የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አገራዊ ጥሪ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወቅታዊ የኢትዮጵያ ጉዳዮችን አስመልክተው ለኢትዮጵያውያን ያስተላለፉት አገራችንን በጋራ እንታደግ መልዕክት።

PM Abiy Ahmed address to the nation on COVID - 19

PM Abiy Ahmed Source: PMO

ውድ የሀገሬ ሕዝቦች፣

የተከበራችሁ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ሲቪል ማህበራትና የሀገር ሽማግሌዎች፣ ክቡራትና ክቡራን

 ባለፉት ጥቂት ወራት በመላው ዓለም ተሠራጭቶ በሀገራችን ኢትዮጵያም ልዩ ልዩ ሀገራዊ እንቅስቃሴዎችን ባስተጓጎለው የኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ወቅቱን የሚመጥኑ ተግባራት በየአቅጣጫው ሲከወኑ መቆየታቸው ይታወቃል። ውሳኔ ከሚሹ ጉዳዮች መካከል ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫን የተመለከተው አጀንዳ አንዱና ዋነኛው ሲሆን  ወራትን በፈጀ ሂደት ውስጥ አልፎ ከውሳኔ ላይ ደርሷል።

እንደሚታወቀው ሕገ መንግሥታችን ምርጫ በየአምስት ዓመቱ መደረግ እንዳለበት ደንግጓል። በሌላ በኩል ወረርሽኙ ምርጫውን ለማካሄድ የሚያስችሉ የዝግጅት ሥራዎችን አስተጓጉሏል፡፡ ለዚህ ሁኔታ መፍትሔ ለመስጠት ሕገ መንግሥታዊ አካሄድ ተከትሎ የፌዴሬሽን ምክር ቤት፥ የቀረበለትን የሕገ መንግሥት ትርጉም ጥያቄ ተመልክቶ ምላሽ ሰጥቷል። ጉዳዩን የመመልከት ሥልጣን ያለው ምክር ቤት ምርጫውን ያራዘመው ጉዳይ ተገትቶ ቀጣይ ምርጫ እስኪካሄድ ድረስ ሁሉም የፌደራልና የክልል ምክር ቤቶች ሥራቸውን እንዲቀጥሉና ከዘጠኝ እስከ አሥራ ሁለት ወራት ባለ ጊዜ ውስጥ ምርጫ እንዲካሄድ ወስኗል፡፡

ለገጠመን ሕገ መንግሥታዊ ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ያሉንን ተቋማት፣ ያሉንን ሕግጋት እና ያሉንን ባለሙያዎች በአግባቡ እንድንጠቀም ከዚህ ቀደም ባልታየ መልኩ በር የከፈተ ሂደት ሲሆን የሀገራችን ዴሞክራሲ ራሱን በራሱ እያጎለበተ ለመሄድ የሚችል መሆኑን በግልጽ አሳይቷል።

ይህ ክስተት የወቅቱን ፈተና ለማለፍ ከማገዝ ባለፈ ነገሩን በትክክል ካጤንነው አጋጣሚው እንደ ሀገር ዴሞክራሲን ለመለማመድ እንድንችል አንድ ርምጃ ወደፊት የገፋን ትልቅ እድል ነው ማለት ይቻላል።

የኮሮና ወረርሽኝ ባሁኑ ሰዓት የማያስጨንቀው ሀገር የለም። በኢትዮጵያም አደጋው እየሰፋ መጥቷል። በየጊዜው የሚወጡት መረጃዎች እንደሚያሳዩት ከሆነ በኮሮና የሚጠቁትና የሚሞቱት ዜጎቻችን ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል። በተለይም በመጭው ክረምት ቁጥሩ ከዚህም የበለጠ ሊያሻቅብ እንደሚችል ይገመታል። እንደሚታወቀው በሽታው የተወሰኑ አካባቢዎችን ለይቶ ወይም ጥቂት ሰዎችን ብቻ መርጦ የሚያጠቃ አይደለም፤ ለሁላችንም የመጣ፣ እያንዳንዳችንን ሊያጠቃ የሚችል አደገኛ ወረርሽኝ ነው። ፈተናው የመጣው ለሁላችንም እንደመሆኑ መጠን መዋጋት የሚገባንም በጋራና በሁሉም አቅጣጫ መሆን ይገባል። በአንድ ግንባር ተዋግተን ኮሮናን እንረታዋለን ማለት ዘበት ነው። ቢያንስ ቢያንስ ሶስት ግንባሮች ሙሉ አቅማችንን አሟጥጠን መታገል ይገባናል።

አንደኛ - በጤናው ዘርፍ የጀመርናቸውን እንቅስቃሴዎች አጠናክረን በመቀጠል ሲሆን፥ የበሽታውን መስፋፋት እንዲቀንስ ከማድረግ ባልተናነሰ ታማሚዎች እንዲያገግሙ ማስቻል ይጠበቃል።

