ቪክቶሪያ ውስጥ በኮሮናቫይረስ የስድስት ሰዎች ሕይወት አለፈ፤ 384 በቫይረሱ ተጠቁ

***ጊዜያዊ የአረጋውያን መጦሪያ ሠራተኞች ከነገ ጀምሮ ለዕረፍት ሲወጡ ክፍያ ያገኛሉ

Dan Andrews

Victorian Premier Daniel Andrews. Source: AAP

ቪክቶሪያ ሰኞ ዕለት ካስመዘገበችው 532 አዲስ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ዛሬ ማክሰኞ ወደ 384 ዝቅ ብሏል።

ፕሪሚየር ዳንኤል አንድሩስ ዛሬ ጠዋት የስድስት ሰዎች ሕይወት በቫይረሱ ማለፉን ገልጠዋል።

ያም ቪክቶሪያ ውስጥ በቫይረሱ ሕይወታቸው ያለፈውን ቁጥር ወደ 83 ከፍ እንዲል አድርጓል።  

በአውስትራሊያ አቀፍ ደረጃም የሟቾች ቁጥር 167 ደርሷል። 

በዛሬው ዕለት ሕይወታቸው ካለፈው ስድስት ሰዎች ሁለቱ ዕድሜያቸው 90ዎቹ ውስጥ ሶስቱ በ80ዎቹ አንዱ በ70ዎቹ ያሉ ነበሩ።

ከስድስቱ አራቱ ሕልፈተ ሕይወቶች ከአረጋውያን መጦሪያ ጋር የተያያዙ ናቸው።

ቪክቶሪያ በቫይረሱ ተይዘው ካሉት 4,775 ውስጥ 769ኙ በአረጋውያን መጦሪያ የሚገኙ ናቸው።  

ፕሪሚየር ዳንኤል አንድሩስ - ምንም እንኳ የግል አረጋውያን መጦሪያ ዘርፉ የሚተዳደረው በጋራ ብልፅግናው መንግሥት ቢሆንም የቪክቶሪያ መንግሥት የበኩሉን አስተዋፅዖ እንደሚያበረክት ተናግረዋል።

አያይዘውም፤ የአረጋውያን መጦሪያ ዘርፉ ለአረጋውያኑ ተገቢውን ክብካቤና የደኅንነት ጥበቃ ይሰጣል የሚል አመኔታ እንደሌላቸው ሲገልጡ፤

"እዚህ ቆሜ የግል የአረጋውያን መጦሪያ ተቋማቱ ለተጠዋሪዎቹ ተገቢውን ክብካቤና የደኅንነት ጥበቃ ያደርጋሉ ብዬ በሙሉ እምነት ልነግራችሁ አይቻለኝም። ያንን ማለት የምችል ቢሆን ኖሮ፤ እንዲያ ብዬ በነገርኳችሁ ነበር። ስለሆነም እዚህ ቆሜ ያን አልላችሁም። እንዲሁም፤ እዚህ ቆሜ ያ የጋራ ብልፅግና መንግሥቱ ጉዳይ ነው ብዬም አልልም። እነዚያን የመጦሪያ ቤቶች እኛ አናስተዳድራቸውም። ይሁንና ተጠዋሪዎቹ በሙሉ ቪክቶሪያውያን ናቸው" ብለዋል።    

 በሌላም በኩል ኒው ሳውዝ ዌይልስ በዛሬ ዕለት ማክሰኞ 14 አዲስ በኮሮናቫይረስ ሰዎች የተጠቁባት መሆኗን አስታውቃለች። 

ይህ በእንዲህ እንዳለም፤ ጊዜያዊ የአረጋውያን መጦሪያ ሠራተኞች ከነገ ረቡዕ ጀምሮ በፍትሕ የሥራ ኮሚሽን ውሳኔ መሠረት ከሥራቸው ለዕረፍት ሲወጡ እንደ ቋሚ ሠራተኞች ክፍያ እንዲያገኙ ይደረጋል።

ይሁንና ይህ በወረርሽኙ ሳቢያ የወሸባ ክፍያ የሚቆየው ለሶስት ወራት ብቻ ነው። 

ኮሚሽኑ ከዚህ ውሳኔ የደረሰውም ጊዜያዊ ሠራተኞች የኮቪድ - 19 ምልክቶች ቢኖሩባቸውም በገቢ ችግር የተነሳ ወደ ሥራ በመምጣት ቫይረሱን እንዳያስፋፉ ለመከለላከል መሆኑን ገልጧል።    

የአውስትራሊያ ሠራተኞ ማኅበር በበኩሉ የወረርሽኝ ዕረፍት ክፍያው በአንድ ዘርፍ ብቻ ሳወሰን ሁሉንም የአውስትራሊያ ሠራተኞች እንዲያካትት ለፌዴራል መንግሥቱ ጥያቄ አቅርቧል።   

 


Share

Published

Updated

By NACA
Presented by Kassahun Seboqa Negewo

Share this with family and friends