1 መግቢያ
የኩሽና የኩሸቲክ ጉዳይ የፖለቲካ መነጋገሪያ ከሆነ ሰነበተ። እውነታውን መርምሮ ከማወቅ ይልቅ እዚህም እዚያም ለግዜያዊ ፍጆታ በሚመስል የታሪክ መሰረት የሌለው ትርክት በዘፈቀደ ሲሰጥ ይስተዋላል። ይህን ጉዳይ ፈረንጆች ሳይቀሩ ታዝበውታል፤ “ዛሬ የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች የኩሸቲክ ህዝብ ከሴሜቲክ ህዝብ በላይ የሀገሪቱ ባለመብት እንደሆኑ አጥብቀው ያሰምሩበታል” (ብሬየር 2007:460)። ለዚህ ሶስት መሰረታዊ ምክንያቶችን ማቅረብ ይቻላል። አንደኛ፣ የዘመናችን የኩሸቲክ ቋንቋ ተናጋሪዎችን ከጥንታዊ የኩሽ ህዝቦች ጋር አለቦታቸው ማዛመድ፤ የቋንቋና የህዝብ ግንኙነትን በውል አለመለየትና ስለቋንቋዎቹ የቅርብ ግዜ ጥናቶች የደረሱብትን በአግባቡ አለመረዳት ችግር ነው። ሁለተኛው፣ በቀደምት ፀሀፊዎች የቀረቡ ግልፅ ያልሆኑ፣ በተወሰነ ደረጃም የሚያምታቱና አሳማኝ ታሪካዊ መረጃ የሌላቸው፣ እንዲሁም ታሪክና እምነት አለመንገዳቸው እየተደባልቁ የቀረቡባቸው ትርክቶች መቅረባቸውም ጭምር ሊሆን ይችላል። ሶስተኛው፣ ስለኩሽ ስርወመንግሥትና ስለኩሸቲክ ቋንቋዎች ቀደም ባሉት ግዜያት ብዙም አለመታወቁ ነበር። ስለኩሸቲክ ቋንቋዎች የእርስበርስ ግንኙነትና አጠቃላይ የዘር ምደባ በበቂ ሁኔታ አይተወቅም ነበር። አሁንም በአርኪ ሁኔታ ታውቋል ማለት አይቻልም። ለዚህ የተለያዩ ድምዳሜ ላይ የደረሱ የቅርብ ግዜ ጥናቶችን ማየቱ ብቻ በቂ ነው። ስለጥንታዊው የኩሽ ስርወመንግሥትም ያለው ሁኔታ ተመሳሳይ ነው። የግብፅ ታሪክ ጥላ የሆነበት ይመስላል። ስለዚህ ስርወመንግሥት አሁንም ብዙ ታውቋል ማለት አይቻልም። ለዚህ በርካታ ምክንያቶች አሉ። አንደኛው፣ ፅሁፍ በኩሽ ስርወመንግሥት የጀመረው ዘግይቶ መሆኑና እሱም ቢሆን ይዘቱ አለመታወቁ ነው። ሁለተኛው ዘረኝነት ነው። የኩሽ መንግስት በማያጠያይቅ የጥቁር ህዝብ ታሪክ በመሆኑ ይህን ለማጥናት በቀደሙት ግዚያት ብዙም ተነሳሽነት አለማሳየት ነበር። በርግጥ ከቅርብ ግዜ ጀምሮ በርካታ ጥናቶች እየቀረቡ ይገኛል።
ታሪክ ተረት አይደለምና ታዳሚን ለመሳብ እያጣፈጡ፣ ሲያሻም እየለወጡ ወይም እያዛቡ ለማቅረብ የሚያስችል መድረክ የለውም። በታሪክ ስም የቀረቡ ስራዎች ሁሉ ታሪክ ሊሆኑ አይችሉም። ሰነድና ማስረጃ የሌለው ስራ ጎራው ከታሪክ አይደለም። በሰነድና በማስረጃ የቀረቡ የታሪክ ስራዎች እንኳ ተጨማሪ ሰነድና ማስረጃ ሲገኝ፣ ውስጣቸው እየተመዘነ የሚሻሻለው ተሻሽሎ፤ የሚለወጠው ተለወጦ ይፃፋል። የተረት ዋንኛ መመዘኛው ውበቱ ሲሆን፣ የታሪክ ግን እውነታ ነው። በቋንቋዎች መሀከል ያለ ዝምድናም ከስያሜ መመሳሰል ብቻ ተነስቶ የሚፈረጅ ሳይሆን፣ ራሱን በቻለ ሳይንሳዊ መንገድ ተጠንቶ የሚወሰን ነው። ልክ እንደታሪኩ ስራ ተጨማሪ ማስረጃ ሲገኝ በአንድ ወቅት የነበረ አስተሳሰብ/ምደባ በሌላ ወቅት የማይሻሻልበት ወይም ሙሉ በሙሉ የማይሰረዝበት ምክንያት የለም። በዚህ መጣጥፍ ወደፖለቲካው ዝርዝር ሳንገባ፣ ከስነልሳንና ከታሪክ አንፃር በኩሽና ኩሸቲክ ላይ ጠቅለል ያለ ትንታኔ ለማቅረብ እንሞክራለን። ሰፊ ቦታ የለንምና የኩሽን አጠቃቀም ከጥንት እስከዛሬ ምን እንደሚመስል ለማሳየት ስንሞክር በጣም ባጠረ መልክ ነው። ዋናው አላማችን ኩሽ ወይም የዚህ ዝርያ ቃል በሆኑት ስያሜዎች ስለሚጠቀሱት ህዝቦች እና ቋንቋዎች እንዲሁም ስለጥንታዊ የኩሽ ስርወመንግሥት ጠቅለል ያለ ግንዛቤ ማስጨበጥ ነው።
2 ኩሽ
ኩሽ ጥንታዊ ቃል ነው። ይህ ቃል በመፅሀፍ ቅዱስ እንዲሁም በጥንታዊ ግብፆች ስራዎችም ተጠቅሶ ይገኛል። እስካሁን ባለን መረጃ፣ በግብፅ ኩሽ የሚል ቃል (ወይም የዚህ ተመሳሳይ ቅርፅ) ተፅፎ ከተገኘው ረጅም እድሜ ያስቆጠረው በመካከለኛው ስርወመንግሥት ዘመን በ2100 ቅጋአ ነበር። የኩሽ ሀገረ-ግዛት በየወቅቱ መስፋትና መጥበብ ቢያሳይም በዋናነት የሚያመለክተው ከግብፅ ደቡብ ነጭ አባይ፣ ጥቁር አባይ፣ እና አትባራ ወንዞች የሚገናኝበትን ግዛት ባሁኑ ግዜ ሱዳን የሚባለውን የጎረቤታችንን ሀገር ነው። በሰሜን በኤለፋንቴ የመጀመሪያው ካታራክት የጥንታዊ ግብፅ እና የኩሽ ስርወመንግሥታት ጥንታዊ ወሰን ተደርጎ ይቆጠራል። ደቡብ ሱዳን በዚህ መንግስት ግዛት ስር አይካተትም። ኢትዮጵያን ቀርቶ ከኢትዮጵያ ግዛት በኩሽ ስር የነበረ በታሪክ አይታወቅም። ኩሽ ግዛቱን ወደሜሮኤ ባዞረበት ወቅት ኢትዮጵያ የተጠናከረ የራሷ አስተዳደር ነበራት። እንደውም ለኩሽ ማዕከላዊ መንግሥት መጥፋት ዋናው ምክንያት የኢትዮጵያው የአክሱም ስርወመንግሥት እንደሆነ ይታመናል።
የኩሽ ስርወመንግሥት የኢትዮጵያ ስርወመንግሥት እንዲሁም የኑብያ ስርወመንግሥት በመባልም ይታወቃል። እነዚህ የኋለኞቹ አጠቃቀሞች አሁንም በተለዋዋጭነት በምሁራን ስራዎች ይገኛሉ። በርግጥ ኑብያ የሚለውን ስያሜ በስፋት የሚጠቀሙበት የታሪክ ባለሙያዎች ናቸው። የኩሽ ስርወመንግሥት እራሱን ኑብያ በሚል ስያሜ ጠርቶ አያውቅም። የኩሽ ስርወመንግሥት የራስ ስያሜ ምናልባት ካሽ ሊሆን ይችላል። ከመካከለኛው የግብፅ ስርወመንግሥት ጀምሮ በግብፃውያን ዘንድ ባብዛኛው ተመዝግቦ የሚገኘው ካሽ በሚል ነው።
የኩሽ ስርወመንግሥት የ25ኛው ስርወመንግሥት ባለቤቶች ናቸው። በዚህ ስርወመንግሥት በርካታ ታላላቅ የስልጣኔ ተግባራት ተከናውነዋል። ግብፅም ታላቅ የቆዳ ስፋት የነበራት በዚሁ በኩሽ አገዛዝ ስር በነበረችበት ወቅት ነው።
ኩሽ በጥንታዊ አጠቃቀሙ ህዝብን/ነገድን ለማመልከት ሲውልም ይስተዋላል። በሁሉም ቦታዎች በዚህ ቃል የተገለፁት ነገዶችም ሆኑ ቦታዎች ሁሌም አንድ ናቸው ማለት ግን አይቻልም። በአንዳንድ ስራዎች የቃሉ አጠቃቀም ግልፅ ያልሆነበት ሁኔታም አለ። በዚህ ክፍል በጥንታዊ ስራዎች የዚህን ቃል አገባብ፣ እንዲሁም የኩሽ ግዛትን እንመረመራለን።
2.1 የኩሽ/የቃሉ ምንጭ
ኩሽ እንደቃልነት ከጥንት እስካሁን በሁሉ ቋንቋ አንድ አይነት ንበት አልነበረውም። በርግጥ ይህ እንዲሆን መጠበቁም የዋህነት ነው። ከተለያዩ ታሪካዊ አጋጣሚዎች በተጨማሪ እያንዳንዱ ቋንቋ የራሱ የሆነ የሰዋስው ስርዓት አለውና አንድ አይነት ንበት በሁሉ ቋንቋ የግድ መኖር የለበትም። ይህ ቃል በግዕዝ ካሱ ነው። ለዚህ ከቀዳሚ ስራዎች ውስጥ የኢዛናን የድንጋይ ላይ ፅሁፎች መጥቀስ ይቻላል። በኢዛናው ፅሁፍ (DAE 5,6,7) ላይ በግሪኩ ኢትዮጵያ የሚለው በግዕዝና በሳብያን ቅጂው ሐበሠተ ‘ሀበሻ’ የሚለውን ወክሎ ነው።
ብሬየር (2007) በግብፅ በተለያዩ ወቅት እንዲሁም በተለያዩ ቋንቋዎች ቃሉ ምን እንደሚመስል በዝርዝር ተመክልቷል። እንደብሬየር ከሆነ፣ በጥንታዊ ፋርስ ኩሳ፣ በእብራይስጥ ኩሺ፣ በሜሮቲክ ቄስ /qes/፣ (በመካከለኛው) ባቢሎንያን ካሺ /Ka-ši/፣ በቅብጥ (Coptic) ኤክዮሽ /ekjōš/ የሚል እናገኛለን (ብሬየር 2007:458)። ብሬየር (ዝኒከማሁ) የቅብጡ ኤክዮሽ ከ*ኢካሽ እንደመጣ ግምቱን ሰጥቷል። ለዚህ ምክንያቱም፣ በ25ኛው የግብፁ ስርወመንግሥት ወቅት በተፃፈ ፅሁፍ ላይ እና በዲሞቲክ የዚህ ቃል ቅርፅ ኢክሽ /ikš/ ስለሆነ ነው። ብሬየር ኢክሽ በበኩሉ ከካሺ/ክሺ//kši/ የመጣ ይመስላል ይላል። በመካከለኛው የግብፅ መንግስት፣ ካ/ክሺ /K š(i)/ ሲሆን፣ ሁለተኛው አማካይ ዘመን በሚባለው ክሺ /Kš(i)/ ነው። በአዲሱ ስርወመንግሥት ደግሞ ክሽ /Kš/ ነው። በጥንታዊ የግብፅ ቋንቋ ከ /k/ ስርጭቱ በጣም አናሳ ነው። ይህ ድምፅ ብዙውን ግዜ የሚገኘው በተወሰኑ ቃላት ውስጥ በመሆኑ የውሰት ሊሆን ይችላል የሚል ግምት አለ። ይህም ማለት ከ ያላቸው ቃላት በጥንታዊ ግብፅ የምናገኛቸው ከሌሎች ቋንቋዎች የተወሰዱ/የተወረሱ ሳይሆኑ አይቀርም ነው። የዚህ አንድምታው ደግሞ ጥንታዊ ግብፅ ካሽ (ወይም የዚህ ቃል የተለያየ ቅርፅ) ከሜሮቲክ ጋር ተዛማጅ ከሆነ ጥንታዊ አባት ቋንቋ ተውሶ ይሆናል የሚል ነው (ብሬየር ዝኒከማሁ)። የሜሮቲክ አባት ቋንቋ ሜሮቲክ ይገኝበት የነበረው አካባቢ፣ የአሁኒቱ ሱዳን የነበረ ነው ተብሎ ይታሰባል።
