የሜልበርን ተማሪዎች ከጁላይ 20 ጀምሮ ወደ ርቀት ትምህርት ሊመለሱ ነው

የቪክቶሪያ ዋና የጤና ኃላፊ ምክርን ተከትሎ የኮሮናቫይረስ ገደቦች የተጣለባቸው የሜልበርንና ሚችል ሻየር ነዋሪ ተማሪዎች ከሰኞ ጁላይ 20 እስከ ኦገስት 19 ትምህርታቸውን ከቤት ውስጥ ሆነ እንዲከታተሉ የቪክቶሪያ መንግሥት ወስኗል።

RETURN TO FLEXIBLE AND REMOTE LEARNING

Source: Getty Images

ሜልበርን ውስጥ ተስፋፍቶ ያለውን የኮሮናቫይረስ ለመግታት በተጣሉት የሶስተኛ ደረጃ ገደቦች ሳቢያ ከመጀመሪያ እስከ 10ኛ ክፍል ያሉ ተማሪዎች የሶስተኛ ተርም ትምህርታቸውን በኦንላይን ከቤት ሆነው ይከታተላሉ። 

ገደቦቹ ያልተጣሉባቸው አካባቢ ተማሪዎች በተያዘላቸው መርሃ ግብር መሠረት ከሰኞ ጁላይ 13 ጀምሮ በአካል በየትምህርት ቤቶቻቸው ተገኝተው ትምህርታቸውን ይቀጥላሉ። 

የ10ኛ፣ 11ኛ ክፍል እንዲሁም የ10ኛ ክፍል ተማሪ ሆነው የ VCE እና VCAL ክፍል ተከታታዮች ግና ከሰኞ ጁላይ 13 ጀምሮ በየመማሪያ ክፍሎቻቸው ሆነው ትምህርታቸውን ይማራሉ። 

የርቀት ትምህርቱን አዋኪነትና ፋይዳ አስመልክተው የቪክቶሪያ ፕሪሚየር ዳንኤል አንድሩስ ሲናገሩ፤

“ቀደም ሲል የኮሮናቫይረስ ተዛማጅነትን ለመግታት ልጆችን ከትምህርት ቤት አስቀርቶ ቤት ውስጥ እንዲማሩ ማድረግ አንዱ ሁነኛ ክንዋኔ እንደነበረ ሁሉ፤ አሁንም ሁነኛ የጥረቶቻችን አካል ይሆናል"

“የሶስት ገና የትምህርት ቤት ዕድሜ ላይ ያሉ ልጆች አባት እንደመሆኔ ለበርካታ ቤተሰቦች አዋኪ እንደሚሆን እረዳለሁ። ይሁንና ተማሪዎችን፣ አስተማሪዎችንና መላ ቪክቶሪያውያንን ለመታደግ የኮሮናቫይረስን መስፋፋት እንዲያዘግም ማድረግ ግድ ይለናል" ብለዋል።

የቪክቶሪያ የትምህርት ሚኒስትር ጀምስ ሜርሊኖም በበኩላቸው፤
“ወደ ርቀት ትምህርት መመለስ ለበርካቶች ፈታኝ እንደሁ አውቃለሁ። ሆኖም፤ ዳይሬክተሮቻችን፣ መምህራኖቻችን፣ ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞቻችን፣ ተማሪዎቻችንና ወላጆች ዳግም እንደሚያኮሩን እርግጠኛ ነኝ” በማለት ተናግረዋል።


Share

Published

Presented by Kassahun Seboqa Negewo

Share this with family and friends