድ የጥቃት ቁጥሮቹ ዝቅተኛነት አስባብ ለፖሊስ ሪፖርት ያለመደረግ ጉዳይ እንደሚሆን ስጋትን የተላበሰ አመኔታ አላቸው።
በሌላም በኩል ወ/ሮ አዳምስ በማኅበራዊ መገለሉ ሳቢያ ተጠቂዎች ከአጥቂዎቻቸው ጋር 24/7 ቤት ውስጥ በመሆናቸው ሪፖርቶች ለፖሊስ ላይደርሱ እንደሚችሉና ምናልባትም በወርኃ ጁን/ጁላይ ከቤት ውስጥ ወጣ-ወጣ ማለት ሲጀመር የጥቃት ሪፖርቶች ሊያሻቅቡ እንደሚችሉ ያላቸውን ግምት ገልጠዋል።
አያይዘውም፤ ባንኮቹ የወሰዱት የአሠራር ለውጦች ወደ ተገቢ አቅጣጫ እያመራ ያለ ቢሆንም፤ ብዙ ተጨማሪ ሥራዎች ሊሠሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በእርስዎ ወይም በሚያውቁት ሰው ላይ የቤት ውስጥ ጥቃት ደርሶ ካለ 1800RESPECT [[1800 737 732]] ይደውሉ።
አጣዳፊ ከሆነም 000 ይደውሉ።
ኮሮናቫይረስን አስመልክቶ በቋንቋዎ መረጃ ካሹ sbs.com.au/coronavirus ድረገጻችንን ይጎብኙ።