2.2 ጥንታዊ ሀገረ ኩሽ
የዛሬ ዘጠኝ ሺህ ዓመት ገደማ ከኢትዮጵያ ደጋማ ቦታዎች ጀምሮ የአባይ ሸለቆን ይዞ እስከታች ግብፅ ድረስ ተመሳሳይ የባህል ስልጣኔ አብቦ እንደነበር ይገመታል። የስንቁፋሮ/አርኪዮሎጂ ውጤቶች እንደሚያሳዩት ከሆነ በዚህ አካባቢ የነበሩ ህዝቦች እስከ 3000 ቅጋአ ድረስ ተመሳሳይ ባህልና የእድገት ደረጃ ላይ ነበሩ። የቀብር ስርዓታቸው ተመሳሳይ፣ ካልሆነም አንድ አይነት ነበር። የሸክላ ስራዎቻቸው፣ ከድንጋይ እና ወደኋላ ላይ ደግሞ ከብረት የተሰሩ መሳሪያዎቻቸው አንድ ናቸው። እነዚህ መሳሪያዎች በደቡብ እስከ ካርቱም፣ በሰሜን ደግሞ እስከ አስዩት ድረስ በቁፋሮ ተገኝተዋል። እንደ አዳም (1981:232) ከሆነ መሳሪያዎቹ በርካታ አካባቢዎች የአኗኗር ዘይቤያቸው፣ እምነታቸው፣ የቀብር ስርዓታቸው፣ እንዲሁም አጠቃላይ ህይወታቸው/የየቀን ኑሯቸው፣ አደን፣ አሳ ማስገር፣ እና የከብት እርባታ እንዲሁም በጣም ቀላል የሆነ የእርሻ ተግባር ጅማሮ ተመሳሳይ ነው።
በግብፅና ከመጀመሪያው ካታራክት በስተደቡብ ባለው ህዝብ መሀከል የስልጣኔ ልዩነት በዋነኛነት መታየት የጀመረው ከፅሁፍ ጋር በተያያዘ ባህል እንደሆነ ይገመታል። ፅሁፍ በግብፅ 3200 ቅጋአ አካባባቢ መታየት ጀመረ። ከመጀመሪያው ካታራክት በታች ባለው ህዝብ ግን ይህ ሁኔታ አልታየም። የኩሽ ግዛት የፅህፈት ባህልን ያስተዋወቀው በኋላ ላይ ዘግይቶ በሜሮኤ ዘመን ነው። በርግጥ ኩሾች ግብፅን ጠቅልለው በገዙበት ወቅት የሚያስተዳድሩትን ህዝብ ባህል በመውሰድ በፅሁፍ መገልገላቸው አልቀረም።
በአሁኒቷ ሱዳን የዛሬ 6 ሺህ አመት (ቅጋአ) ገደማ በከርማ አካባቢ መታየት የጀመረው ስልጣኔ እያደገ ሄዶ ምናልባትም በከርማ ራሱን የቻለ መንግስት በ2600 ቅጋአ አካባቢ የተመሰረተ ይመስላል (ለምሳሌ ቦኔትን 1983ን ይምልከቱ)። የከርማ ስረወመንግስት ወይም የከርማ ባህል በአሁኑ ማእከላዊና ሰሜን ሱዳን ተነስቶ በግዜ ሂደት እየተስፋፋ ከ2500 እስከ 1500 ባለው ግዜ ውስጥ የጥንታዊ ግብፅ ደቡብ ጠረፍ እንደደረሰ ታሪካዊ ማስረጃዎች አሉ። የኩሽ ስርወመንግሥት መነሻ ይህ የከርማ ስርወመንግሥት ነው። ስለከርማ በርግጠኝነት ብዙ ማለት አይቻልም። በዚች ከተማ እስካሁን የተገኘ ምንም የፅሁፍ ማስረጃ የለም። ከተማዋም በ6ኛው መቶ ክፍለዘመን ቅድመ ጋራ አቆጣጠር (ቅጋአ) በግብፆች እንዳልነበረች ሆኗ ወድማለች። ስለዚች ከተማና ባጠቃላይ በወቅቱ ስለነበረው የኩሽ/የከርማ ስርወመንግሥት መረጃ የምናገኘው ከውድመት ከተረፈው ከከተማዋ ፍርስራሽ እና ከግብፅ ምንጮች ነው።
የመካከለኛው ስርወመንግሥት መስራች የሚባለው የ21ኛው መቶ ቅጋአ ዳግማዊ ሜንቱሆተፕ የተከፋፈሉትና የደከሙትን የግብፅ ግዛቶች አንድ በማድረግ ወደጠነከረ ማእከላዊ ስረወመንግስት ማምጣት ብቻ ሳይሆን፣ ከግዛቱ አልፎ በኩሽ ስርወመንግሥት/በከርማ ስርወመንግሥት ላይ በሀያ ዘጠነኛው እና በሰላሳ አንደኛው የንግስና ዘመኑ ዘመተ። የግብፅና የኩሽ ስርወመንግሥታት ግጭት በዳግማዊ ሜንቱሆተፕ አላበቃም። ከዳግማዊ ሜንቱሆተፕ ከአምስት መቶ አመት በኋላ የተነሳው ቀዳማዊ ቶተሚስ ተደጋጋሚ ዘመቻ በኩሽ ላይ በማድረግ ወደበኋላ ላይ ተሳክቶለት በ1504 ቅጋአ አካባቢ ኩሽን በራሱ ግዛት ስር አደረገ። የኩሽ ስርወመንግሥት በግብፅ ስር ከመውደቁ በፊት ከ1700 ጀምሮ በጣም እየተጠናከረ መጥቶ ነበር። በ1700 እስከ 1500 ባለው ግዜ ውስጥ በአካባቢው የነበሩትን ትንንሽ ስርወመንግሥታት አስገብሮ ድንበር ለማስፋትም ችሎ ነበር።
ኩሽ በ15ኛው መቶ ቅጋአ አካባቢ በግብፅ ስር ብትወድቅም፣ ከሁለት መቶ ዓመት በላይ በዘለቀ ህዝቡ በግብፅ አገዛዝ ላይ ያምፅ ነበር። ይህ አመፅ ገፍቶ የግብፅ አዲሱ ስረወመንግስት በተከፋፈለበትና በደከመበት በ11ኛው መቶ ቅጋአ አካባቢ ኩሽ እራሷን ችላ ነፃ ወጣች (ከብዙ በጥቂቱ አርኬል 1955ን ይመልከቱ)።
ኩሽ ከግብፅ በነበራት ጥንታዊ ንክኪ በተጨማሪ ለአራት መቶ አመት ያህል እንደአንድ የግብፅ አካል ሆና መቆየቷ ከፍተኛ የባህል ተፅዕኖ አሳድሮባታል። በተለይ ናፓታ ከፍተኛ የስላጣኔ እና የሀይማኖት ማእከል ሆና እንድትወጣ አስችሏታል። ናፓታ በሀይማኖት ማዕከልነቷ የግብፅ እምብርት ከመሆንም አልፋ የኩሽ ስረወመንግሥት መቀመጫም/ዋና ከተማም በ8ኛው መቶ ቅጋአ ለመሆን በቃች። ኩሽ ነፃነቷን ካስመለሰች በኋላ ከ11ኛው መቶ ቅጋአ እስከ 8ኛው ቅጋአ ድረስ ዋና ከተማዋ ከርማ ሳይሆን አይቀርም ተብሎ ይገመታል። በዚህ ላይ ያለው መረጃ ስስ ነው።
በናፓታ የኩሽ ስረወመንግስት የመጀመሪያው ንጉስ አላራ ነው። በግብፅ ላይ ወረራ በማካሄድ ግብፅን ሊቆጣጠር የሞከረው ንጉስ ካሻታ የአላራ ወራሽ ነው። ንጉስ ካሻታ ምንም እንኳ በአንዳንዶች የ25ኛው የግብፅ ስርወመንግሥት መስራች ተደርጎ ቢቆጠርም ሙሉ በሙሉ ተሳክቶለት ግብፅ በተራዋ በኩሽ ግዛት ስር እንድትወድቅ ያደረገው ፕዬ ነው። ከዚህ ዘመን ጀምሮ ያለውን የኩሽ ስረወመንግሥት በሁለት ከፍሎ መመልከቱ የተለመደ ነው። እነዚህም የናፓታን ዘመን እና የሜሮኤ ዘመን በመባል ይታወቃሉ። ስያሜያቸው የወጣው የኩሽ ስርወመንግሥት መቀመጫ ከነበሩት ዋና ከተሞች በመነሳት ነው። የናፓታን ዘመን ከከርማ ማግስት በግልፅ ከሚታወቀው የኩሽ ታሪካዊ ስርወመንግሥት ምስረታ አንስቶ መቀመጫው ከናፓታን ወደ ሜሮኤ ከተሸጋገረበት 591 ቅጋአ አካባቢ ወይም አንዳንዶች እንደሚሉት 4ኛው መቶ ቅጋአ አካባቢ ያለውን ሲያመለክት የሜሮኤው ደግሞ ከዚህ ዘመን ቀጥሎ የኩሽ ስርወመንግሥትን ወደ የመጨረሻ መቃብር ከተተው ከሚባለው ከኢዛና ግዜ፣ አራተኛው ጋአ ድረስ ያለውን ይይዛል። የናፓታ ዘመንን በራሱ በሁለት ከፍሎ ማየት ይቻላል። አንደኛው ኩሽ ገናና ሆኖ መላው ግብፅን ተቆጣጥሮ ከራሱ ግዛት ጋር ደምሮ ያስተዳደረበትን እስከ 654 ቅጋአ አካባቢ ዘመን የሚያካትት ሲሆን፣ ሁለተኛው ከግብፅ ተባሮ የበላይነቱ አክትሞ በጥንቱ ግዛቱ ብቻ የተወሰነበትንና ከዚያም የአስተዳደር ከተማውን ወደሜሮኤ ያዛወረበትን እንደዲክሰን (1964: 123) ከሆነ ከ654 እስከ 591 ቅጋአ ያለውን ግዜ ያካትታል።
ኩሾች ናፓታ ላይ ሆነው ግብፅን ማስተዳደር ብቻ ሳይሆን ከግብፅ ግዛት ከተባረሩም በኋል ዋና ከተማቸውን ወደ ሜሮኤ እስከዛወሩ ድረስ እዚያው ነበሩ። ኩሾች ግብፅን ተቆጣጥረው የ25ኛው ስርወመንግሥት በመመስረት የቆዩበት ዘመን 744 እስከ 656 ቅጋአ አካባቢ ድረስ ነው። ናፓታ ዋና ከተማቸው አድርገው የቆዩበት ዘመን ደግሞ እስከ 538 ቅጋ አካባቢ ይደርሳል። የሜሮኤ ዘመን ከዚህ፣ ማ. 538 ቅጋአ ጀመሮ እስከ 350 ጋአ አካባቢ ያለው ነው። 350 ጋአ ሜሮኤ ሙሉ በሙሉ በኢዛና የወደመችበት ዓመት መሆኑን ልብ ይሏል።
የኩሽ ስርወመንግሥት ለኢትዮጵያ ድንበር ወደሚቀርበው ወደሜሮኤ ዋና ከተማውን ያዞረው በኢትዮጵያ የዳኣማት ስርወመንግሥት ከተመሰረተ በኋላ ነው ማለት ነው። በዚህን ወቅት በአሁኒቷ ኢትዮጵያ-ኤርትራም ሆነ በጥንቱ የአክሱም እና የዳአማት ስርወመንግሥታት በሚያካልለው ግዛት የኩሽ ስረወመንግሥት አልፎ ስለመግዛቱ እስካሁን የሚታወቅ ምንም ማረጋገጫ የለም። በርግጥ ስለኩሽ ሀገር ስፋት እርግጠኛ ሆኖ መናገር አይቻልም። አንድም በየወቅቱ የመጥበብና የመስፋት ሁኔታ ከላይ እንደገለፅንው ስለሚያሳይ ነው። ይሁን እንጂ ኩሽ በተለይ በደቡብና በምዕራብ ያሉትን ጠረፎች ካሳደረባቸው የባህል ተፅዕኖ በመነሳት ግምት መስጠት ይቻላል። በሜሮኤና በአክሱም የነበሩት ስርወመንግሥታት ስሪት የተለያየ ነው። የኩሹ ሙሉ ዝምድናው/ባህላዊ ተፅእኖው የግብፁ ሲሆን፣ የኢትዮጵያው ግን ባህር ተሻግሮ ከደቡብ አረቢያ ነው። ይህን በተመለከተ ከብዙ በጥቂቱ ሙንሮ ሄይ (1991)ን፣ ባጅ (1928) እና ስርግው ኃብለሥላሴ (1972)ን ይመልከቱ። ለተጨማሪ፣ ሌክላንት በዚህ ጉዳይ ላይ የዘረዘረውን ይመልከቱ (ሌክላንት 1981: 283-285)።
