ባለፉት 24 ሰዓታት ቪክቶሪያ ውስጥ በአንድ ነጠላ ቀን በአውስትራሊያ ደረጃ ከፍተኛ ሬኮርድ ያስመዘገበ የ10 ሰዎች ሕይወት በኮቪድ 19 ተቀጥፏል።
በቫይረሱ ሕይወታቸውን ያጡት ሰባቱ ወንዶችና ሶስቱ ሴቶች ሲሆኑ፤ ዕድሜያቸው ከ40ዎቹ እስከ 80ዎቹ የሚገኙ ናቸው።
የሰባቱ ሰዎች ሕልፈተ ሕይወትም በአረጋውያን መጦሪያ ከተከሰተው ወረርሽኝ ጋር የተያያዘ ነው።
የ10ሩ ሰዎች ሞት ቪክቶሪያ ውስጥ በኮሮናቫይረስ ሕይወታቸው ያለፈውን ሰዎች ቁጥር 71 ሲያደርስ በአገር አቀፍ ደረጃ ወደ 155 እንዲያሻቅብ አድርጓል።
በቫይረሱ የተጠቁ 228 ቪክቶሪያውያን ሆስፒታል ተኝተው ሕክምና እየተከታተሉ ሲገኙ፤ 42 በፅኑ ሕመምተኛ ክፍሎች ውስጥ የሕክምና እርዳታ እየተደረገላቸው ነው።
ቪክቶሪያ በትናንትናው ዕለት ቅዳሜ 42,573 የኮሮናቫይረስ ምርመራ በማካሄድ እስከአሁን በአንድ ቀን ከተካሄዱት ምርመራዎች ከፍተኛውን ቁጥር የያዘ መሆኑን ፕሪሚየር ዳንኤል አንድሩስ ገልጠዋል።
አክለውም፤ 560 በቫይረሱ የተጠቁት ሰዎች ከአረጋውያን መጦሪያ ጋር የተያያዘ መሆኑና 381 የአረጋውያን መጦሪያ የጤና ሠራተኞችም በቫይረሱ መያዛቸው "በጣሙን ፈታኝ" ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ቫይረስ ኒው ሳውዝ ዌይልስ
ኒው ሳውዝ ዌይልስ በበኩሏ ባለፉት 24 ሰዓታት 15 አዲስ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎችን አስመዝግባለች።
በቫይረሱ ከተያዙት ውስጥ አራቱ ከአንድ ጊዜ በላይ በደቡብ - ምዕራብ ሲድኒ የቤተክርስቲያን ፀሎት ሥነ ሥርዓትን ከተከታተለች አንዲት ሴት ጋር በነበራቸው ቅርበት ሳቢያ ነው።
ይህንኑ ክስተት ተከትሎም የኒው ሳውዝ ዌይልስ ጤና መሥሪያ ቤት ባለፉት ቀናት አምስት የጸሎት ሥነ ሥርዓቶችን የተካፈሉ ምዕመናን የቫይረስ ስሜት ያደረባቸው መሆኑን እንዲከታተሉ፣ ሕመም ከተሰማቸውም ራሳቸውን እንዲያገሉና ምርመራ እንዲያካሂዱ አሳስቧል።
በቫይረሱ ከተያዙት ውስጥ ስምንቱ ከታይ ሮክ ሬስቶራንት ጋር የተያያዘ መሆኑም ተገልጧል። ስድስቱ ሆቴል ውስጥ ወሸባ ገብተው የነበሩ ሲሆን አንዱ በቫይረሱ እንደምን እንደተያዘ እየተጠና ይገኛል።
ደቡብ ቻይና ባሕር
አውስትራሊያ የቻይናን የደቡብ ቻይና ባሕር ይገባኛል የውኃ ወሰን ተጻርራ ድጋፏን ለዩናትይድ ስቴትስ ሰጥታለች።
አውስትራሊያ በተባበሩት መንግሥታ ቋሚ ተጠሪዋ በኩል ለመንግሥታቱ ድርጅት ባቀረበችው ደብዳቤ "ቻይና በደሴቶቹ ዙሪያ የባሕር ወሰኖች ይገባኛል ማለት ከዓለም አቀፍ ሕግ ጋር የማይጣጣም ነው" ብላች።
ይህንኑ የአውስትራሊያን አቋም የጋራ ይሁንታ ለማላበስ የአውስትራሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሜሪዝ ፓይንና የመከላከያ ሚኒስትር ሊንዳ ሬይኖልድስ በዓመታዊው የአውስትራሊያ-ዩናይትድ ስቴትስ ዓመታዊ የሚኒስትሮች ስብሰባ ለመታደም ወደ አገረ አሜርካ ያቀናሉ።