በአንድ የቪክቶሪያ የእርድ ሥጋ ማዘጋጃ ፋብሪካ ውስጥ የተከሰተው ኮሮናቫይረስ ትናንት ለሊቱን ቁጥሩ ከግማሽ ደርዘን በላይ ንሮ አድሯል።
የቪክቶሪያ በጅሮንድ ቲም ፓላስ ዛሬ ማክሰኞ 17 ሰዎች ትናንት በኮቪድ - 19 መያዛቸው ተመዝግቦ ማደሩንና ያም በጠቅላላ ቪክቶሪያ ውስጥ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥርን 1423 ማድረሱን ገልጠዋል።
ከዚህም ውስጥ አሥራ አንዱ ብሩክሊን ከሚገኘው ሲዳር ሥጋዎች ፋብሪካ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ናቸው።
በፋብሪካው በተከሰተ የኮሮናቫይረስ የተጠቁ ሰዎች ቁጥርም 45 ደርሷል።
ኩባንያውና የቪክቶሪያ ዋና የጤና ኃላፊ በየፊናቸው የፋብሪካውን ሥጋ መመገብ በጤና ላይ ጠንቅ እንደማያስከትል ለሕዝብ እየነገሩ ነው።
ሁሉም 350 የፋብሪካው ሠራተኞች ሜይ 1 የኮቪድ - 19 ምርመራ የተደረገላቸው ሲሆን፤ አጠቃላይ ጽዳት እስኪካሔድና ምን ዓይነት ቀጣይ እርምጃዎችን መውሰድ እንደሚገባ እስከሚወሰን ድረስ የእርድ ሥጋ ማዘጋጃው ለ14 ቀናት ተዘግቷል።
እስካሁን ቪክቶሪያ ውስጥ በኮሮናቫይረስ 18 ሰዎች ሕይወታቸው አልፏል።

Cedar Meats Australia is seen in Melbourne, Monday, 4 May, 2020. Source: AAP
በቫይረሱ ከተያዙት 1423 ሰዎች ውስጥ 748 ወንዶችና 675 ሴቶች ናቸው።
በዕድሚያቸውም ከሕጻናት እስከ ዘጠናዎቹ መጀመሪያ ያሉ ይገኙባቸዋል።
በቫይረሱ ከተያዙት 1423 ሰዎች ውስጥ 1166 ከከተማ 218 ከገጠር ናቸው።
በአሁኑ ወቅት 12 በቫይረሱ የተጠቁ ሰዎች ሆስፒታል ውስጥ ሲገኙ፤ ስድስቱ በፅኑ ሕሙማን ክፍል የሕክምና እርዳታ እያገኙ ነው።
1311 አገግመዋል።
ቪክቶሪያ ውስጥ እስካሁን 152 000 ያህል የኮቪድ - 19 ምርመራዎች ተካሂደዋል።