አንዘፈዘፈኝ፡፡
መጀመሪያ በጆሮዬ በኩል ሽው ያለው ነፋስ የፈጠረብኝ ቅዝቃዜ ነበር የመሰለኝ፡፡
ደገመና አንቀጠቀጠኝ፡፡ እጆቼ በረዶ እንደጨበጡ መሰሉ፤ የላይኛው ጥርሴ ከታችኛው ጋር ጠብ ገጠመ - ገጭገጭ፣ ቀጭ-ቀጭ፡፡
እያረምኩት የነበረውን ዘገባ አቋርጬ ላፕቶፔን አጥፌ ከወንበሩ ተነሳሁ፡፡
መኝታ ቤት ገባሁ፤
ማንቀጥቀጡ ጨመረ - እንዴውም ባሰበት፡፡
ብርድልብስና ጋቢ ደርቤም አልቆም ሲለኝ የወቅቱ ዝናብ የፈጠረው የአዲስ አበባ አየር መቀዝቀዝ የመሰለኝን ግምት ትቼ ያች ልማደኛ ወባ ተነሳችብኝ ማለት ነው አልኩ፡፡
አምስት ደቂቃ ባልሞላ ጊዜ ራሴን መውገር ጀመረኝ፡፡
እየተንቀጠቀጥኩ ነው ፤ አሁንም አልቆምም፡፡
አሁን ደግሞ ላብ ተጨመረበት፡፡ አሁን ወባ ነው ከሚለው ግምቴ ወጣሁ - ወባ ሲነሳብኝ አልቦኝ አያውቅም፡፡
----
ቤታችን ውስጥ ባልጠበቅነው ሁኔታ ነው የገባብን፡፡ “የትመጣነቱን” ወደኋላ እያሰስን በደረስንበት መደምደሚያ መሰረት በኮሮና ቫይረስ የተያዘ ሰው (ልብ አድርጉ መያዙንም ያውቃል) ከቤታችን ውስጥ ያለች አንድ ሰው ወደምትሰራበት ቢሮ በንዝህላልነት በመምጣቱ፣ መጥቶም ማስክ ባለማድረጉ፣ በዚያም ላይ ርቀት መጠበቅ በማይቻልበት ሁኔታ ውስጥ አገልግሎቱን ተጠቅሞ መሄዱ ነው ወደቤታችን ሰተት ብሎ እንዲገባ መነሻው፡፡
እርግጥ ነው እኔን ጨምሮ አጋላጭ የስራ ቦታና ሁኔታ ውስጥ ስራ የምንሰራ የቤተሰባችን አባላት ብዙ ብንሆንም ከአንድ ዓመት በላይ በቆየው የኮሮና ዘመን ውስጥ ያደረግነው ጥንቃቄ ውጤታማ ነበር - ያለማካበድ ራሳችንንም ሆነ በዙሪያችን ያሉትን ለመጠበቅ ብዙ ተጨንቀናል፤ ጥረትም አድርገናል፡፡ አቋማችን አንድ ነበር - ኮሮናን መታገል!!!
