እንደራሴ ዳንኤል አንድሩስ የቪክቶሪያን ቀጣይ ከኮሮናቫይረስ ገደቦች መውጫ ፍኖተ ካርታ ዛሬ እሑድ ኦክቶበር 24 ይፋ አደረጉ።
ኦክቶበር 21 የቪክቶሪያ ተከታቢዎች ቁጥር 70 ፐርሰንት በመድረሱ የረገቡ የመጀመሪያ ዙር ገደቦችን ተከትሎ ለሁለተኛ ጊዜ ተጨማሪ ገደቦች ኦክቶበር 29 ከምሽቱ 6:00pm ጀምሮ ይነሳሉ።
ለሁለተኛ ጊዜ ገደቦቹ እንዲነሱ የሚደረገው የተከታቢዎች ቁጥር 80 ፐርሰንት ስለሚደርስ ነው።
አቶ አንድሩስ በታካይነትም የተከታቢዎች ቁጥር 90 ፐርሰንት ሲደርስ የሚከሉ ተጨማሪ ገደቦችን በፍኖተ ካርታቸው ላይ አካትተዋል።
በዚህም መሠረት፤
ማኅበራዊ
- ቤትዎ ውስጥ በየቀኑ ከ10 ያልበለጡ ጎብኚዎችዎን ከእነ ጥገኞቻቸው ማስተናገድ ይቻላሉ
- እስከ 30 ሰዎች ከቤት ውጪ መሰባሰብ ይችላሉ
- የቤት ውስጥ ማኅበረሰብ ስፖርቶች በአነስተኛ ቁጥር ክፍት ይሆናሉ
የፊት ጭምብል
- ከዕለት ዓርብ ምሽት ጀምሮ ከቤትዎ ሲወጡ የፊት ጭምብል ለማድረግ ግድ አይሰኙም። ይሁንና አካላዊ ርቀትን ለመጠበቅ አዋኪ በሆኑባቸው የቤት ውስጥ ሁኔታዎች የፊት ጭምብል ማጥለቅን ግድ ይላል። ከቤት ውጪም የሰዎች እንቅስቃሴዎች በሚበረክቱባቸውና አካላዊ ርቀትን ለመጠበቅ በሚያስቸግሩ ጎዳናዎችና ገበያዎች አካባቢ የፊት ጭምብልን የማጥለቅ ግዴታ ባይኖርም ይመከራል።
- የቪክቶሪያ ተከታቢዎች ቁጥር 90 ፐርሰንት ሲደርስ ከፍተኛ ተጋላጭነት ካላቸው እንደ ሆስፒታል፣ የአረጋውያን መከባከቢያ፣ የሕዝብ ትራንስፖርት፣ ፍርድ ቤትና የማረሚያ ተቋማትን ከመሳሰሉት ውጪ የፊት ጭምብሎችን ማጥለቅ ግዴታ አይኖርም።
የችርቻሮ ሱቆች
- ሁሉም የችርቻሮ ሱቆች ክፍት ይሆናሉ።
መስተንግዶዎች
- ከዓርብ 6pm ጀምሮ ምግብ ቤቶች፣ መጠጥ ቤቶችና የአካል እንቅስቃሴ ሥፍራዎች ሙሉ ክትባት ለተከተቡ ደምበኞች የአራት ስኩየር ሜትር ርቀት መጠንን ጠብቀው በቤት ውስጥ ማስተናገድ ይፈቀድላቸዋል
- ከ500 ያልበለጡ ሙሉ ክትባት የተከተቡ ደንበኞችን የሁለት ስኩየር ሜትር ርቀትን በጠበቀ ሁኔታ ከቤት ውጪ ማስተናገድ ይችላሉ።
- የጸጉር ቤቶች፣ የውበት ሳሎኖችና የግል ክብካቤ ግልጋሎት ሰጪዎች ሙሉ ክትባት ለተከተቡ ክፍት ይሆናሉ።
ትምህርት ቤቶች
- ሙሉ በሙሉ ወደ መማሪያ ክፍሎቻቸው መመለስ ከሚገባቸው ኖቬምበር 1 ቀደም ብለው ዓርብ ኦክቶበር 29 ይመለሳሉ።
ሲኒማና ቲያትር ቤቶች
- ሲኒማና ቴያትር ቤቶችን የመሳሰሉ የቤት ውስጥ መዝናኛ ሥፍራዎች ከማስተንግዶ አቅማቸው ከ75 ፐርሰንት ባልበለጠ ለደንበኞቻቸው ክፍት ይሆናሉ
- ስታዲየምና መካነ እንሰሳት ከ5,000 ላልበለጡ ታዳሚና ጎብኚዎችን ማስተናገድ ይችላሉ
- ለጃንዋሪ 26 Boxing Day ክሪኬት ጨዋታ 80,000 ታዳሚዎች ስታዲየም ተገኝተው መመልከት እንደሚችሉ ይጠበቃል።
ጋብቻ፣ ቀብርና ቤተ እምነቶች
- ሙሉ ክትባት የተከተቡ ቤት ውስጥ በአንድ ሰው አራት ስኩየር ሜትር አካላዊ ርቀትን ጠብቀው
- 500 ከቤት ውጪ ባሉ የሠርግ፣ ቀብርና የቤተ እምነት ሥነ ሥርዓቶች ላይ መታደም ይችላሉ።
የተከታቢዎች ቁጥር 90 ፐርሰንት ሲደርስ
- ዕድሜያቸው 12 እና ከዚያ በላይ የሆኑ የቪክቶሪያ ነዋሪዎች የክትባት መጠን ረቡዕ በ26 ኖቬምበር 90 ፐርሰንት ይደርሳል ተብሎ ይታመናል
- ከዚያን ቀን ጀምሮም የአካላዊ ርቀት ድንጋጋጌዎች ይነሳሉ
- ለቤት ውስጥና ከቤት ውጪ ኩነቶች የክትባት መሥፈርቶችንና COVIDSafe ድንጋጌዎችን ከመከተል በስተቀር የታዳሚ ሰዎች ቁጥር ገደብ አይኖርም።
ቪክቶሪያ ውስጥ ባለፉት 24 ሰዓታት 1,935 ሰዎች በኮቪድ-19 ሲጠቁ 11 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል።
ባለፈው ዓርብ ከ99,000 በላይ ቪክቶሪያውያን ክትባት በመከተባቸው ዕድሜያቸው 16 እና ከዚያ በላይ ሆኖ የመጀመሪያ ክትባት የተከተቡ ሰዎች ቁጥር 90.2 ሙሉ ክትባት የተከተቡ 73.1 ፐርሰንት መድረስ ችሏል።