ከዛሬ ሐሙስ ሜይ 27 ጀምሮ እስከ ጁን 3 የሚቆዩ የኮሮናቫይረስ ገደቦች ቪክቶሪያ ላይ መጣላቸውን የክፍለ አገሩ ተጠባባቂ ፕሪሚየር ጄምስ ሜሪሊኖ አስታወቁ።
በዚህም መሠረት፤
ማኅበራዊ
ከቤትዎ መውጣት የሚችሉት ለአምስት ጉዳዮች ብቻ ይሆናል።
- መሠረታዊ ለሆኑ የገበያ ሸመታ
- ለሌሎች ክብካቤ ለማድረግ
- ፈቃድ ያለው የሥራ ገበታ ላይ ለመሠማራት
- እስከ ሁለት ሰዓት የሚደርስ የአካል እንቅስቃሴ ለማድረግና
- ክትባት ለመከተብና ልዩ ፈቃድ ሲኖር ይሆናል።
ፍቅራዊ ግንኙነት ካለዎት ግለሰብ በስተቀር ቤትዎ ውስጥ ጎብኚዎች ማስተናገድ አይችሉም።
በግልና በአደባባይ መሰባሰብ አይፈቀደም።
ከቤት ሆነው መሥራት የሚችሉ ከሆነ ሥራዎን ቤትዎ ሆነው ማከናወን ይችላሉ።
የ5 ኪሎ ሜትሮች ገደብ
ከመኖሪያ ቤትዎ ርቀው መሔድ የሚችሉ እስከ 5 ኪሎ ሜትሮች ርቀት ድረስ ነው።
ከተፈቀደልዎት የርቀት ገደብ ውጪ መሔድ የሚችሉት፤
- በ5 ኪሎ ሜትሮች ርቀት ውስጥ አስፈላጊዎ የሆኑ ቁሳቁሶችን ለመሸመት ወይም ግልጋሎቶችን ለመጠቀም የማይችሉ ከሆነ
- ፍቅረኛዎን ለመጎብኘት
- ፈቃድ ያለዎት ሠራተኛ ከሆኑ
- ክብካቤ ለማድረግና ሌሎች ሰብዓዊ ርህራሄን ግድ የሚሉ ጉዳዮች ካለዎት ይሆናል።
የፊት ጭምብሎች
ቤትዎ ውስጥ ካልሆነና ከጤና ጋር የተያያዘ ፈቃድ ከሌለዎት በስተቀር በማናቸውም የቤት ውስጥና ከቤት ውጪ እንቅስቃሴዎ ወቅት የፊት ጭምብሎችን የማድረግ ግዴታ አለብዎት።
ትምህርትና ሙዋዕለ ሕጻናት
ሙዋዕለ ሕጻናትና የቤተሰብና ሕጻናት ክብካቤ ማዕከላት ክፍት ይሆናሉ።
ትምህርት ቤቶች ተጋላጭ ከሆኑና በሥራ ገበታቸው ላይ መገኘት እጅጉ አስፈላጊ ከሆኑ ሠራተኞች ልጆች በስተቀር የትምህርት አሰጣጣቸው በርቀት የማስተማሪያ ዘዴ ይሆናል።
የከፍተኛ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት የርቀት ትምህርት ብቻ ይሰጣሉ።
ችርቻሮ
የምግብና መስተንግዶ ግልጋሎት ሰጪዎች ግልጋሎቶቻቸውን አዝዘው ወደ ቤታቸው በሚወስዱ ደንበኞች ብቻ ይወሰናል።
ግልጋሎቶቻቸው በእጅጉ አስፈላጊ የሆኑ ቸርቻሪዎች ለአንድ ሰው በ 4 ስኩየር ሜትር ርቀት ገደብ አገልግሎቶቻቸውን ለመስጠት ክፍት ይሆናሉ።
ሌሎች ቸርቻሪዎች በኦንላይን አዝዘው ንክኪ በሌለው መንገድ ግልጋሎቶቻቸውን መጥተው ለሚወስዱ ደንበኞች አገልግሎቶቻቸውን መስጠት ይችላሉ።
ጸጉር ማስተካካከያ፣ የውበት ሳሎንና የግላዊ ክብካቤ ንግድ ቤቶች ዝግ ይሆናሉ።
አካላዊ እንቃስቃሴ ማካሄጃ
የቤት ውስጥ አካላዊ መዝናኛዎችና የስፖርት እንቅስቃሴዎች ዝግ ይሆናሉ።
ከቤት ውጪ አካላዊ መዝናኛና የስፖርት እንቅስቃሴዎች የተከለከሉ ሆነው የመጫዎቻ ሥፍራዎች ክፍት ይሆናሉ።
ኩነቶች
የቤት ውስጥ ሆነ የውጪ ቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ መገኘት የሚችሉ ለቀስተኞች ቁጥር ከ10 የበለጠ አይፈቀድም፤ የቀብሩን ሥነ ሥርዓት የሚመሩትን አይጨምርም። የገድቡ ቁጥር ዕድሜያቸው ከ12 ዓመት በታች የሆኑ ሕጻናትን አያካትትም።
የቤት ውስጥም ሆነ ከቤት ውጪ ሠርግ አይካሄድም፤ ለፍጻሜ ሕይወት ተቃርበው ወይም አገር ለቅቆ የሜሄድ ጉዳዮች ካልገጠሙ በስተቀር። በእኒህ ኩነቶች ላይ መገኘት የሚችሉት 5 ሰዎች ብቻ ይሆናል። ሁለቱን ተጋቢዎች ጨምሮ፣ አንድ አጋቢና ሁለት እማኞች።
የሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓቶች ላይ በኦንላይን ካልሆነ በስተቀር በአካል መታደም የተከለከለ ነው።