የኔም ሆነ የቤተሰቦቼ መጠንቀቅ ብቻውን አልቦ ጥረት ሆነ - ቤታችን ገባ፡፡
እርግጥ ነው በአገራችን ቁጥሩ እያሻቀበና እንደገና እያገረሸ ስለመጣ ማንኛችንም ልንያዝ እንደምንችል አምነን ከስነ ልቡና ጦርነቱ ጋር እየተዋጋን ነው የሰነበትነው፡፡ ማንኛችን ቀዳሚ፣ ማንኛችንም ቀጣይ ተረኛ እንደሆንን ነው የማናውቀው እንጅ ልንያዝ እንደምንችል አምነናል - አለመያዝ የምንችልበትን ጊዜ አልፈናል፤ ምክንያቱም ስራ ቦታ ለብሰን የዋልነውንም ጫማና ልብስ ደጅ አውልቀን ብንገባም ፣ ልጆችን ከማግኘታችን በፊት በሳሙናና አልኮሆል ብንታጠብም ትንፋሽ ልናፀዳ የምንችልበት አኗኗር ውስጥ አይደለንም - ሰብሰብ ብለን የምንኖር ቤተ-ሰዎች ነን፡፡ በዚያም ላይ ኮሮናውን ያስተላለፈውን ሰው ያለበትን ሁኔታ ከመስሪያ ቤቷ እስከሚነገራት ድረስ ያወቀ ማንም ሰው አልነበረም፡፡
የሆነው እንዲህ ነው፡፡
ከቤተሰባችን አንዷ ብን ብን የሚል ሳል ጀመራት፡፡
ድካምና ከፍተኛ ራስ ምታት ተከተለ፡፡
እርግጥ ነው ሳል እንደጀመራት ከመሃላችን ራሷን ብትነጥልም ሳንዘገይ እንዳልቀረን መገመት አያቅትም፡፡ አዎ - ዘግይተናል፡፡ በዋዜማውና በዕለቱም ቢሆን ተነካክተናል - ትንፋሽ ተለዋውጠናል - ማዕድ ተጋርተናል፡፡
የፈራነው ደረሰ - የሸሸነው ቀረበን፡፡ የምርመራ ውጤቷ “ኮቪድ ፖዚቲቭ” ሆነ ተባልን፡፡ አለመደንገጥ አንችልም - እስከ ሁለተኛው ቀን ብን ብን ይልባት የነበረው ሳል እየባሰ፣ ራስ ህመሟ እየጨመረ፣ የመገጣጠሚያ ቁርጥማቷ እየናረ ሄደ፡፡ የምናውቃቸውን የሕክምና ወዳጆች እየጠየቅን፣ ከኮቪድ መከታተያ ማዕከል በስልክ ከሚመክሯት እያጣቀስን፣ ባህላዊውንም ዘመናዊውንም እያደረግን ማስታገሻ ታገኝ ዘንድ ብንጥርም ቀን በጨመረ ቁጥር የሚብሰውን ህመሟን በቅርብ ርቀት እየሰማንና እያየን ስንጨነቅ ዋልን፣ አደርን፡፡
ይህ በሆነና እሷ ውጤቷ በታወቀ በሰባተኛ ቀኑ ነው እኔ መንዘፍዘፍ የጀመርኩት፡፡ የእሷን ውጤት ካወቅን በኋላ ሁሉም የቤተሰብ አባል ከውጫዊ እንቅስቃሴ ተገትተን ቤት መዋል ጀምረናል፡፡ በመሆኑም ቤት ሆኘ እየሰራሁ ሳለሁኝ ነው እንዝፍዝፍ ያልኩት፡፡
-----