ኩሽ ኢትዮጵያ ድንበር ውስጥ ዘልቃ ስለማስተዳደሯ ሳይሆን፣ ይልቁንም ወደበኋላ ላይ ሜሮኤ እራሷ በአክሱም አገዛዝ ስር ሳትወድቅ አልቀረችም። ኢዛና በሜሮኤ የነበረውን የኩሽ መንግስት እንደደመሰሰ ትቶልን ካለፈው የድንጋይ ላይ ፅሁፎች ይታወቃል። ምናልባትም ኢዛና ወደሜሮኤ ዘምቶ ሊያጠፋት ያስቻለው፣ ግብር አልከፍልም በማለት እያስቸገረች ሊሆን ይችላል።
2.2 የኩሽ ነገድና ቋንቋ በጥንታዊው የኩሽ መንግስት
ኑቢያ የጥንቱን የኩሽ ሀገር እና ስልጣኔ ለማመልከት በስፋት በተለይ በምሁራን ስራ ላይ ይዘወተራል። ይሁን እንጂ፣ ኑቢያ የሚለው ቃል የመጣው ኖባ ከሚባሉ በሶስተኛው መቶ ጋአ አካባቢ የላይኛው ኑቢያን/ኩሽን ወረው ከነበሩ (በወቅቱ) ዘላን ህዝቦች ነው። እነዚህ ህዝቦች ሮማኖች ኖባቲያ ይሏቸው ነበር። ኑቢያ ከኖባቲያ በሂደት የተገኘ ነው። ቃሉ መጀመሪያ ተጠቅሶ የሚገኘው ኖባዎች ኩሽን ከወረሩበት ከ600 ዓመት በፊት ጀምሮ ነው። ኖባቲያ በፕሊኒ የመጀመሪያው መቶ ክፍለዘመን ስራ ተጠቅሶ ይገኛል። ፕሊኒ የጠቀስውን ስራ ከያዝን 3ኛው መቶ ቅጋአ ይሄዳል (ለእንግሊዝኛ ትርጉም ራክሃም 1942፡480ን እና ኤዲ እና ሌሎች 1996፡548ን ይመልከቱ)።
ኑቢያኖች በኩሽ ስርወመንግሥት ስር ቢኖሩም እና የኩሽ ስርወመንግሥት በተለዋጭ የኑብያ ስርወመንግሥት እየተባለ ቢጠራም፣ እነዚህ ህዝቦች ግን ከኩሾች የተለዩ ናቸው። የኖባ/ኑብ ህዝቦች በዚሁ ስያሜ እየተጠሩ አሁንም በግብፅ እና በሱዳን አሉ። በሱዳን እነዚህ ህዝቦች 15% እንደሆኑ ይነገራል። ቋንቋቸውም የአባይሰሀራዊ ወገን ነው። ጥንታዊ የስልጣኔው ባለቤት ኩሾች ግን በአሁኑ ግዜ እራሱን በቻለ ብሄረሰብ አይታወቁም። የኑቢያን ህዝቦች ቋንቋ ከኩሾች ቋንቋ ጋር ግን የተለየ ነው። የኩሾች ቋንቋ በሜሮኤ የተገኘው ነው ተብሎ ይታሰባል። በናፓታና ሜሮኤ ከተሞች የነበሩት ህዝቦች የተለያዩ ተደርገው አይወሰዱም። እነዚህ ህዝቦች ኩሾች ናቸው።
የሜሮቲክ ቋንቋ እስካሁን ሁሉም የተስማማበት የዘር ምደባ የለውም። በተወሰኑ ስራዎች የአፍሮኤስያዊ ቋንቋ አካል ተደርጎ ሲቆጠር፣ በአንዳንድ ስራዎች ደግሞ በኒሎሰሃራን ታላቅ የቋንቋ ቤተሰብ ስር የምስራቅ ሱዳኒክ ቋንቋ ሳይሆን አይቀርም የሚል ግምት አለ። የኋለኛውን በተለይ ራይሊ (2004) አጥብቆ ይገፋበታል። ይሁን እንጂ፣ የሜሮቲክ ቋንቋ ወገኑ ከዚህ ነው ለማለት የሚያስችል በቂ መረጃ እስካሁን አልተገኘም።
ስለኩሽ ህዝቦች ማንነት የተለያየ፣ አንዳንዴም ተቃራኒ አስተያየት ይገኛል። በጥንታዊ ግብፆች እይታ ኑቢያኖች/ኖባዎች በመልክ ከነሱ ጠቆር ቢሉም በትክለ ሰውነታቸው ግን አንድ ናቸው። እንደአዳም ከሆነ ኩሾች ግን በመልክ ብቻ ሳይሆን በሰውነት ቅርፅም ከኑቢያኖችና ከግብፆች የተለዩ ናቸው (አዳም 1981፡231)። የኩሾች ትክለ ሰውነት የማእከላዊና ምእራብ አፍሪካን ይመስላል (ዝኒ ከማሁ)።
ኩሾች ከኑቢያኖችና ከግብፆች በተለይ የምዕራብ አፍሪካን ሰዎች ይመስላሉ የሚለውን የአዳምን ትንታኔ ለመቀበል አስቸጋሪ ነው። አንደኛ፣ የምዕራብ አፍሪካን ትክለ ሰውነት የሚመስሉ ስዕሎችና ቅርፆች መገኘታቸው እውነት ቢሆንም፣ ይህ የኩሽን ህዝብ ሙሉ በሙሉ ለመግለፅ አይበቃም። በግብፅም የምዕራብ አፍሪካ ሰዎችን የመሰሉ የጥንታዊ ግብፃውያን ምስሎች አሉ። እንደዚህ አይነቱን ብቻ በመያዝ ጥንታዊ ግብፆች የምዕራብ አፍሪካን ይመስላሉ ማለቱ አሳማኝ አይደለም። ምክንያቱም በርካታዎቹ ቅርፃ ቅርፆችና ስዕሎች የሚያሳዩት ከዚህ የተለየ ነውና። በኩሾችም ያለው ሁኔታ ይኸው ነው። ጥንታዊ ግብፆችም ሆኑ ኩሾች በትክለ ሰውነት ደረጃ በበርካታ ቅርፆች እንደሚታየው ልዩነት የላቸውም። በሰርቪስ (1998) እና ሌሎች በርካታ ስራዎች ላይ የቀረበውም ይህንኑ የሚያስረግጥ ከአዳም የተለየ ሀሳብ ነው። ለምሳሌ የኩሽ ህዝቦች የአሁኒቷን ሰሜን ሱዳን ህዝቦች እንደሚመስሉ፣ ከተዉልን የግርግዳ ላይ ስዕሎች እና ቅርፃቅርፆች/ሀውልቶች እንዲሁም ከጥንታዊ ኩሾች ቅሪተ አካል የስነሰብ ጥናት እንዳረጋገጠው የሰሜን ሱዳን ህዝቦች ጋር አንድ ናቸው (ሰርቪስ 1998: 56)። በርግጥ ኩሾች ከጥንታዊ ግብፆች ምናልባት ትንሽ ጠቆር ያሉ ሊሆን ይችላል። ብሬየር ቪችልን በመጥቀስ የሚከተለውን ይላል፤ “አረብኛ ተናጋሪ የሆኑ በግብፅ የሚገኙ የቤጃ ሰዎች/ቡድን አሁንም ጠቆር ያለ ቆዳ ያለውን ህዝብ ኪሻብ ይላሉ (ብ በኪሻብ ላይ ያለችው ተባእታይ ተሳቢ አመልካች ነች)” (ብሬየር 2007:459)። በ1820 ቅጋአ በ ማለፊያ/መግቢያ መፅሀፍ ‘ቡክ ኦፍ ጌትስ’ የነገዶች ምስል ላይ ኩሽ የቀረበው ከሌሎቹ ጥቁር ሆኖ ነው።
ምስል 1፡ ከግራ ወደ ቀኝ ቴሙ ‘ሊቢያዊ’፣ ነሀሱ ‘ኩሽ’፣ አሙ ‘ኤስያዊ’ እና ፔት ‘ግብፃዊ’ Source: Supplied
ኩሽን ከጥቁረት ጋር ማያያዝ የመጣውም አንዲያም እራሳቸው ኩሾች ከግብፆች በተለይ ጠቆር ስለሚሉ ወይም በሚያስተዳድሩዋቸው ህዝቦች መሀከል ሌሎች ጠቆር የሚሉ ኖረው ሊሆን ይችላል። ግሪኮች ኩሾችን ለመግለፅ ኢትዮጵያ የሚለውን የተጠቀሙበት ለዚህ ሊሆን ይችላል። በቀጣዩ ክፍል እንደምንመለከተው ለምሳሌ በመፅሀፍ ቅዱስ ኩሽ የሚለው ስም በአብዛኛው በግሪክ ኢትዮጵያ በሚል ተተክቶ ይገኛል።
ምናልባት ከሶስተኛው ክፍለዘመን ጀምሮ የኑቢያኖች/ኖባዎች የበላይነት እያገኙ መምጣት፣ ከዚያም የእስልምና ሀይማኖት መስፋፋት የተለየ የአረብ ማንነትን እያላበሰ የኩሽ ማንነት ሊጠፋ እንደቻለ መገመት ይቻላል። “በአሁኑ ግዜ 70% ያህሉ የሱዳን ህዝብ አረብ ነኝ ወይም የአረብ ዝርያ አለኝ ይላል። ከእነዚህ ጃአልዪን፣ ሻይጊያ እና ማናሴር ይገኙበታል። በእነዚህ 70% አረብ ነን በሚሉ ሱዳኖች እና በኑቢያኖች መሀከል ያለው ዋና ልዩነት ቋንቋ ነው። ኑቢያኖች የጥንቱን ኑቢያን የሚባለውን ቋንቋ ሲናገሩ፣ ሌሎቹ አረብኛን ይናገራሉ።
ኑቢያኖችም አሁንም ማንነታቸውን ሳያጠፉ በመኖራቸው፣ የአረብ ማንነት የወሰዱት ኩሾች ናቸው ብሎ መገመት ይቻላል። ይህ ግን ኑቢያን ማንነትን የወሰዱ ኩሾች ሊኖሩ አይችሉም ማለት አይደለም። ህዝቡ ከነበረው ለረጅም ግዜ የቆየ ግንኙነት የተነሳ የተቀላቀሉ እንዳሉ መገመት ስህተት ሊሆን አይችልም (ዝኒ ከማሁ)። በአሁኑ ግዜ አረብ ነኝ በሚለውና በኑብያኖች መሀከል በመልክም ሆነ በአጠቃላይ በሰውነት/በአካል መለየት አይቻልም። ስለዚህ አረብ ነን የሚለው ሱዳናዊ ከቋንቋ የዘለለ የደም ትስስር ከአረቦች ጋር እንደሌለው መገመት ይቻላል። ከዚህ በፊት የወጡ ስራዎችም በርግጥ ይህንኑ አስረግጠው ብለውታል። የኩሾች ጉዳይ ከአግዐዝያን/ግዕዝ ተናጋሪዎች ጋር ተመሳሳይ ነው። ዛሬ የጥንታዊ አክሱም መስራች የሚባሉት ግዕዝ ተናጋሪ የነበሩት በሌላው ተውጠው የተለየ የነገድ ማንነት የላቸውም።
2.3 የኩሽ ነገድ በመፅሀፍ ቅዱስ እሳቤ
በመፅሀፍ ቅዱስ ያለውን የኩሽ አገባብ በርካታ ስራዎች ሲመረምሩት ቆይተዋል። በሀገራችን እንኳ ሩቅ ሳንሄድ ኪዳነወልድ ክፍሌን (1948) እና ተክለፃዲቅ መኩሪያን መጥቀስ ይቻላል። የኤፍሬም ይስሐቅ (1980) ኩሽ፣ ጁዳይዝም እና ስሌቨሪ ‘ኩሽ፣ ይሁዲነት እና ባርነት’ የሚለው መጣጥፍ የኩሽን አገባብ በስፋት በመፅሀፍ ቅዱስና በድኅረ-መፅሀፍ ቅዱስ የአይሁድ እምነት ስራዎች ውስጥ የሚመረምር ነው።