ሁለተኛ - በኢኮኖሚው ዘርፍ የተጋረጠብንን አደጋ በመቀነስ ሲሆን ወረርሽኙ በፈጠረው ዓለም አቀፋዊና ሀገራዊ ሥጋት ምክንያት ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች መቀዛቀዛቸው ምጣኔ ሀብታችን ላይ ከፍተኛ ጫና እንዳይፈጥሩብን ከበፊቱ በተለየ ልዩ ልዩ ዘዴዎችን ቀይሰን በመንቀሳቀስ ሀገራዊ ፐሮጀክቶችን ማጠናቀቅ።

ሦስተኛ - ከታሪክ እንደምንማረው ወረርሽኞችን ተከትሎ ረሃብ የመከተላቸው እድል እጅግ ከፍተኛ ነው። ከዚህም በተጨማሪ በወረርሽኙ ዓለማቀፋዊነት ምክንያት ከውጭ የሚመጡ የምግብ ድጋፎች ሊቀዛቀዙ፣ በውጭ ምንዛሬ እጥረት ምክንያትም የምግብ ግዥዎች ሊቀንሱ ይችላሉ። ስለሆነም ወረርሽኙ የአርሶ አደሮቻችንና አርብቶ አደሮቻችን ዐቅም በማዳከም የምግብ ምርቶች ላይ ማሽቆልቆል እንዳያጋጥመን ምን መደረግ እንዳለበት ስልቶች መንደፍ ያስፈልጋል፡፡ ለአርሶ አደርና አርብቶ አደር ዜጎቻችን የተለየ ትኩረት ሰጥተው ምርታማነትን እንዲጨምሩ ለማስቻል ከወዲሁ እገዛዎች መጀመር አለባቸው።

ከእነዚህ ጉዳዮች አኳያ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሰሞኑን ያሳለፈው ውሳኔ ባንጻራዊነት ትኩረታችንን ለብዙዎቹ ችግሮቻችን እንብርት ወደሆነው ወደ ኮሮና እንድናደርግ ይረዳል፡፡ ማንኛውም ሀገራዊ ነገር የሚደረገው ለሕዝብ ነው። ሕዝብ ሳይኖር ለሕዝብ የሚደረግ ነገር አይኖርም። የፌዴሬሽን ምክር ቤት በምርጫና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ የሰጠው የእፎይታ ጊዜ ለሕዝብ ደኅንነት የተሰጠ ጊዜ እንጂ ለፓርቲዎች የተሰጠ ጊዜ አይደለም። ውሳኔው ያስፈለገው ለሕዝቡ ደኅንነት እንጂ ለመንግሥት አይደለም። ምርጫውን ማራዘም ያስፈለገው ለምርጫ ሲባሉ በሚከናወኑ ኩነቶች ምክንያት የሚፈጠር አደጋን ለመቀነስ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር መንግስት ለውሳኔው ተግባራዊነት የበኩሉን ሚና እንደሚጫወት ከወዲሁ ለመግለጽ እወዳለሁ፡፡
ሕዝብ ሳይኖር ለሕዝብ የሚደረግ ነገር አይኖርም። የፌዴሬሽን ምክር ቤት በምርጫና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ የሰጠው የእፎይታ ጊዜ ለሕዝብ ደኅንነት የተሰጠ ጊዜ እንጂ ለፓርቲዎች የተሰጠ ጊዜ አይደለም።
በኢትዮጵያ ውስጥ ዴሞክራሲ እንዲያብብና ሀገራዊ መግባባት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ገዥው ፓርቲ በቀጣይ ጊዜያት በዋና ዋና ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በውይይትና በምክክር መሥራቱን ይቀጥላል። ምንም እንኳ በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ የሚኖረን አመለካከት አንድ ዐይነት ባይሆንም ያለችን ሀገር ግን አንድ ናት። ለአንዲቷ ሀገራችን ስንል በሰከነ፣ በሠለጠነና ነገን አርቆ በሚያይ በሳል ስሜት ውይይትና ምክክር ማድረጋችንን አናቋርጥም።

በተለይም የሀገራችንን መጻዒ ዕድሎች በሚወስኑ ዋና ዋና ጉዳዮች ዙሪያ የጋራ መግባባት ላይ እየደረስን ነገሮችን ማስተካከል ይጠበቅብናል፡፡ አሁን የትኛውም ተግባር ለአንድ የተወሰነ አካል ተጠቅልሎ የሚሰጥበት ወቅት አይደለም። ኮሮና በኢኮኖሚው ዘርፍ ላይ እያሳደረ ያለውን ጫና የመቀነስ ኃላፊነት የሁላችንም ነው። የሥራ ፈጠራን ማበረታታት፣ አዳዲስ የልማት ዕድሎችን መጠቀም፣ ግብርናችን ከዚህ በፊት ባልተጓዘባቸው መንገዶች ሄዶ ምርትና ምርታማነትን እንዲጨምር ማስቻል፣ አምራች ኢንዱስትሪው ከውጭ የሚመጡ ሸቀጦችን ሊቀንስ በሚችልበት መንገድ ዐቅሙን አሟጥጦ እንዲያመርት መደገፍ፣ አማራጭ የፋይናንስ ምንጮችን ማፈላለግ የእያንዳንዳችን የቤት ሥራ በመሆኑ በሐሳብ፣ በስትራቴጂና በልዩ ልዩ መንገዶች የየበኩላችንን ማበርከት ይጠበቅብናል። ይህ ጉዳይ ሀገርን እንደ ሀገር፣ ሕዝብንም እንደ ሕዝብ ለማኖር የሚሠራ ሀገራዊ ሥራ በመሆኑ ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች በየዘርፋቸው ሊረባረቡበት የሚገባ ከፈተና መውጫ መንገዳችን ነው።