የወዳደቁ ቁሳቁሶችን አሰባስበንና ሸጠን ባገኘነው ገንዘብ በዋግኸምራ ዞን ከጓደኞቼ ጋር በዳስና ዛፍ ጥላ ስር ለሚማሩ ተማሪዎች በተለያዩ ሁለት ትምህርት ቤቶች የመማሪያ ክፍሎች ግንባታ ለማስጀመር የአራት ቀናት የመኪና ጉዞ አድርገን ተመልሰናል ፤ በሳምንቱ ደግሞ በመንገዳችን አቋርጠነው ሄደን ወደነበረው ወደ ላሊበላ ሄደን በከተማው ተዘጋጅቶ በነበረው የዩኒቨርሲቲዎች ፎረም ስብሰባ ለፕሬዝደንቶች ስለፕሮጀክታችን ገለፃ ለማድረግ ጉዞ አደረግን፤ በዚህ ሁሉ መሃል ደግሞ ዕለታዊ ስራዎቼን ላለማስተጓጎል ባለሁበት ሆኘ ስሰራ አመሽ ነበር - ድካምና የእንቅልፍ ማጣት ከተጫጫነኝ ሰንብቷል፡፡ ድካም ይሰማኝ ነበር፡፡
እናም እንዲያ ሲያንዘፈዝፈኝ የገመትኩት አቅሜ ስለተዳከመ ከዓመታት በፊት የያዘኝ ወባ የተነሳ፣ ወይም ታይፈስ የያዝኝ እንዲመስለኝ ቢያደርግም ከቤታችን አጮልቆ የሚያይ ኮሮና መኖሩን ግን አስረግጬ አውቃለሁ፡፡
ግን ቫይረሱ ከቻይና ተነሳ ከተባለበት ጊዜም ጀምሮ ከዚያም ኢትዮጵያ ገብቶ በይፋ ከተነገረበት መጋቢት 4 ቀን 2012 ዓም ጀምሮ ምልክቶቹን ለመረዳት የምቸገር ሰው አልነበርኩም፡፡
ከወዳጆቼ ጋር ሆኘ ከመደበኛ የጋዜጠኝነት ስራዬ በተጨማሪ “የኮሮና ጉዳይ - Corona Issues “ የሚል የፌስቡክ የቡድን ገፅ ከፍተን መረጃ ስናደርስ፣ ስናጣራና ስናሳውቅ ቆይተናል፡፡
በተለያዩ ሚዲያዎችም የገባኝን ያህል ለማሳወቅ በሚል ስሳተፍ ነበር፡፡
እኔ ከልቤ (ስለምፈራው) ስታገለው ነበር፡፡ በዚህ “ፍርሃት” በወለደው ትግል የጣና ሶሻልሚዲያ አዋርድ ሽልማትም አግኝቸበታለሁ፡፡ በሽልማቱ ወቅትም “ስለኮሮና የምፅፈው ስለምፈራው ነው” ብየ ነበር፡፡ ከልቤ እፈራው ነበር፡፡
የጓደኞቼ አይተኬ ጥረት እንደተጠበቀ ሆኖ እኔም ሆንኩ “ሞደሬተሮቹ” ለአንድ ዓመት ግድም ያለመሰሰትና መሰልቸት መረጃ ለማድረስ ስንታትር ነበር፡፡
እናም የኮሮና ምልክቶችን ለመለየት ብዙ አልሰንፍም - ቤት ውስጥ የታመመ ሰው መኖሩ ሲታከልበት ደግሞ አስቡት፡፡ ግን ወባው እንደተነሳበት ሲያንቀጠቅጠኝ መጀመሪያ የወቅቱ ቅዝቃዜ የፈጠረብኝ ብርድ፣ ቀጥሎ ደግሞ ጉዞ ስላበዛሁና እስከ አነጋግ እያመሸሁ የምሰራው ጉዳይ ስለነበረኝ በአቅሜ መዳከም ወባዬ የተነሳብኝ ወይም “ታይፈስ/ታይፎይድ” ነገር የጀመረኝ ነበር የመሰለኝ፡፡
ከማንዘፍዘፍ ወደ ከፍተኛ ራስ ህመም ሲሸጋገር፣ አንድ ሰዓት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ደግሞ እንደጉንፋን የሚመስል የአፍንጫ መታፈን ሲከተልብኝ ተረኛው እኔ እንደሆንኩ ይሰማኝ ጀመር፡፡ ጥርጣሬዬን ወደ እርግጥኛነት አሳደኩት፡፡
