አያሌ አውስትራሊያውያን ከነገ ጀምሮ ወደ ባሕር ማዶ ለመጓዝ መሰናዶ ላይ ባሉበት ወቅት ታይላንድ በሯ ለአውስትራሊያውያን ጎብኚዎች ክፍት መሆኑን አስታወቀች።
አውስትራሊያ ሙሉ ክትባት ለተከተቡ አውስራሊያውያንና የውጭ አገራት ዜጎች ዓለም አቀፍ ድንበሮቿን ከነገ ኖቬምበር 1 ጀምሮ ከፍታ ቅበላና ሽኝት ታደርጋለች።
ከሁለት ወራት በፊት ጭር ብላ የነበረችው ባንግኮክ ከተማ ደምቃለች።
ቀደም ሲል በቀን እስከ 23 ሺህ ሰዎች በኮቪድ-19 ይጠቁባት የነበረችው አሁን ወደ 10 ሺህ ወርዷል።
ከነገ ጀምሮ ሙሉ ክትባት የተከተቡ አውስትራሊያውያን ለምዝናናትም ሆነ ከጓደኞቻቸውና ቤተሰቦቻቸው ጋር ለመገናኘት ወደ ታይላንድ ሲገቡ ወሸባ ለመግባት ግድ አይሰኙም።
ወደ ታይላንድ እንዲዘልቁ ከተፈቀደላቸው 46 አገራት መካከል አውስትራሊያ አንዷ ናት።
በአዲሱ ድንጋጌ መሠረት ወደ ታይላንድ ለመሔድ ከጉዞዎ አንድ ሳምንት ቀደም ብለው በኦንላይንና መመዝገብና የታይላንድን ይለፍ ማግኘት ይኖርብዎታል።
ሙሉ ክትባት የተከተቡና የሕክምን ኢንሹራንስ ያለዎት ስለመሆንዎም ማስረጃ ማቅረብ ይጠበቅብዎታል።
ከበረራዎ በፊት የኮቪድ ነፃ ምርመራ ውጤት ሊኖርዎ ይገባል፤ ታይላንድ እንደደረሱም የሚደረግልዎ ምርመራ ውጤት በማግሥቱ እስከሚደርስዎ አንድ ምሽት ከሆቴልዎ ሳይወጡ መጠብቅ ይኖርብዎታል።
የምርመራ ውጤትዎ ከኮቪድ ነፃ ሆኖ ከተገኘ ከሆቴል ክፍልዎ ወጠው መሔድ ይችላሉ። ይሁንና ከአንድ ሳምንት በኋላ ዳግም ተመርምረው ውጤትዎን በሞባይል ስልክ ኧፕ ማሳወቅ ይገባዎታል።
ሆኖም በኮሮናቫይረስ የተጠቁ ከሆነ ወሸባ መግባት ግዴታዎ ይሆናል።
በዚህ ዓመት ካልሆነልዎትም በቀጣዩ ዓመት ለመጓዝ ተስፋ ያድርጉ።