ኩሽ (እና ከዚህ ስር የወጡ ቃላት) በተለያዩ ቋንቋዎች ባሉት መፅሀፍ ቅዱስ ተመሳሳይ አይደለም። በአንድ ቋንቋ በተለያየ ወቅት በሚገኙ መፅሀፍ ቅዱስ ቅጂዎች ውስጥ እራሱ ልዩነት አለ። በእብራይስጥ ኩሽ የሚለውን በሶስተኛው መቶ ቅጋአ ወደግሪክ የተተረጎመው ብሉይ ኪዳንና ሌሎች የእብራይስጥ ፅሁፎች ላይ በወጥነት ኢትዮጵያ በማለት ቀርቧል። እንደዚሁም፣ ቨልጌት የሚባለው የአራተኛው ክፍለዘመን የላቲን መፅሀፍ ቅዱስ ትርጉምም ኢትዮጵያ በሚል ያቀርበዋል። በእንግሊዝኛው ኪንግ ጀምስ ቅጂ ኢትዮጵያ የሚለውን ከኩሽ ከሚለው ጋር እናገኛለን። ለምሳሌ፣ የካም ልጆችን ሲዘረዝር (ዘፍ 10፡6, 1መዋ 1፡8፣ 1መዋ 1፡9፣ 1መዋ 1፡ 10) ኩሽ ሲል፣ በሌሎች በርካታ ቦታዎች ደግሞ ኢትዮጵያ ይላል። በአማርኛው መፅሀፍ ቅዱስ ያለው ሁኔታም እንደዚሁ ነው። ለምሳሌ፣ በ1962 በወጣው መፅሀፍ ቅዱስ ላይ ኩሽ (ዘፍጥረት 10:6፣ 7 እና 8)፣ ኢትዮጵያ (ዘፍ 2፡13፣ 2መሳ 19፡9፣ አስ 1፡1፣ አስ 8፡9፣ ወዘተ)፣ እንዲሁም ኵሲ (2ሳሙ 18:21፣ 2ሳሙ 18:22፣ 2ሳሙ 18:23፣ 2ሳሙ 18:31፣2ሳሙ 18:32፣ ኢር 36፡14፣ ሶፎ 1፡1) እና ኩዝ (መዝ 7፡መግቢያ [7፡1]) እናገኛለን። ከእብራይስጡ ለመስማማት በእንግሊዝኛው ቅጂ ከግሪኩ ኢትዮጵያ የሚለውን በመተው ኩሽ የሚለውን ብቻ በመውሰድ የቀረቡ የቅርብ ግዜ ቅጂዎች አሉ። የዚህን ቃል አገባብ በመፅሀፍ ቅዱስ ስንመረምር ለሁለት ነገሮች ውሎ እናገኛለን። አንድም፣ ህዝብን (ማ. ነገድን ወይም ግለሰብን)፣ እና ሁለትም ሀገርን ሲገልፅ ይታያል። ሀገርን የሚገልፀው በእንግሊዝኛው ኪንግ ጀምስ ቅጂም ሆነ በአማርኛው በ1962 ህትመት ላይ ብዙውን ግዜ ኢትዮጵያ በሚል ይገኛል።
ኩሽ የሚለው ወይም ከዚህ ቃል የወጡ በመፅሀፍ ቅዱስ ብቻ ሳይሆን በድኅረ-መፅሀፍ ቅዱስ ባሉ የአይሁድ ስራዎች ህዝብን እና ሀገርን ለማመልከት ሲውል እንደሚገኝ በመስኩ ጥናት ያደረጉ በርካታ ባለሙያዎች ሲገልፁ ኖረዋል።
በመፅሀፍ ቅዱስ ያለው ኩሽ የወከለው ከግብጽ በስተደቡብ ያለውን በቀዳሚዎቹ የተመለከትንውን ሀገርና ነገድ ብቻ አይደለም። ከላይ እንደገለፅንው ኩሽ የካም የመጀመሪያ ልጅ ሲሆን፣ ሚዝራም (ግብፅ)፣ ከነዓን (የከነዓን ምድር)፣ እና ፑት ወንድሞቹ ናቸው። ኩሽ በዘፍጥረት 10፡6 እና መዋዕለ ቀዳማዊ 1:8 የኒምሮይድ አባት ነው። ኒምሮይድ እንደአይሁዶች ዘልማድ የመጀመሪያውን መንግስት በባቢሎን የመሰረተ ታላቅና ኃይለኛ ንጉስ ነበር። በኦሪት ዘኁልቆ 12፡1 የሙሴ ሚስት ኢትዮጵያዊ/ኩሽ ይላታል። ይሁን እንጂ የሙሴ ሚስት ዚፎራ/ሲፎራ ከሚዲያን እንደሆነች በተለያዩ ቦታ ተገልፆ ይገኛል። ሚዲያን ደግሞ ትክክለኛው ቦታ የት እንደሆነ የተለያየ አስተያየት ቢኖርም፣ በመካከለኛው ምስራቅ የነበረ ሀገርን እንደሚያመለክት ሁሉም ማለት ይቻላል የታሪክ ባለሙያ የሚስማሙበት ነው። ሌላኛው በእብራይስጥ መፅሀፍ ቅዱስ ውስጥ ያለው ኩሽ ስለተባለው ሰው በመዝሙር 7 ላይ የተገለፀው የብንያማዊው ሰው ነው። ይህ ሰው የሳኦል ተከታይ እንደነበር ይገመታል።
አንዳንድ ቀደምት ስራዎች የሁሉም ምንጭ መፅሀፍ ቅዱስ አድርግው ከማሰብ ኩሽ የሚለው ቃል ከግብፅ ደቡብ ለሚኖረው ህዝብና ሀገር መዋል የጀመረው ከመፅሀፍ ቅዱስ በመውሰድ ነው ቢሉም፣ እብራይስጥ እራሱ ቃሉን የወሰደው በተገላቢጦሹ ከሀገሩ ስያሜ መሆኑን መገመት አዳጋች አይደለም። ባለፈው ክፍል እንደተመለከትንው ኩሽ አዲስም ሆነ ብሉይ ኪዳን የሚባል ሳይፃፍ የነበረ ስያሜ ነው። ይህ ቃል ዳዊት ነገሠ ከተባለበት ከሺህ ዓመት በፊት የነበረ ቃል ነው። ለመጀመሪያ በግብፅ ስራዎች በተጠቀሰበት በ11ኛው ስርወመንግሥት በ2100 ቅጋአ ራሱን የቻለ እብራይስጥ የተባለ ቋንቋም ሆነ የአይሁድ ህዝብ አይታወቅም። የእብራይስጥ ምሁር የሆነው ዴቪድ ጎልደንበርግ (ገፅ 18)ም የእብራይስጡ ኩሽ በግብፅ ስራዎች ከእነሱ ደቡብ ለሚኖሩት መጠሪያነት ካዋሉት ካሽ ከሚባለው ቃል ነው የመጣው ይላል። የእብራይስጥ መፅሀፍ ቅዱስ በተፃፈበት ወቅት የኩሽ/ኑቢያ መንግስት ዋና መቀመጫው ሜሮኤ ነበር። በመፅሀፍ ቅዱስ ይህን ቦታ በተለይ የሚመለከት ተደርጎ የተጠቀሰበትም አለ። ለምሳሌ፣ ሕዝቄል 29፡10ን፣ ናሆም 3:9ን ይመልከቱ።
2.4 ኩሽ፣ ኢትዮጵያና ጥቁረት
የኩሽ መንግስትንም ሆነ በመፅሀፍ ቅዱስ የሚገኘውን ኩሽ የተሰኘውን ነገድ በጥንታዊ ግሪክ ኢትዮጵያ ይለዋል። ግሪኮች ኢትዮጵያ የሚለውን ቃል ተጠቅመው የምናገኘው ከሆሜር እና ሄሮዱተስ ጀምሮ ነው። ቃሉንም የተጠቀሙበት ወጥ በሆነ መልኩ አይደለም። አንዳንዴ መላው አፍሪካን ለማመልከት ነው። ከላይ እንደገለፅንው በግሪክ ኢትዮጵያ ማለት በፀሀይ የተቃጠለ ፊት ያለው ህዝብ ማለት ነው። ይህን የኛ ሀገር ቀደምት የታሪክ ፀሀፊዎችም ተገንዝበውታል። ለምሳሌ ተክለፃዲቅ (1951፡12)ን ይመልከቱ። በጥንታዊ ግሪክ ፀሀፊዎች ስለዚህ ሀገርና ህዝብ ያለውን አጠቃቀም፣ በአንደኛው ክፍለዘመን የነበረው ስትራቦ ጂኦግራፊያ በሚለው መፅሀፉ በምዕራፍ አንድ በዝርዝር የቃኘበትን ክፍል መመልከት ጠቃሚ ነው።
የኦሪት ዘፍጥረትን ወደግሪክ በአራተኛው መቶ ቅጋአ ሲመልሱ ኩሽ የሚለውን ኢትዮጵያ ብለውታል። ይህ የግሪኩ ስራ ሴፑጊነት በመባል የሚታወቀው ነው። በዚህ ስራ በእብራይስጡ ኩሽ የሚለውን የተረጎመው ኢትዮጵያ እያለ ነው ። ኢትዮጵያ ማለት የተቃጠለ ፊት ማለት ነው። በሀገር ስምነትም ጥቁር ህዝብ የሚኖርበትን አፍሪካንና የተወሰነ የኤስያን ክፍልም ያመለክት ነበር። የዚህ ቃል ፍቺ መለጠጥ ኩሽ ወይም ኢትዮጵያ አፍሪካን ባጠቃላይ አንዳንዴ ሲያመለክት በመጥበብ ደግሞ የጥንቱን ኩሽ ግዛት ያመለክታል። ይህን ጉዳይ፣ የኛ ፀሀፊዎች ሳይቀሩ የተገነዘቡት ጉዳይ ነው። ለምሳሌ፣ ኪዳነወልድ ክፍሌን (1948)፣ ኅሩይ ወልደስላሴ (1999) እንዲሁም ተክለፃዲቅ መኩሪያን ከብዙ በጥቂቱ ይመልከቱ።
የቃሉ በሀገር ስምነትም ሆነ በህዝብ ስምነት የነበረው ውክልና በታሪክ ሁልግዜ አንድ አልነበረም። ከላይ በመፅሀፍ ቅዱስ ላይ እንደተመለከትንው በታሪክ ፀሀፊዎችም ያለው አጠቃቀም እንደታሪክ ፀሀፊው የጂኦግራፊ እውቀት ይወሰን ነበር። ከክርስትና በፊት በግሪኮች ስላለው አጠቃቀም ዳሰሳ የአንደኛው መቶ ክፍለዘመን የነበረውን ስትራቦን መመልከት ጠቃሚ ነው። ስትራቦ እራሱ ኢትዮጵያ ሲል መላው አፍሪካን የሚያካትት ነው። እዚህ ላይ ጃክሰን (1939:4-5) ስታሮቦ እና ከሱ በፊት የነበሩት ስለቃሉ ያላቸውን አጠቃቀም የገለፀውንም ይመልከቱ። በግሪኮችና በሮማኖች ቃሉ ስለነበረው አጠቃቀምና ስለአጠቃላይ ጥቁር ህዝቦች ስኖውደንን (1970) መመልከቱ ጠቃሚ ነው።
ኢትዮጵያ በታሪክ ለአሁኒቷ ሀገር መጠሪያ እራሱ ተወላጁ አውሎት የምናገኛው ወደ አራተኛው ክፍለዘመን አካባቢ ነው። በቀዳሜ ክፍሎች እንደገለፅንው ኢዛና ግዛቶቼ ባላቸው ስር በግሪኩ ኢትዮጵያ ብሎ የጠቀሰው በሳቢያን እና ግዕዝ ‘ሀበሻ’ የሚለውን የሚመለከት ነው። ይህ ግዛት ከሰሜን ኢትዮጵያ ይዞ በአክሱማውያን ይተዳደር የነበረውን ቢያንስ እስከማዕከልዊ ኢትዮጵያ ያለውን የሚያካታት ነው። ኢዛና ግዛቴ ብሎ ከዘረዘራቸው ውስጥ ጽያሞ በምዕራብ ኢትዮጵያ ጋምቤላን የሚመለከት ነው (ስርግው 1972፡94ን ይመለከቱ)። የሚገርመው አንዳንድ የኩሽ ሰዎችም ሀገራቸውን ኢትዮጵያ ያሉበት መረጃዎች አሉ። ለዚህ ዋናው ተጠቃሹ የስድስተኛው ክፍለዘመን ጋአ የሲልኮ ፅሁፍ ነው (በጅ 1928፡114ን ይመልከቱ)።