ወዲያውኑ ለራስ ህመሙ ማስታገሻ “ፓናዶል” ዋጥኩ፡፡
አፍንጫዬን ለጀመረኝ ሳይነስ መሰል መታፈን ደግሞ በፈላ የ “ባሕር ዛፍ ቅጠል” እንፋሎት እንድታጠን ቀረበልኝ፡፡ ብርድልብስና ጋቢዬን ተከናንቤ እየበረደኝ በጀመረኝ ላብ ውስጥ ሆኘ ታጠንኩ፡፡ ስታጠን በፈላ ውሃ ውስጥ እንደሚበርደው ሰው የሆንኩ ያህል ነበር የሚሰማኝ፡፡
ለረጅም ሰዓት የእንፋሎቱን አየር ስቤ እያስወጣሁ መተንፈሻ አካሌን ለማፅዳት ሞከርኩ፡፡ ከዚያም ክንብንብ እንዳልኩ ተጠቅልዬ ተኛሁ፡፡
እንዳይነጋ የለም ነጋ - በላብ የራሰውን ብርድልብስ ቀየርኩ፡፡ መኝታ ቤቴ ወደ ወሻባ እንድትቀየር ተወሰነ - በምርመራ እስኪረጋገጥ ብቻዬን እሆን ዘንድ ግድ ነበር፡፡
እሷ ውጤቷ እንደታወቀ “ አሲትሮማይዚን” የሚባል መድሃኒት ለሶስት ቀናት እንድትውጥ በሀኪሞች ምክር ተነግሯት ነበርና በጠዋቱ ተገዝቶልኝ እኔም መዋጥ ጀመርኩ፡፡ ይህ መድሃኒት የመተንፈሻ አካል በተለይም ጉሮሮ እንዳይበከል እገዛ ያደርጋል ስላሉ እኔም በባሕር ዛፍ እንፋሎት ከመታጠን ባለፈ ዋጥኩት ፤ ትንፋሼን ከመሸንቆር አስቀድሜ ለመከላከል ፤ ቫይረሱ ወደ ሳንባዬ ሳይደርስ በሩን ለመጠርቀም በሚል ወዲህ መድሃኒት፣ ወዲያ ባሕርዛፍ በታካይነት ደግሞ ትኩስ ነገር ፡፡
ቀን አንድ - መንዘፍዘፍና ራስ ህመም፡፡
ቀን ሁለት - ከፍተኛ ራስ ህመም፣ ከፍተኛ የጀርባና ወገብ ህመም - መጠነኛ ላብ፡፡
ቀን ሶስት - ከፍተኛ ራስ ህመም፣ ከፍተኛ የወገብ ህመም፣ ከፍተኛ ላብ፡፡
------

Source: Demeke Kebede
በሁለተኛው ቀን ከቀትር በኋላ ወደ ሀኪም ሄጄ በምርመራ ለማረጋገጥ ባስብም የህመሙ ስቃይ አይደለም ወደ ሀኪም ቤት ለማምራት ከመኝታ ቤት ወደ ሽንት ቤት ለመራመድ እንኳን ጉልበት ከዳኝ፡፡
ሶስተኛው ቀን የባሳ ጣዕር ነበር፡፡ መቆም፣ መቀመጥ፣ መገላበጥ፣ መተኛትም ሆነ መራመድ የሚከለክል ቃል መግለፅ የማይችለው ከፍተኛ የወገብ ህመም አሰቃየኝ፡፡
ናላዬ ዞረ፡፡
ተንቆራጠጥኩ፡፡
ቀድማ የታመመችው ቤተ-ሰዋችን እኔ እየባሰብኝ ሲሄድ እሷ በአንፃሩ ስቃዩ እየቀነሰላት ነበር ፤
በዚህ አጋጣሚ የቦሌ ክፍለ ከተማ የኮሮና ክትትል ባለሙያዎች ያለማሳለስ በስልክ ሲያደርጉላት የነበረውን ክትትል፣ አይዞሽታና ምክር አለማመስገን አይቻልም፡፡
