አንድ የ26 ዓመት ግራንድ ሃያት ሆቴል ወሸባ ሠራተኛ በኮሮናቫይረስ መያዝን ተከትሎ የቪክቶሪያ መንግሥት ከዛሬ ሐሙስ ፌብሪዋሪ 04 ጀምሮ የፊት ጭምብል ማጥለቅ፣ የቤት ውስጥ መሰባሰብና የሥራ መመለስ መጠንን አስመልክቶ መለስተኛ ለውጥ አድርጓል።
በዚህም መሠረት ነዋሪዎች በማናቸውም ሰዎች በሚሰባሰቡባቸው ቤቶች ውስጥ (ሥራ፣ የገበያ አዳራሾች፣ ትምህርት ቤት ክፍል ውስጥ) በመሳሰሉት ሥፍራዎች የፊት ጭምብል እንዲያጠልቁ፣ ቀደም ሲል ቤት ውስጥ እስከ 30 ሰዎች ለመሰባሰብ እንዲችሉ ተፈቅዶ የነበረው ወደ 15 ዝቅ ብሏል፣ ከሰኞ ፌብሪዋሪ 8 ጀምሮ 75 ፐርሰንት ሠራተኞች ወደ ሥራ እንዲመለሱ ታቅዶ የነበረ ቢሆንም በቫይረስ ክስተቱ ሳቢያ ወደ 50 ፐርሰንት ዝቅ እንዲል ተደርጓል።
በቫይረሱ የተያዘው ግለሰብ ጃኑዋሪ 29 ራስል ስትሪት ኤክስፎርድ ሆቴልን 11pm እና 11.35pm እንዲሁም ኪባብ ኪንግዝ ከ 11.24pm - 12.15am ተገኝቷል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ ግለሰቡ የተገኘባቸው አካባቢ የነበሩ ግለሰቦች የኮሮናቫይረስ ምርመራ እንዲያደርጉ የተጠየቁ ሲሆን፤ እንዲሁም ግርናድ ሃያት ሆቴል የነበሩ 600 የአውስትራሊያ ኦፕን ተጫዋቾች፣ ኃላፊዎችና ሠራተኞች የቫይረስ ምርመራ አድርገው ከቫይረሱ ነፃ መሆናቸው እስኪረጋግጥ ድረስ ራሳቸውን እንዲያገልሉ ተደርጓል።
በዛሬው ዕለት ፌብሪዋሪ 4 ሜልበርን ፓርክ ውስጥ የአውስትራሊያ ኦፕን ግጥሚያ አይካሄድም።