***
ታሪካዊው የኩሽ/ኑብያ ስርወመንግሥት በአፍሪካ የነበረ የጥቁሮች መንግሥት መሆኑ ጥያቄ የለውም። ይህ መንግስትን ግሪኮች ኢትዮጵያ ይሉት ነበር። ኩሽም ሆነ ኢትዮጵያ ከጥቁረት ጋር እየተያያዘ ለመላው አፍሪካና ሌሎች ጠቆር ላሉ ህዝቦችና እነዚህ ህዝቦች ለሚገኙባቸው ሀገሮች ሲውል ቆይቷል። የአብረሀም እምነት፣ ስለፍጥረት ትንታኔ ሲሰጥ አንድም ከዚህ ጋር እያዛመደ፣ አንዳንዴም ከዚህ እየዘለለ ማቅረቡን አይተናል። ኩሽ በመፅሀፍ ቅዱስ ያለው እሳቤ ሙሉ በሙሉ ከታሪካዊው ኩሽም ሆነ ከህብረተሰቡ የዘርም ሆነ የቋንቋ ግንኙነት/ዝምድና አንድ ነው ማለት አይቻልም። ለምሳሌ፣ ከነኣን የኩሽ ወንድም የሀም ልጅ ተደርጎ ሲቀርብ፣ እስራኤሎች ደግሞ ከሀም ወንድም ከሴም የተወለዱ ተደርገው ቀርበዋል። ከነአን ይናገሩት የነበረው ቋንቋ፣ ከእብራይስጥ ጋር በጣም የሚቀራረብ የዘዬ ያህል ሊታይ የሚችል የንግግር አይነት ነው። እነዚህ ህዝቦች የሚኖሩትም አንድ ቦታ ወይም ጎን ለጎን ከእራኤሎች ጋር ነበር። ለእስራኤሎች ከእነዚህ ህዝብ በላይ በዝምድና የሚቀርባቸው አልነበረም። እስራኤሎች በኦሪት ያለውን ታሪክ ሲያቀናብሩ ከከነአኖች ጋር ደመኛ ስለነበሩ፣ ከነአኖችን ከነሱ በዝምድና ማራቅ ብቻ ሳይሆን፣ የእግዚአብሄርም እርግማን እንዳለባቸው በማድረግ ለማቅረብ ሞክረዋል የሚል ግምት አለ። ከነአን የኩሽ ወንድም ሊያስብላቸው የቻለውም ምክንያቱ ይህ ሊሆን ይችላል። ኑምሮእድ የባቢሎን/የአካድያን መስራች ተደርጎ የተወሰደው ካየን አካዶች ሴሚቲክ እንጂ የኩሸቲክ ቋንቋ ወገን ተናጋሪ አይደሉም። ስለዚህም በእብራይስጥ ቋንቋ እራሱ ኩሽን ከጥቁረት ጋር ማያያዝ የተጀመረው ጎልደንበርግ እና ሌሎችም በርካታዎች እንዳሉት የግሪኩን ትርጉም በመመልከት ወደኋላ ላይ የመጣ ነው።
3 ኩሸቲክ
ኩሸቲክ በአፍሮኤስያዊ ስር ለሚመደቡ ቋንቋዎች (እና እነዚህን ቋንቋዎች ለሚናገሩ ህዝቦች) መጠሪያ የሚውል የቤተሰብ ስም ነው። በዚህ ቤተሰብ ስር ባሁኑ ወቅት የሚመደቡት፤ (1) ማእከላዊ ኩሸቲክ፣ (2) ሰሜን ኩሸቲክ፣ (3) ደቡብ ኩሸቲክ፣ እና (4) ምስራቅ ኩሸቲክ ናቸው። ኦሞቲክ በቀደምት ስራዎች፣ ምዕራብ ኩሸቲክ በሚል በዚሁ የቋንቋ ቤተሰብ ስር ይመደብ ነበር። ፍለሚንግ በተለያዩ ስራዎች ይህ የቋንቋ ቤተሰብ እራሱን ችሎ (በአፍሮኤስያዊ ስር) አንድ የቋንቋ ቤተሰብ እንደሆነ ካሳየ በኋላ በኩሸቲክ ስር የመመደቡ ሁኔታ ከሞላ ጎደል ቀርቷል። ባሁኑ ወቅት በዚህ ጉዳይ ብዙም የሚያከራክር አይደለምና የኦሞቲክን ጉዳይ እዚህ አናየውም። ቋንቋና ነገድ በኢትዮጵያ ቅፅ ሁለትን ይመልከቱ። ለተለየ አመለካከት ግን ዛቦርስኪ (1986)ን ይመልከቱ።
ኩሽ የሚለውን ቃል ለቋንቋ ቤተሰብ እና ያንን ቋንቋ ለሚናገሩ ህብረተሰብ ማዋል የተጀመረው ሴም የሚለውን ቃል ለዚሁ ተግባር መዋሉን በማስተዋል ነው። በኩሸቲክ እና በሴሜቲክ ቋንቋዎች መሀከል መመሳሰል መኖሩን ማስተዋል የተጀመረው ወደኋላ እስከ 17ኛው ክፍለዘመን ይሄዳል (ላምበርቲ 1991፡52)። ሴማዊ ያልሆኑ ግን ከሴም ቋንቋዎች ጋር የሚመሳሰሉ ቋንቋዎች ሲገኙ በ19ኛው ክፍለዘመን እነዚህ ቋንቋዎች ሀሜቲክ የሚል ስያሜ ተሰጣቸው። አሁን አፍሮኤስያዊ የሚባለው ግዙፍ የቋንቋ ቤተሰብ በመነሻው የሚታወቀው ሀሚቶ-ሴሚቲክ በመባል ነበር። በወቅቱም ጥናቶቹ የሚያተኩሩት ሀሜቲክ የተባሉትን ከሴሜቲክ ቋንቋዎች አንፃር መተንተን ላይ ነበር። ሀሜቲክ የተባሉት ቋንቋዎች ግን በውስጣቸው የሴምቲክ የቋንቋ ቤተሰብ ያህል የሚታዩ በርካታ ቡድኖች የሚመሰርቱ መሆናቸው ሲታወቅ ይህን ስያሜ በመተው እራሳቸውን ችለው በተለያዩ ስያሜዎች መጠራት ተጀመረ። የቋንቋው የቤተሰብ ስያሜም ተለውጦ አፍሮኤስያዊ ተባለ። እዚህ ላይ ልብ ማለት የሚገባን በአፍሮኤስያዊ ደረጃ የሚታዩ በአፍሪካ ደረጃ ብቻ ቢያንስ ሌሎች ሶስት የቋንቋ ግዙፍ ቤተሰቦች መኖራቸው ነው። በመፅሀፍ ቅዱስ እሳቤ ከሄድን እነዚህ ብቻ ሳይሆን በአለማችን ያሉ ሁሉ የቋንቋ ግዙፍ ቤተሰቦች አንድ ብቻ በሆኑ ነበር። የቀረው ያፌት ነውና። ሀሜቲክ፣ ሴሜቲክ የሚሉት ቃላት ከመፅሀፍ ቅዱስ ካለው ቢወሰዱም በቋንቋ ቤተሰብ ስያሜነታቸው ፈፅሞ የመፅሀፍ ቅዱስን የዘር ግንድ እሳቤ መሰረት ያደረጉ አይደለም። ይህ ባለመሆኑም ነው አሁን ይህ ቃል ታላቅ የቋንቋ ቤተሰብ አፍሮኤስያዊ የሚባለው። ይህንንም ትቶ ሌላ ማለት ይቻላል። በርግጥም ሌሎችም ስያሜዎች አሉ። ለዝርዝሩ ሆጅ (1976:43)ን ይመልከቱ።
3.1 የኩሽ ቋንቋዎች የእርስ በርስ ግንኙነት እና ምደባ
ኩሸቲክ ተዘውትረው ከሚጠሩት ስድስት የአፍሮኤሽያዊ ታላቅ ቤተሰብ ቅርንጫፎች ውስጥ አንደኛው ቤተሰብ ተደርጎ ቢወሰደም፣ ይህ ምደባ ያልለቀለት አይደለም። ኩሸቲክ እንደተቀሩት ቤተሰቦች በእኩል ደረጃ የሚታይ አንድ ቤተሰብ ተደርጎ መወሰድ አይገባውም የሚሉ ትንሽ የማይባሉ ጥናቶች አሉ። ቀረብ ብለን ስንመረምርም የምናገኘው እውነታ ከእነዚህ ጥናቶች ጋር ተመሳሳይ ነው፤ በኩሸቲክ ቋንቋዎች ውስጥ ያለው ግንኙነትም ጥብቅ አይደለም። በእያንዳንዳቸው ንኡሳን የቋንቋ ቤተሰቦች ውስጥ ያለው ክፍፍል በየወቅቱ እየታደሰ ያለ ከመሆኑም በላይ፣ በየክፍሎቹ መሀከል ያለው ግንኙነት እንኳ ገና መፍትሄ አላገኘም። ለዚህ አንደኛው ምክንያት በየቋንቋዎቹ ላይ አጥጋቢ ጥናት አለመደረጉ ነው። ትንሽ የማይባሉት ቋንቋዎች ገና መሰረታዊ የሰዋስው ጥናት እንኳ ያልተደረገባቸው ናቸው። በማናቸውም የሀገራችን ቋንቋዎች ላይም ቢሆን አጥጋቢ ጥናት ተደርጓል የሚያስብለን ደረጃ ላይ አይደለንም። ትንሽ ጥናት በተደረገባቸው ቋንቋዎች ላይ እንኳ ያለው ሁኔታ በታች ደረጃ በአንዳንዶቹ ለምሳሌ ኮንሶና ኦሮምኛ፣ ሱማልኛና ሬንድባሬ፣ የአገው ቋንቋዎች፣ የደጋማው ኩሸቲክ ቋንቋዎች መሀከል እርስ በርስ ግልፅ የሆነ ዝምድና ቢኖርም ወደላይ በሄድን ቁጥር (ማ. ከፍ ባለ የቤተሰብ ደረጃ ሲደርስ)፣ ግንኙነቱ በጣም ደካማ/ስስ ነው። ይህም ዝምድና አብዛኛው የተወሰኑ ምእላዶችን ከመያዝ ላይ የመጣ እንጂ በመሰረታዊ የቃላት ደረጃ ግንኙነቱ በጣም አናሳ ነው። በምዕላድ ደረጃም ቢሆን በኩሸቲክ ስር የተመደቡት ከሌሎቹ በበለጠ ይቀራረባሉ ማለት አይደለም። ለምሳሌ፣ ቤንደር (1997ሀ&2003) በኩሸቲክ ስር ያሉትን ንዑስ ቤተሰቦች ያስቀመጣቸው በእኩል ደረጃ ከበርበር እና ሴሜቲክ ጋር ነው። በአፍሮኤስያዊ ስር የራሳቸውን ክፍል ይዛመዳሉ ብሎ ማክሮ-ኩሸቲክ በሚል ስያሜ ስር የመደባቸው በእኩል ደረጃ የሚታዩ ቡድኖች ከበርበርና እና ሴሜቲክ ተርታ፣ ማዕከላዊ ኩሸቲክ/አገው፣ ቤጃ፣ ደጋማው ምስራቅ ኩሸቲክ፣ እና ቆላማው ምስራቅ ኩሸቲክ (ደቡብ ኩሸቲክን ጨምሮ) ናቸው (ቤንደር 2003: 29)። ኦሬልና ስቶልቦቫ (1995) በኩሸቲክ ስር ባሉት ንኡሳን ቤተሰቦች የእርስ በእርስ ግንኙነት ከቤንደር ጋር ተመሳሳይ አከፋፈል ሰንዝረዋል። እንደነዚህ ሰዎች ከሆነ፣ በኩሸቲክ ንዑሳን ቤተሰቦች ስር የሚታየው መመሳሰል አይነታዊ ነው።
3.2 የኩሽ ቡድኖች ዳሰሳ
ኩሸቲክ ቤተሰብን ሰሜን ኩሸቲክ (ቤጃ)፣ ማእከላዊ ኩሸቲክ/አገው፣ ምስራቅ ኩሸቲክ፣ እና ደቡብ ኩሸቲክ በሚል የሚታየው የተለመደ ክፍፍል ከቀድሞው የነበረ ወይም በሁሉ ስምምነት ያለበት አይደለም። የዚህ ምደባ በተለይ በግሪንበርግ (1963) የቀረበ ነው። ግሪንበርግ ኩሸቲክን የከፋፈለው ሰሜን ኩሸቲክ፣ ደቡብ ኩሸቲክ፣ ማእከላዊ ኩሸቲክ፣ ምስራቅ ኩሸቲክ፣ እና ምእራብ ኩሸቲክ በሚል ነው። ከላይ እንደገለፅንው፣ የኋለኛው በአሁኑ ግዜ ለብቻው ተገንጥሎ የወጣውን ኦሞኦቲክን የሚመለከት ነው። የተቀሩት አራቱ ምድቦችም አከፋፈል ቢሆን በሁሉ ተቀባይነት ያለው አይደለም። የኩሸቲክ ውስጥ ምደባ ከስራ ስራ አብዛኛውን ግዜ ይለያያል። በአንዳንድ ስራዎች ደቡብ ኩሸቲክ የሚባለው እንዳለ ቀርቶ በምስራቅ ኩሸቲክ ተጠቃሎ ይገኛል። እንደዚሁም ማእከላዊ ኩሸቲክ በምስራቅ ኩሸቲክ ውስጥ ተመድቦ የምናገኝበትም አጋጣሚ አለ። በዚህ ክፍል ስለእነዚህ ቡድኖች መጠነኛ ዳሰሳ እናደርጋለን። ይህን ደሳሰችንን የምናደርገው ከላይ በጠቀስናቸው አራት ምድቦች፣ ማለትም ሰሜን ኩሸቲክ፣ ማእከላዊ ኩሸቲክ፣ ደቡብ ኩሸቲክ እና ምስራቅ ኩሸቲክ በሚሉ ምድቦች ስር ነው። ይህን ያደረግንው ምደባው የተዘወተረ ከመሆኑ የተነሳ እንጂ ትክክል ነው ከማለት አይደለም።