ትኩስ ነገር አብዝተን እየጠጣን ነው፡፡
የሚገርመው የእሷና እኔ የህመም ስሜታችን ፈፅሞ የተለያየ መሆኑ ነው፡፡ እሷ ያስላታል፣ ይቆረጥማታል፣ የምግብ ጣዕም አትለይም፡፡ በአንፃሩ እኔ ደግሞ ምንም ሳል የለብኝም፣ መገጣጠሚያዎቼን አይቆረጥመኝም፣ የምግብ ጣዕም አሳምሬ እለያሁ፡፡
የራስ ህመምና የወገብ ህመሙ ሁለታችንም ላይ የሚታይ ነበር፡፡ ከፍተኛ ላብ ግን እኔ ላይ ብቻ ነበር የነበረው፡፡
-----
አራተኛው ቀን ደረሰ፡፡
ስቃዩ የኔ እየባሰ - የእሷ እየቀነሰ መጣ፡፡
አሁንም አሁንም ምግብ እመገባለሁ - እየተንቆራጠጥኩ ስመገብ አልፎ አልፎ እንደ ልጅነቴ ከአፌ እያፈተለከ የሚደፋም አልጠፋም፡፡
ቤተሰቦቼ ከመጨነቃቸው ብዛት አንድ ጊዜ ዝንጅብል፣ ሌላ ጊዜ ሎሚና ብርቱካን፣ ደግሞ ሌላ ጊዜ ኑግና ኦቾሎኒ፣ ሲያሰኛቸው ሾርባ እያዘጋጁና እያፈራረቁ ትኩስ ትኩሱን ያቀርቡልኛል - እሱን እልፋለሁ፡፡ ትኩስ ነገር የምጠጣበት ከንፈሬ ተንገረገበ፤ ምላሴ ቅቅል ስጋ በአፌ የማላምጥ እስኪመስለኝ ነፈረ፡፡
ጉሮሮዬ እስካሁን ደህና ነው፡፡ ምንም የህመም ስሜት የለውም፡፡
ደረቴም አልተወጠረም፡፡ ትንፋሼም ጥሩ ነው፡፡
ቁርጥማትም የለም፡፡
በመጋዝ የወገቤን መለያያ እየሰነጠቁብኝ ያሉ እስኪመስለኝ ድረስ የወገብ ህመሙ ብቻ ነው ያየለብኝ፡፡
የምር ስቃዩን መቋቋም አቃተኝ - እንባ ሳላቀር አልቀረሁም፡፡
ቤተሰብ ተጨነቀ - እሷ አንፃራዊ መሻሻል ብታሳይም ቅሉ የኔ እያደር ባሰ፡፡ እናም ቤቱ በጭንቅ ተሰቀዘ፡፡ አንድም የኔ ስቃይ እየበዛ መምጣት፣ ሁለትም ቀጣይ የቤተሰብ አባል ማን ይሆን በሚል ቤተሰብ ከታመሰ ሰነበተ፡፡ እንደማይቀር አምነን በስነ ልቡና እንዘጋጅ ስንባባል እንዳልከረምን ሲከሰት ቤተሰባችንን ወኔ ከዳው፡፡
በቅርብ የሚታወቁ ሰው መሞታቸው መሰማቱ ጉልበት አራደ፡፡
ፈራን፡፡
በአፋቸው “አይዞህ” ይሉኛል - እኔ ግን በአይናቸው ላይ መሸበራቸው ይነበበኛል፡፡
በዚህ መሃል የሔራን ታናሽ ኄኖን አመመኝ አለች፡፡ አምስት ዓመቷ ነው፡፡ ቀድማ አፀደ ህፃናት መግባቷን ምክንያት አድርገን፣ ስስ ነገር ስለሆነች በሚል ኮሮናን ፈርተን ከትምህርት ቤት አስቀርተናል - አቋርጣ ቤት እንድትውል ፈርደንባታል፡፡
ዳሩ ከትምህርት ቤት ብናስቀራትም ቤት ሰተት ብሎ መጣባታ !
