የኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን የሕዳሴ ግድብ ድርድር ተራዘመ

ግብፅና ሱዳን "ቅሬታ" አሰሙ

Water negotiation

Eng. Dr Seleshi Bekele, Minister for Water, Irrigation and Energy Source: Courtesy of PD

የኢትዮጵያ የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ትናንት ሐምሌ 28 - 2012 ባወጣው መግለጫ፤ በኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን መካከል የሕዳሴ ግድብን አስመልክቶ ተጀምሮ የነበረው ድርድር መራዘሙን አስታውቋል።

ሚኒስቴር መሥሪያ ለድርድሩ መቋረጥ አስባብ ስለሆነው ጉዳይ ጉዳይ ሲገልጥ "ግብፅና ሱዳን ኢትዮጵያ ያቀረበችውን ደንብ ለመመልከት ጊዜ እንደሚፈልጉ ጠቅሰው ስብሰባው እንዲራዘም በጠየቁት መሠረት አገራቱ የውስጥ ምክክራቸውን ሲያጠናቅቁ ድርድሩን ለመቀጠል ስምምነት ተደርሷል" ብሏል።

በዚህም መሠረት ሶስቱ አገራት ግብፅ ያቀረበችውን ቀን ተቀብለው ቀጣዩን ድርድር ለመቀጠል ለነሐሴ 4 - 2012 (ኦገስት 10 - 2020) ቀን ቆርጠዋል።

የሶስቱ አገራት የሕግና የቴክኒክ ቡድናት የውኃ ሚኒስትሮች ሐምሌ 27 - 2012 በታደሙበት ወቅት የድርድሩ አጀንዳ አተኩሮ የነበረው የሶስትዮሽ ተደራዳሪ አገራቱ ባልተስማሙባቸው ጉዳዮች ላይ መክረው ከእልባት ላይ መድረስ ነበር።

ይኼው ድርድር በተካሄደበት ወቅት የደቡብ አፍሪካ፣ የአውሮፓ ሕብረትና የዩናይትድ ስቴትስ ታዛቢዎችና የአፍሪካ ሕብረት ባለ ሙያዎች ታድመዋል።

የግብፅ የውኃና መስኖ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት በበኩሉ ወደ ስብሰባው ከመግባታቸው ጥቂት ቀደም ብሎ ከኢትዮጵያ የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ረቂቅ "የግድብ ሙሌት መመሪያዎችና ደንቦች" እንደደርሱት ጠቁሞ፤ ረቂቁ "ስምምነቱ ሕጋዊ አስገዳጅነት" እንዲኖረው አላከተተም በማለት ቅሬታውን አስታውቋል።

ሆኖም ሰኞ ኦገስት 10 ወደ ድርድሩ እንደሚመለስ ገልጧል።

የሱዳን የውኃ ሃብቶችና መስኖ ሚኒስትር - ፕሮፌሰር ያሲር አባስ በበኩላቸው ረቂቁ ከኢትዮጵያ አቻቸው የደረሳቸው ወደ ስብሰባው ከመዝለቃቸው ጥቂት ሰዓታት በፊት መሆኑንና ረቂቁ የመጀመሪያው የግድቡ ሙሌት ላይ የተወሰነ እንጂ "የግድቡን አሠራር ሂደትና የዓባይ ወንዝ ውኃን" ያካተተ ባለመሆኑ መገረማቸውን ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ በኩል በተከታታይ በተደረጉ ውይይቶች የምታካሂደው ድርድር በሕዳሴ ግድብ ዙሪያ እንጂ የዓባይ ወንዝና ሕጋዊ አስገዳጅነት ባለው ስምምነት ላይ አለመሆኑን መገለጿ ይታወቃል። 

     


Share
Published 5 August 2020 2:52pm
Updated 5 August 2020 4:47pm
By Kassahun Seboqa Negewo

Share this with family and friends