3.2.1 ማእከላዊ ኩሸቲክ
ማእከላዊ ኩሸቲክ የአገው ቋንቋዎች በመባልም የሚታወቁት ናቸው። እነዚህ ቋንቋዎች ኻምጣንጋ፣ ቅማንትነይ፣ አዊ፣ እና ቢለን ናቸው። አሁን የጠፋው ከይላ በዚህ የቋንቋ ቤተሰብ ስር የሚመደብ ነው።
ኻምጣንጋ በማእከላዊ ወሎ የሚነገር ቋንቋ ነው። ህብረተሰቡ ኽምጣ ይባላል። ቅማንትነይ የቅማንት ብሄረሰብ የሚናገረው በጎንደር ያለ ቋንቋ ነው። ይህ ቋንቋ በመጥፋት ላይ እንዳለ ይታወቃል (ዘለዓለም ልየው 2003ን ይመልከቱ)። አዊ በአዊ ዞን በጎጃም ክፍለሀገር የሚገኝ ነው። ቋንቋው በርካታ ዘዬዎች በውስጡ እንዳሉት ይገመታል። ህብረተሰቡ አዊ ይባላል (ተሾመ 2015 እና በዚያ ላይ የተጠቀሱ ስራዎችን ይመልከቱ)። ቢለን በኤርትራ የሚገኝ ነው። እነዚህ አራቱም ባንድ ወቅት ምናልባትም ወጥ የሆነ ሀገር ይዘው እንደነበር ይገመታል። ልክ ሰሜን አርጎብኛ ከአማርኛና ከደቡብ አርጎብኛ ቋንቋዎች ይልቅ የአባት ማእከላዊ ደቡብ ኢትዮ-ሴማዊ ቋንቋን ጥንታዊ ቅርፅ የሚያንፀባርቅ ነው ተብሎ እንደሚወሰድ ሁሉ፣ አውንጊም ከሁሉም የማእከላዊ ኩሸቲክ ቋንቋዎች ጥንታዊ ቅርፅ የያዘ ነው ተብሎ ይገመታል (ዛቦርስኪ 1984ን ይመልከቱ)።
የአገው ቋንቋዎች ምንም እንኳ ኩሸቲክ ቢባሉም ከሌሎች ኩሸቲክ ከሚባሉት የቋንቋ ቤተሰቦች ጋር ያላቸው ግንኙነት ግልፅ ነው ማለት አይደለም። ሄትዝሮን (1980) እና ዛቦርስኪ (2001) ማእከላዊ ኩሸቲክ እራሱን የቻለ የኩሽ ክፍል ሳይሆን በምስራቅ ኩሸቲክ ክፍል እንዲካተት ሀሳብ አቅርበዋል። ሄትዝሮን በተለይ ከደጋማው ምስራቅ ኩሸቲክ ጋር አንድ ግንባር አድርጎታል። ሄትዝሮንና ዛቦርስኪ የማእከላዊ ኩሸቲክን ራሱን የቻለ ቅርንጫፍነት የሞገቱት አንዳንድ የስነምዕላድ ባህርያትን በመያዝ ነው። ለምሳሌ፣ ዛቦርስኪ ቅድመቅጥያ የሚወስዱ ግሶችን መሰረት በማድረግ ነው። በሌላ በኩል በመሰረታዊ ቃላት ደረጃ የአገው ቋንቋዎች ከሌሎቹ ኩሸቲክ ቋንቋዎች ያላቸው ዝምድና ለሴሜቲክ ቋንቋዎች ካላቸው የተለየ አይደለም። በዚህ ምክንያት አንዳንድ ጥናቶች፣ ለምሳሌ፣ ቤንደር (1997 & 2003)ን ይመልከቱ፣ የሴም ቋንቋዎችን ከሌሎቹ የኩሽ ቋንቋ ቤተሰቦች በእኩል ደረጃ መመደብ እንደሚገባቸው ይገልፃሉ። አፕልያርድም (2011:39) በእያንዳንዱ ኩሸቲክ የቋንቋ ክፍለ ቤተሰብ ውስጥ ያለው ልዩነት ባጠቃላይ ሴሜቲክ ውስጥ ካለው አይተናነስም ይላል። መረጃዎችና ሰፊ ጥናቶች ሲገኙ አሁን ኩሽ የተባሉት ልክ ኦሞቲክ ኩሽ አይደለም እንደተባለው ሌላ ስያሜ ወጥቶላቸው ለብቻቸው ሊቀመጡ ወይም ባንድ ሊጣመሩ ይችላሉ። የሌሎቹ የኩሽ ቋንቋዎች ቤተሰቦችም የእርስ በእርስ ግንኙነት ይህን ያህል የጠበቀ አይደለም። እስቲ በዝርዝር ሌሎቹንም እንመልከታቸው።
3.2.2 ሰሜን ኩሸቲክ
ሰሜን ኩሸቲክ ባሁኑ ግዜ ውክልናው በቤጃ ነው። ይህ ቋንቋ አንዳንዶች ከኩሽ በመጀመሪያ ላይ የተገነጠለ ነው ሲሉ፣ የተወሰኑ ደግሞ ለምሳሌ ሮበርት ሄትዝሮን (1977/1980) ፈፅሞ በኩሽ ቤተሰብ መመደብ የለበትም ይላሉ። እንደኋለኞቹ አባባል ቤጃ ራሱን ችሎ በቀጥታ ከአፍሮኤስያዊው ልዕለ ቋንቋ/ታላቅ ቤተሰብ የወረደ ተደርጎ መቆጠር ይገባዋል። ቤጃ በኩሸቲክ ስር ሊመደብ የሚያስችለው አንዳንድ ከሌሎች ኩሸቲክ የሚጋራቸው ድህረቅጥያዎች አሉት የሚልም ይገኝበታል (ዛቦርስኪ 1984:128ን ይመልከቱ)። የተለያዩ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ከሆነ፣ ቤጃ በኩሸቲክ ስር መመደብ አለበት የሚባል ከሆነ፣ ከዚህ ቤተሰብ በመጀመሪያ የተገነጠለ ተደርጎ መወሰድ ይገባዋል ነው። ማውሮ ቶስኮም የኩሸቲክ እና ኦሞቲክ ቅኝት በሚለው መጣጥፉ የተለያዩ ባለሙያዎችን ስራዎች በቃኘበት ስራ ውስጥ ተመሳሳይ ድምዳሜ ላይ ደርሷል (ቶስኮ 2003:87)።
ቤጃዎች ጥንት የኩሽ ግዛት በተዳከመች ግዜ በ1ኛው ቅጋአ ሜሮኤን ተቆጣጥረው ዳግም እንዲያንሰራራ ጥረው ነበር። እራሳቸው ግን በቀጥታ ጥንታዊ የኩሽ ግዛትን የመሰረቱ ተደርገው አይወሰዱም። አብዛኛው አሰፋፈራቸውም በባህር ጠረፉ ነው። ቤጃ በግዕዝ በኢዛና ፅሁፍ (DAE 11) ላይ ብጋ በሚል የተገለፀው ነው። እነዚህ ህዝቦች በኢዛና ስር ነበሩ።
3.2.3 ደቡብ ኩሸቲክ
ደቡብ ኩሸቲክ ከኢትዮጵያ ውጭ በታንዛንኛ፣ በኡጋንዳ፣ እና በኬንያ የሚነገሩ ቋንቋዎችን የሚመለከት ነው። ይህ የቋንቋ ቤተሰብ በጣም አከራካሪ ነው። በዚህ ቋንቋ ቤተሰብ ስር የተመደቡ ቋንቋዎች ካንድ ወላጅ ደቡብ ኩሸቲክ መምጣታቸው በጣም አጠያያቂ ነው። እራሱ ደቡብ ኩሸቲክ የሚለው ምደባ በጣም አጠያያቂ እንደሆነ የዛቦርስኪን (1984) ጥናት መመልከቱ ይበቃል። እንደዛቦርስኪ ከሆነ በዚህ ስር የተመደቡት አንዳንዶቹ ቋንቋዎች በምስራቅ ኩሸቲክ ስር ሊመደቡ ይችላሉ። በዚህ ጉዳይ ላይ ከብዙ በጥቂቱ ዛቦርስኪ (1984)ን እና በዚያ የተጠቀሱ ስራዎችን ይመልከቱ።
3.2.4 ምስራቅ ኩሸቲክ
ምስራቅ ኩሸቲክ በሁለት ይከፈላል። አንደኛው ደጋማው ምስራቅ ኩሸቲክ የሚል ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ቆላማው ምስራቅ ኩሸቲክ የሚል ነው። የመጀመሪያው ሲዳማን፣ ከምባታን፣ ሀዲያን፣ ጌዲኦን፣ እና ቡርጂን ይይዛል። ቡርጂ ከሁሉም ይልቅ ጥንታዊ ተደርጎ ይቆጠራል (ዛቦርስኪ 1984: 133)። ቆላማው ምስራቅ ኩሸቲክ ሶማሌን፣ ኦሮሞን፣ ኮንሶን፣ አፋርን እና ሌሎች በርካታ በቁጥር አናሳ ተናጋሪ ያላቸውን ቋንቋዎች ይይዛል። ይህ የቋንቋ ቡድን ከሌሎቹ የኩሸቲክ ቤተሰቦች ይልቅ በርካታ ቋንቋዎችን የሚይዝ ነው። ከነዚህ ውስጥ ኦሮምኛና ሶማልኛን መጥቀስ ይቻላል።
ለኦሮምኛ በጣም ቅርብ የሆነው ቋንቋ ኮንሶኛ ነው። እነዚህ ሁለቱ ኮንሶይድ ወይም ኦሮሞይድ በሚል በአንድ ቡድን ይመደባሉ። የኮንሶ ህዝብና የኦሮሞ ህዝብ በባህልና በትክለ ሰውነት/መልክ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ስለሚለያዩ፣ በቋንቋ ቢዛመዱም ሁለቱ ህዝቦች ጥንተ አመጣጥ አንድ ላይሆን ይችላል ከሚል የተለያየ መላምት አለ። ለምሳሌ ፓውል ብላክ (1975)ን ይመልከቱ።
4 ማጠቃለያ
ኩሽ የሚለው ቃል በመፅሀፍ ቅዱስ እንዲሁም በጥንታዊ ግብፆች ስራ ውስጥ ይገኛል። ጥንታዊ ግብፆች ኩሽ የሚለውን (ወይም የዚህን ዝርያቃል) የሚጠቀሙበት ከነሱ ግዛት በስተደቡብ በአሁኑ ግዜ በሱዳን ከዛሬ አራትና አምስት ሺህ ዓመት ገደማ ጀምሮ የነበረውን የከርማን ስርወመንግሥትና ከዚያም በማስከተል በእዚሁ በሱዳን እስከ አራተኛው ክፍለዘመን ድረስ የነበሩትን ስልጣኔዎችና መንግስታት ለማመልከት ነው። በመፅሀፍ ቅዱስ ደግሞ ኩሽ በዋነኛነት ነገድን ያመለክታል። በቋንቋ ቤተሰብ ስያሜነቱ፣ ኩሸቲክ ይባላል።
በክፍል ሶስት በቋንቋዎች መሀል ስላለው ግንኙነት ያነሳንው ኩሸቲክ የሚለው ስያሜ ከጥንት ጀምሮ ኩሽ በመባል የሚታወቁ ህዝቦች የሚናገሩትን ቋንቋዎቹ ምንም አጠያያቂ ባልሆነ መንገድ እርስ በርስ የሚዛመዱ ታሪካዊ መሰረት ያላቸው መሆኑን የሚያመለክት አለመሆኑን ለማመልከት ነው። በርግጥ፣ የተወሰኑ ፊደል የቆጠሩ ሰዎች ካልሆኑ በቀር ባሁኑ ወቀት የትኛውም የኩሸቲክ ቋንቋ ተናጋሪ ኩሽ ነኝ ሲል አይሰማም። ኩሽ ስለመባሉም የሚያውቀው ነገር የለም። በህዝቡ ዘንድ ያለው የተለየ ነው። ለምሳሌ ቤተ እስራኤል በሚል ወደ እስራኤል የሄዱት የአገው ወገን የነበሩ ህዝቦች ናቸው። እንዚህ ህዝቦች ከጥንትም አይሁዶች ሆነው በግዜ ሂደት ግን አገው ሆነው ሊሆን ይችላል። ሱማሌዎችንም ብንወስድ የአረብ ሊግ መሆናቸውን እንኳ ከፖለቲካ/ሀይማኖት ጋር ብናያይዘው እንደ ኢሳ፣ ዳሮድ የሚባሉት ጎሳዎች የሴም ዘሮች ነን የሚሉ ናቸው። በርግጥ የጎሳቸው መስራች ተደርገው የሚቆጠሩት ከአረብ ሀገር መጥተው ሊሆን ይችላል (ሌዊስ 1998፡18ff.)። በሲዳማ ህዝቡ ከእስራኤል እንደመጣ የሚገልፅ አፈታሪክ አለ። ለህብረተሰቡ የትመጣ አፈታሪክ የሀይማኖት ተፅዕኖ ትልቅ ቦታ ቢኖረውም፣ በሁሉም ቦታ የጥንቱን ማንነት ያስተዋል ማለት አይቻልም። በየትኛውም ወቅት ኩሽ አሁን በዚህ ስም የሚጠሩ ቋንቋ ተናጋሪዎችን ነጥሎ ለማመልከት የዋለበት ግዜ የለም።