ይብሱኑ ከወገቤ ስቃይ በላይ “አመመኝ “ ማለቷ ሰቀዘኝ፡፡
“ምንሽን ነው የሚያምሽ” አልኳት ህመሜን አምቄ፡፡ ብዙዎቹን የኮሮና ምልክቶች በልጅ አንደበቷ ስትነገረኝ መስማት ትንፋሽ ቀጥ ያደርጋል፡፡
ጠንካራ ነኝ ብልም ልፍስፍስነቴ የገባኝ ይህን ጊዜ ነው፡፡
ልጆችን እምብዛም እንደማይጎዳ ባውቅም የሚነጥቀኝ መሰለኝ - ባባሁላት፡፡
አክስቷ እያንከበበች ወደ ክሊኒክ ይዛት ሄደች፡፡
በቤታችን የሆነውን ሁሉ ነግራ “ቼክ” ተደረገች፡፡ የምግብ ፍላጎት መቀነሷ፣ ትኩሳቷና ደረቷ አካባቢ አመመኝ የምትለው ከጉንፋን መሰል ሳሉ ጋር ተደማምሮ አንድ ነገር እንዳትሆን በሚል ፍርሃት ቤታችን ተጨነቀ፡፡
“የኦክስጅን ሌቭሏ ጥሩ ነው፡፡ ምግብ አስገድዳችሁም ቢሆን አብሏት፤ ሙቋት ከመጠን ያለፈ አይደለም፡፡ ስለዚህ ሁኔታዋ አያሰጋም አትጨነቁ፤ ከሁለት ሶስት ቀን በኋላ ይለቃታል” የሚል ደርዘኛ ምክሩን ለግሶ ላካት፡፡
ወዲህ እኔ እንቆራጠጣለሁ፤ ወዲያ ኄኖንን በስስት አያለሁ፡፡
በአካልም በአዕምሮም ጭንቅ ውስጥ ገባሁ - የእናቷን ድንጋጤ ልተወው፤ በጥቅሉ ቤተሰቡም ተኮራመተ - ዘመድ አዝማድ ተጨነቀ፡፡
----
አራተኛው ቀኔ ላይ የወገብ ህመም ማስታገሻ ከፋርማሲስት ዘመዳችን ተላከልኝ፡፡
የሚደንቅ ነው - በወሰድኩት ሰላሳ ደቂቃ ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ቀጥ አለ፡፡
ማመን አልቻልኩም፡፡ በዚህ ፍጥነት ወገቤ ሰላም ይሆንልኛል ብዬ ለማመን ተቸገርኩ - ግን እውነት ነበር፤ ስቃዩ ብን ብሎ ጠፋልኝ፡፡ ተ-መ-ስ-ገ-ን !!
ራሴን ግን ይጠዘጥዘኛል - ላቡም ሄድ መለስ ይልብኛል፡፡
በአምስተኛው ቀን ሰኞ ዕለት በጠዋት ለምርመራ ሄድኩ - የመረጥኩት ሰፈራችን ካለው ጤና ጠቢያ መሄድ ነበር፡፡ ተሰልፌ ተመርምሬ መጣሁ፡፡
በአፍንጫዬ አስገብተው ሳምፕል የወሰዱበት “ዘንግ” ግን ዘገነነኝ፡፡ በአፍንጫዬ ሲገባ ወደ ውስጥ ዘልቆ በዓይኔ የወጣ ያህል ነበር ያመመኝ - የምር ለመናገር ቀፋፊና የሆነ ብስጭትጭት የሚያደርግ ስሜት የሚፈጥር ነበር፡፡