አሁን ዳር ቆሞ የመመልከቻና ጣት የመጠቋቆሚያ ጊዜ ላይ ባለመሆናችን የጋራ ክንዳችንን አጠንክረን መፍትሔ መፈለግ ይኖርብናል። ከዚህ ጎን ለጎን መጭውን ምርጫ ነጻ፣ ዴሞክራሲያዊ፣ ሰላማዊና ተአማኒ ለማድረግ በጋራ በቂ ዝግጅት እያደረግን እንቆያለን። አንዱ ዋናው ዓላማችን መጭውን ምርጫ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵውያን የሚመጥን ማድረግ መሆኑ ሊሠመረበት ይገባል። በዚህ ረገድ ከፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከሲቪክ ማኅበራት፣ ከሃይማኖት ተቋማት፣ ከታዋቂ ሰዎች፣ ከሚዲያ ልሂቃን፣ ከሀገር ሽማግሌዎች፣ ከጎሳ መሪዎችና ከሌሎች ከሚመለከታቸው ሁሉ ጋር፤ የኮሮና መከላከል ርምጃችንን በማያውክ መልኩ በመወያትና በመመካከር እንሠራለን። ይኽን የምናደርገው እንዲሁ አደረግን ለማለትና ለይስሙላ መሆን የለበትም። ሁላችንም በታሪክ ፊት ድምጻችን ጎላ ብሎ የምንናገረው በአንደበታችን ሳይሆን በተግባራችን ነው። ስለሆነም እያንዳንዳችን ለተግባራዊነቱ ከወዲሁ ቆርጠን እንድንነሳ ጥሪዬን አቀርባለሁ።
አንዱ ዋናው ዓላማችን መጭውን ምርጫ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵውያን የሚመጥን ማድረግ መሆኑ ሊሠመረበት ይገባል።
በመንግሥት በኩል ይሄንን አጋጣሚ ሀገርና ሕዝብን ለማዳን ግዳጅ እንደተሰጠው፣ ኃላፊነት እንደ ተጣለበት አድርጎ ይቀበለዋል። እንደ ገዥ ፓርቲ ይሄንን ጊዜ እንደ ተጨማሪ የሥልጣን ዘመን ሳይሆን፥ እንደ ተጨማሪ የኃላፊነት ዘመን እናየዋለን። የፌዴሬሽን ምክር ቤት ያሳለፋቸውን ውሳኔዎች ሁላችንም በዚህ መልኩ ከተቀበልን፣ ምክር ቤቱ የሕዝብን ደህንነት በበቂ ሁኔታ ለማስጠበቅ በማለም እንዳሳለፋቸው አድርገን ካመንን በእርግጥም ከፊታችን መልካም ተግባር የምንፈጽምበት ጊዜ ተዘርግቷል። እናም የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የኢኮኖሚ ተዋንያን፣ ሲቪክ ማኅበራት፣ የሚዲያ ልሂቃን፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና በየዘርፉ ጠቃሚ አስተዋጽዎችን የምታበረክቱ አካላት በሚከተሉት ዋና ዋና ጉዳዮች ዙሪያ የበኩላችሁን ለመወጣት ዝግጁ እንድትሆኑ እጠይቃለሁ፡-
እንደ ገዥ ፓርቲ ይሄንን ጊዜ እንደ ተጨማሪ የሥልጣን ዘመን ሳይሆን፥ እንደ ተጨማሪ የኃላፊነት ዘመን እናየዋለን።
አንደኛ፥ የኮሮናን ወረርሽኝን በቁጥጥር ሥር ለማዋል፤

ሁለተኛ፥ ከፊታችን የተጋረጠውን የኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ቀውስ ከፍተኛ ጉዳት ሳያደርስብን በብቃት ለመሻገር፤

• ሦስተኛ፥ ሊደቀኑብን በሚችሉ እንደ ረሃብና የምግብ ምርት እጥረት የሚያስከትላቸው አደጋዎች፣ እና ከሉዓላዊነት ጋር የተገናኙ ጥቃቶችን በቁርጠኝነት ለመመከት፣ እንዲሁም፤

• አራተኛ፥ ቀጣዩን ምርጫ ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊ፣ ነጻና ተአማኒ ለማድረግ በጋራ እንድንሠራ ጥሪ አቀርባለሁ።

ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትሩር!!

ፈጣሪ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿን ይባርክ!

 


Share

Published


Share this with family and friends