በሀገራችን ኢትዮጵያ የኩሽ ምድር መባሉ ዋናው መሰረት የአለማችንን ህዝብ በመፅሀፍ ቅዱስ እሳቤ አለምን ከመተርጎም የመጣ ነው። በአይሁዶች በወቅቱ በነበራቸው ግንዛቤ ለራሳቸው ህብረተሰብ የፃፉትን ይዘው የአለምን ህዝብ መግለፁ ሳይሆን፣ ያንን እውነት ነው ብሎ አለማዊው ፖለቲከኛ መጠቀሙ ይመስላል ትልቁን ስህተት ያመጣው።
ዋቢፅሁፎች
ሀሚልተን እና ፋልኮነር = Hamilton, H. C. and W. Falconer (trans). 1903. The Geography of Starbo: Literally Translated, With Notes. Vol.1. Cambridge: Deighton, Bell & Co., New York: The Macmillan Co., Bombay: A. H. Wheeler & Co
ሀፋስ-ሳኮስ Hafsaas-Tsakos, Henriette(2009)'The Kingdom of Kush: An African Centre on the Periphery of the Bronze Age World System Norwegian Archaeological Review,42:1,50 — 70
ሄትዝሮን = Hetzron, Robert. 1980. The Limits of Cushitic. Sprache und Geschichte in Afrika. 2: 7-126.
ኅሩይ ወልደስላሴ። 1999። የኢትዮጵያ ታሪክ ከንግስተ ሳባ እስከ ታላቁ የአድዋ ድል። አዲስ አበባ፤ ሴንትራል ማተሚያ ቤት።
ሆጅ = Hodge, Carleton T. 1976. Lismaric (Afroasiatic): An Overview. In Bender, M. L. (ed.). The Non-Semitic Languages of Ethiopia. Pp. 43-66. East Lansing: Michigan State University.
ላምበርት = Lambert, T. Series producer. 2015. First Peoples. Corporation for Public Broadcasting.
ሌክላንት = Leclant, J. 1981. The Empire of Kush: Napata and Meroe. In G. Mokhtar. (ed.) General History of Africa. Vol. II: Ancient Civilizations of Africa. Pp. 278 - 297. Berkeley: University of California Press.
ሙንሮ-ሄይ = Munro-Hey, Stuart C. 1991. Aksum: An African Civilisation of Late Antiquity. Edinburgh: University Press.
ሙክታር = Mokhtar, G. with the collaboration of J. VercoutterI. 1981. Introduction. In G. Mokhtar. (ed.) General History of Africa. Vol. II: Ancient Civilizations of Africa. Pp. 1 - 26. Berkeley: University of California Press.
ሞላ = Mola, P. J. D. (2013, March 14). Interrelations of Kerma and Pharaonic Egypt. Ancient History Encyclopedia. Retrieved on 01-12-2020 from .
ሰርቪስ = Service, P. F. 1998. The Ancient African Kingdom of Kush (Cultures of the Past.New York: Benchmark Books.
ስርግው = Sergew Hable Sellassie. 1972. Ancient and Medieval Ethiopian History to 1270. Addis Ababa: Haile Sellassie I University.
ስኖውደን = Snowden, Frank M., Jr. 1970. Blacks in Antiquity: Ethiopians in Greco-Roman Experience. Cambridge: The Belknap Press of Harvard University Press.
ሪሊይ= Rilly, Claude (March 2004) "The Linguistic Position of Meroitic", Sudan Electronic Journal of Archaeology and Anthropology.
ራትክሊፍ = Ratcliffe, Robert R. 2003. Afroasiatic Comparative Lexica: Implications for Long (and Medium) Range Language Comparison. In E. Hajicova, A. Kotesovcova, & J. Mirovsky, Eds. Proceedings of XVII International Congress of Linguists. Prague: Matfyz Press.
ራክሃም= Rackham, H., trans. 1942. Pliny, Natural History, Vol. 2, Libri III-VII. Cambridge, MA: Harvard University Press.
ራይሊ = Rilly, Claude. 2004. The Linguistic Position of Meroitic. Sudan Electronic Journal of Archaeology and Anthropology.
ሮዋን = Rowan, Kirsty. 2006. Meroitic - An Afroasiatic Language? SOAS Working Papers in Linguistics 14:169–206.
ሮዋን = Rowan, Kirsty. 2006. Meroitic: A Phonological Investigation. PhD thesis, SOAS (School of Oriental and African Studies).
ሮዋን = Rowan, Kirsty. 2011. Meroitic Consonant and Vowel Patterning. Lingua Aegytia, 19.
ሸሪፍ = Sherif, N. M. 1981. Nubia before Napata (-3100 to -750). In G. Mokhtar. (ed.) General History of Africa. Vol. II: Ancient Civilizations of Africa. Pp. 245 - 277. Berkeley: University of California Press.
ባየርብራየር = Bierbrier, Morris L. 2008. Historical Dictionaryof Ancient Egypt,Second Edition.Lanham, Maryland; The Scarecrow Press, Inc.
ባጅ = Budge, E. A. Wallis. 1928. A History of Ethiopia Nubia and Abyssinia. According to the Hieroglyphic Inscriptions of Egypt And Nubia, and the Ethiopian Chronicles. London: Methuen &Co Ltd.
ቤንደር = Bender, M. L. 1997. Upside-Down Afrasian. Afrikonistische Arbeitspapiere. 50: 19-34.
ቤንደር = Bender, M. Lionel. 1997ለ. The Nilo-Saharan Lanaguages: Comparative Essay. 2nd Edition. Munchen: LINCOM Europa.