እያጉተመተምኩና በድካም የዛለ እግሬን እየጎተትኩ ቤት ደረስኩ፡፡ ጠርቅሜው የሰነበትኩት ስልኬን ስከፍት ታዋቂው አርቲስት መስፍን በኮሮና ሞመቱን ፌስቡክ ላይ አነበብኩ፡፡
በድንጋጤ ተንዘፈዘፍኩ፡፡
ያ የመጀመሪያው ቀን መንቀጥቀጥ ተመልሶ መጣብኝ፡፡
ልብ አድርጉ በሰቆጣና በላሊበላ ጉዞዬ መሃል ባሉት ቀናት በአንዱ ዕለት ተገናኝተን ነበር፤ እኛ ቤት ኮሮና ከመግባቱ ሶስት ሳምንት በፊት ግድም፡፡ ድንበሯ ሆስፒታል ጥግ በሚገኝ ሬስቶራንት፡፡ እሱ ከጓደኞቹ እኔም ከወዳጄ ጋር ሆነን ጎን ለጎን በሚገኝ ጠረጴዛ በየፊናችን ምሳ ተመግበናል፡፡ በፈገግታ ሰላም ተባብለናል፡፡
መስፍኔ ከጓደኞቹ ጋር እየተመገበ ፣ ሲስቅና ሲጫወት ነበር፡፡ ከራስ ፀጉሩ በተለዬ ጺሙ አድጎ በዚያም ላይ ሸብቶ ስናየው እንዲሁም አብረውት የነበሩት አርቲስቶች ስለነበሩ ከስራ ተመልሰው ወይ ወደ ስራ ሊሄዱ እንደሆነ ያሳብቅባቸው ነበር፡፡
ከሶስት ሳምንት በፊት በቅርብ ርቀት ሲፍለቀለቅ ያየሁት መስፍኔ በኮሮና ምክንያት ያውም በታመመ በአጭር ቀናት ወደማይቀርበት ዓለም መሄዱን ሳነብ ወገቤ ቢንቀጠቀጥ አይፈረድብኝም፡፡ ቅንደቤን ቢያልበኝም ልክ ነበርኩ፡፡
ቀጣዩ ሟች እኔ ነኝ አልኩ፡፡
አስቀድሞ በሶሻል ሚዲያ ንቁ ተሳትፎው የምናውቀው ዶክተር አበበ ሐረገወይን ጣዕር ላይ መሆኑን ከኤካ ኮተቤ ሆስፒታል የለቀቀው “የአይሲዩ” ውስጥ ፎቶ ሲረብኝ ሰንበቶ ነበር፤ መስፍን ሲሞት ሀሞቴ ፈሰሰ፡፡
አንድም ደመነፍሳዊ ፍርሃቴ፣ ሁለትም ትግሌን እንደጀመርኩት ልቀጥለው ብዬ “ የታገልኩት ኮሮና እየታገለኝ ይሆን ወይ” በሚል በይፋ መታመሜን ሶሻል ሚዲያ ላይ አሳወቅሁ፡፡
ላብ ያጠመቀውና ስቃይ ያደቀቀውን ፎቶዬን ለጥፌው ስለነበር ቤተዘመድና የፌስቡክ ወዳጅ ጓደኛ ከውጭም ከአገር ውስጥም የ”አሁን እንዴት ነው” ጥያቄ ያዥጎደጉድ ጀመር፡፡ እርግጥ ነው ከሆነ በኋላ “ኮሜንት” ያነበብኩትንና በቤተሰብ የተነገረኝን እንጅ እኔማ ተንቀጥቅጬ እንደኤሊ ብርድልብሴ ውስጥ ከተሸጎጥኩ ቆየሁ፡፡
----
ስምንተኛው ቀን!
ከቫይታሚኖችም ከምግብ በገፍ እየወሰድን ነው፡፡
እሷ “ኦልሞስት” አገገመች፡፡ ጭራሽ በመስኮት እየተያየን እኔን አፅናኝ ሆነች፡፡ ቤታችን ሆስፒታል መስሏል፡፡
እኔ ራሴን በአለፍ ገደም ጠቅ ጠቅ ቢደርገኝም የወገብ ህመሙ ድራሹ ስለጠፋልኝ ተመስገን ማለት ጀምሬያለሁ፡፡ ከምንም በላይ የህፃኗ ኄኖን ደህና መሆን ሃሳቤን አቀለልኝ፡፡ ሌላው መልካም ነገር ተጨማሪ የቤተሰብ አባል እስካሁን አልታመመም፡፡
----
ዘጠነኛው ቀን፡፡
ሰኞ ያደረኩት ምርመራ ውጤት ሀሙስ ዕለት ተነገረኝ፡፡ “ኮርንነሃል” ተባልኩ፡፡
“ማገገም ስጀምር ነው እንዴ የምትነግሩኝ” ብዬ ለደወለችልኝ ባለሙያ ተናገርኩ - ፎገርኩ፡፡ “ሰሞኑንማ ፈጥኗል እኮ” ብላ አሳቀችኝ፡፡
በርከት ያሉ ለጥንቃቄና ለመዳን መውሰድ የሚገቡኝን ነገሮች ሁሉ መካክራኝ ተሰናበትን፡፡
ከአፍታ ቆይታ በኋላ ወደ ሶሻል ሚዲያ ጎራ አልኩ፡፡
ውጤቴ “ኮሮና” እንደሆነ አወጅኩ፡፡
ሞትን ቢያመልጡ ከመሞት ትንሽ ዝቅ የሚለውን ስቃዩን ግን ማለፍ እንደማይቻል ፣ በዕለታዊው የጤና ሚኒስቴር የኮሮና ሪፖርት ውስጥ የኔም መካተቱን ተናገርኩ፡፡ ማድረጌም ልክ ነበር - አሁን ራሱ ይህንን ለመፃፍ ሳስታውሰው ያንገፈግፈኛል የስቃዩ መጠን፡፡
እኔም ሆንኩ ቤተሰባችን ዕድለኞች ሆነን እንጅ የመጣብን አመጣጥ ክፉኛ ነበር፡፡
ከሀኪሞችና ታመው ከዳኑ ወዳጆቼ በተነገረኝ መሰረት የእኔ ህመም ቀላል የሚባለው አይነት ነው አሉ፡፡ እኔ ደግሞ ለአራት ቀናትም ቢሆን የተሰቃየሁትን ሳስበው ያንገፈግፈኛል፡፡ የኔ ቀላሉ ከተባለ ከባዱን ማሰብ የአንባቢ ፋንታ ነው - ሞት ደግሞ አፉን ከፍቶ እየጠበቀ መሆኑ ሳይዘነጋ፡፡
---
መወሰድ ነበረባቸው ያልናቸውን ሁሉ ነገሮች ወስደናል፤ እዚህ የሚጻፉም የማይጻፉም፡፡
አድርጉ የተባልነውን አድርገናል፤
ምግብና ትኩስ ነገር በሚገባ ተጠቅመናል፤
በቻልነው አቅም የሀኪም ምክር ሰምተናል፤ አካላዊ እንቅስቃሴም አድርገናል፡፡ የፈጣሪ ፈቃድ ታክሎበት ቤታችን ካረበበበት ጭንቀት ወደነበረበት እፎይታ ተመልሷል፡፡
እኔም ስለዳንኩ ወደ መደበኛ ስራዬ ተመልሻለሁ፡፡
አንድ ነገር ግን ልበል - ሞት አድፍጧል፤ ስቃይ አፍጥጧል፡፡ ኮሮና ከያዘ ሳያፈዳይ አይለቅም - ከሆነለት ስልቦን አንቆ ይፈጠርቃል፡፡ ኮሮና ጉንፋን አይደለም - ኮሮና ያው ኮሮና ነው! ክፉ ነው ያሰቃያል - ወይም ይገድላል፡፡ እርስዎ ከሁለቱም ማምለጥ ይችላሉ ፡፡ ምናልባት ቢያዙ ደግሞ ሳይሸበሩ በአጠገብዎ ተይዘው የዳኑ ሰዎች ያደረጉትን ተሞክሮ ይተግብሩ፤ በሀኪሞች ትዕዛዝ ይመሩ፡፡
ልክ እንደኔ ያሸንፉታል፡፡
አዎ ኮሮናን አስቀድሜ ታገልኩት፣ ጊዜ ጠብቆ አድፍጦ ታገለኝ፣ ግን አሸነፍኩት!!

ከዳንኩኝ በኋላ Source: Demeke Kebede
አሁንማ በእጥፍ እታገለዋለሁ!!
ቱ!
የታባቱ!!