ቤንደር = Bender, M. Lionel. 2003. Northeast Africa: A Case Study in Genetic and Areal Linguistics. APAL. 1: 21-45.
ቤንደር = Bender, Marvin Lionel. 1981. The Meroitic problem. In Bender, M. L., editor. Peoples and cultures of the Ethio-Sudan borderlands. pp. 5–32. East Lansing, Michigan: African Studies Center, Michigan State University.
ብሬየር = Breyer 2007. In Uhlig, Siegbert (ed.). Encyclopaedia Aethiopica: Vol. II. Pp. Wiesbaden: Harrassowitz Verlag.
ቦኔት = Bonnet, C. 1983. Kerma. An African Kingdom of the 2nd and 3rd millennia B.C. Archaeology36፡6; 38–45.
ተክለፃዲቅ መኩሪያ። 1951። የኢትዮጵያ ታሪክ ኑብያ-አክሱም ዛጉዬ እስከ ዐፄ ይኩኖ አምላክ ዘመን መንግሥት። አዲስ አበባ፤ ትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት።
ቶስኮ = Tosco, Mauro. 2000. Cushitic Overview. Journal of Ethiopian Studies. 33; 12: 87-121.
ቶስኮ = Tosco, Mauro. 2003. Cushitic and Omotic Overview. In M. Lionel Bender, David Appleyard, and Gabor Takacs (eds.). Afrasian: Selected Comparative-Historical Linguistic Studies in Memory of Igor M. Dlakonoff. Pp. 87-92. Miinchen: Lincom Europa.
አርኬል = Arkell, A. J. 1955. A History of the Sudan. From theEarliest Times to 1821. Athlone Press, London.
አዳም = ADAM, S. with the collaboration of J. Vercoutter. 1981. The Importance of Nubia: A Link between Central Africa and the Mediterranean. In G. Mokhtar. (ed.) General History of Africa. Vol. II: Ancient Civilizations of Africa. Pp. 226 - 244. Berkeley: University of California Press.
አፕልያርድ = Appleyard, David. 2011. Semitic-Cushitic/Omotic Relations. In Stefan Weninger (ed.). The Semitic Languages: An International Handbook. Pp. 39-53.
ኢምበርሊንግ = Emberling, Geoff. 2011. Nubia Ancient Kingdoms of Africa. New York: The Institute for the Study of the Ancient World, New York University.
ኤዲ እና ሌሎች= Eide, Tormod et al., eds. 1996. FontesHistoriae Nubiorum, vol. 2, From the Mid-Fifth to the First Century BC. Bergen: University of Bergen, Department of Greek, Latin and Egyptology.
ኤፍሬም = Ephraim Isaac (1980) Genesis, Judaism, and the ‘sons of Ham’, Slavery & Abolition: A Journal of Slave and Post-Slave Studies. 1:1, 3-17.
ኪዳነወልድ ክፍሌ። Kidanewold Kifle. 1948. Mäs’ħafä säwasɨw wämäzgäbä k’alat ħadis. Dire Dawa, Addis Ababa: Artistic Printing Press.
ክሪንግስ እና ሌሎች = Krings, M. et al. 1999. MtDNA Analysis of Nile River Valley Populations: A Genetic Corridor or a Barrier to Migration? In Am J Hum Genet 64. PP. 1166-76.
ዊሊያምስ = Williams, Bruce. 1980. The Lost Pharaohs of Nubia. In Archaeology. 33; 5: 12-21.
ዌልስቢ = Welsby, Derek A. 1998. The Kingdom of Kush: The Napatan and Meroitic Empires. Princeton, NJ: Markus Wiener.
ዘለዓለም = Zelealem Leyew. 2003. The Kemantney Language – A Sociolinguistic and Grammatical Study of Language Replacement. Cologne: Rüdiger Köppe Verlag.
ደላኒ = Delany, Martin R. 1879. The Origin of Race and Color. Philadelphia: Harper & Brother, Publishers.
ዱንሃም = Dunham, Dows. 1947. Outline of the Ancient History of the Sudan: Part V. The Kingdom of Kush at Napata and Meroe (750 B.C. To A.D. 350). In Sudan Notes and Records. 28: 1-10.
ዲክሰን = ዲክሰን = Dixon, D. M. 1964. The Origin of the Kingdom of Kush. Journal of Egyptian Archeology. 50:121-132.
ዲዮፕ = Diop, Cheik Anta. 1981. Origin of the Ancient Egyptians. In G. Mokhtar. (ed.) General History of Africa. Vol. II: Ancient Civilizations of Africa. Pp. 27 - 57. Berkeley: University of California Press.
ዲዮፕ = Diop, Cheikh Anta. 1974. The African Origin of Civilization. Chicago, Illinois: Lawrence Hill Books.
ጎልደንበርግ = Goldenberg, David M.. 2003. The Curse of Ham: Race and Slavery in Early Judaism, Christianity, and Islam። Princeton: Princeton University Press.
ማስታወሻዎች
የኩሽ ስርወመንግሥት የኩሽ ኢምፓየርም ይባላል። ይህ ሁኔታ በጥንታዊ የአክሱም መንግስትም ላይ እንዲሁ ነው። በበርካታ የታሪክ ስራዎች የአክሱም ስርወመንግሥት ‘Kingdom’ እየተባለ ቢቀርብም፣ አክሱም በውስጡ ሌሎች ስርወመንግሥቶችም ስለነበሩት፣ ገዢውም ንጉሠ ነገሥት ስለሚል፣ ኢምፓየር መባል ይገባዋል የሚል አለ። ለምሳሌ ስርግው ኃብለሥላሴ (1972)ን ይመለክቱ። በኩሽም መንግሥት የነበረው ተመሳሳይ ነው። ኩሽ በውስጡ የተወሰኑ ንኡስ ስረወመንግስታት የነበረበት ወቅት ነበር። በዚህም ኢምፓየር መባል ይገባዋል ከሚል ነው አንዳንዶች የኩሽ ኢምፓየር የሚሉት። በዚህ ስራ፣ ስረወመንግሥት የሚለውን በወጥነት ለጥንታዊ መንግስታቱ ተጠቅመናል። ይህን ያደረግንው እነዚህ መንግሥታት ኢምፓየር መባል አይገባቸውም ከሚል አይደለም። ያንን ለታሪክ ፀሀፊዎች እንተዋለን። አላማችን የኩሽ እና ከዚህ የመነጩት ቃል አጠቃቀምን መመርመር ላይ ነውና ስርወመንግሥት ስንል የተለመደውን ዘልማድ መቀጠላችን ብቻ ነው።
ምንም እንኳ አሳማኝነቱ አጥጋቢ ባይሆንም፣ ለምሳሌ አዳምስ (1985)ን ይመልከቱ፣ ብሩስ ዊሊያምስ (1980) የግብፆች ፋራኦን/የንጉሶች አስተዳደር መነሻ ኩሾች ናቸው የሚል መላምት አቅርቧል።
የዚህ ንጉስ የንግሥና ዘመኑ 2055 ቅጋአ እስከ 2004 ቅጋአ ወይማ ከ2061 እስከ 2010 አካባቢ እንደሆነ ይገመታል። ለመጀመሪያው ግምት ባየርብራየር (2008፡142)ን ይመልከቱ።
በኩሽ ስርወመንግሥት በናፓታን ዘመንና በሜሮኤ ዘመን ስለነበሩት አንኳር አንኳር ታሪካዊ ክስተቶች ጠቅለል ላለና ጭምቅ ሀሳብ ከብዙ በጥቂቱ ዱንሃም (1947:9-10)ን ይመልከቱ።
ኢዛና ማዕረጉን ሲገልፅ የጠቀሳቸው ግዛቶች የሚከተሉት ናቸው፤ “በጠላት የማይሸነፈው የመሐረም ልጅ ንጉሥ ኢዛና የአክሱም፣ የሕምያር፣ የኩሽ፣ የሳባ፣ የሀበሻ፣ የራይዳን፣ የሳልሄን፣ የጺያሞ እና የቤጃ ንጉሠ ነገሥት” (DAE 5/6/7)። ኢዛና ግዛቴ ብሎ በዘረዘራቸው ውስጥ ኩሽ በሚል ከላይ ያስቀመጠንው በግዕዙ ፅሁፍ የቀረበው ካሱ በሚል ነው። በኢዛና ፅሁፍም ኖባ እና ኩሽ/ካሱ የተለያዩ መሆናቸው በግልፅ ተቀምጧል። ለዝርዝር ትንታኔ ቀደም ካሉት ስራዎች ባጅ (1928፡ 248 እና ቀጠይ ገፆችን) ይመልከቱ።
በርግጥ የዚህ አይነት እሳቤ የሚያራምዱ በተለይ አፍሪካ-ማዕከል/Afro-centered የሆኑ ፀሀፊዎች አሉ። ይህ የተጀመረው በዋናነት ጥቁር የራሱ ስልጣኔ የለውም የሚለውን ለመቃወም ቢሆንም፣ ፀሀፊዎች ነገሩን በመለጠጥ ከራሳቸው ትክለ ሰውነት ጋር ለመዛመድ መሞከራቸው አልቀረም። ለምሳሌ ዲዮፕ (1982)ን ይመልከቱ። ዲዮፕ በሌላ ስራውም እንዲያውም ጥንታዊ ግብፅን ከምዕራብ አፍሪካው የኒጀር ኮንጎ አባል ከሆነው ዎልፍ ጋር አንድ ዘር ነው እስከማለት ደርሷል። ይህን የሚደግፍ ምንም ስነልሳናዊ መረጃ የለም። ጥንታዊ ግብፅ በማያጠያይቅ መልኩ የአፍሮኤሽያቲክ አባል ነው።
የቀለም ምስሉን ከታተሙ ስራዎች ማግኘት ስላልቻልን የወሰደንው ከሚከተለው ድረገፅ ነው፤ Retrieved on 01-20-2020
ከብዙ በጥቂቱ ቀደም ካሉት ስራዎች ላይ የሚከተለውን ይመልከቱ፤ The Encyclopaedia Britannica: A Dictionary of Arts, Sciences, and General Literature, Volume 6. Ninth Edition. New York: Charles Scribner's Sons. 1878, p. 729.
“And the sons of Ham; Cush, and Mizraim, and Phut, and Canaan” (Gn 10:6); “The sons of Ham; Cush, and Mizraim, Put, and Canaan” (1Ch 1:8). “And the sons of Cush; Seba, and Havilah, and Sabta, and Raamah, and Sabtecha” (1Ch 1:9) (Bible-King James version, 1611).
ባለፈው ክፍል እንደገለፅንው ኩሽ በግብፆችም ከሀገር ስምነት በተጨማሪ የነገድ ስምም ነበር። በኩሽ ሀገር የሚገኙ ህዝቦች ኩሽ ይባሉ ነበር። ይህን ቃል በሰዎች መጠሪያ ስምም ላይ ይገባ ነበር። ለዚህ ተዘውትሮ የሚጠቀሰው ንጉስ ካሻታ ነው።
ይህን ሰው የ1962 አማርኛ መፅሀፍ ቅዱስ ኩዝ ነው የሚለው፤ “ስለ ብንያማዊ ሰው ስለ ኩዝ ቃል ለእግዚአብሄር የዘመረው የዳዊት መዝሙር” (መዝ 7፡ መግቢያ [7፡1])።
እስካሁንም ይህን ስም የሚጠቀሙ አሉ። ለምሳሌ፣ በጣልያን በየአመቱ በአፍሮኤሽያዊ ቋንቋዎች ላይ የሚደረገው ኮንፈረንስ የሚጠራበት ሀሚቶ-ሴሜቲክ በሚል ነው።
በዚህ ጉዳይ ከላይ እዚህም እዚያም በየቋንቋዎቹ ቤተሰቦች ስር የጠቀስናቸውን ስራዎች ይመለከቱ። ለአጠቃላይ ግንዛቤ በተለይ ዛቦርስኪ (1984&1986)ን፣ ቶስኮ (2000)ን፣ እና ቤንደር (2003)ን ይመልከቱ።