የዓለም ጤና ድርጅት የኮቪድ - 19 ወረርሽኝን በውል መከላከል ካልተቻለ በወረርሽኙ የመጀመሪያ ዓመት እስከ 190,000 ያህል ሰዎች ሕይወት ሊቀጠፍ እንደሚችል አስጠንቅቋል።
የተባበሩት መንግሥታት የጤና ኤጀንሲ የብራዛቪል ቢሮ ጥናት እንዳመለከተው ከሆነ በኮሮናቫይረስ ከ 83,000 እስከ 190,000 አፍሪካውያን ለሞት ሊዳረጉ እንደሚችሉና ከ 29 እስከ 44 ሚሊየን የሚደርሱቱ የቫይረሱ ተጠቂዎች እንደሚሆኑ አመልክቷል።
ምርምሩ መሠረቱን ያደረገው 47 አገራትንና አንድ ቢሊየን ሰዎችን ባካተተ የትንበያ ሞዴል መሆኑን የጤና ድርጅቱ መግለጫ ጠቁሟል።
የጤና ጠበብቱ አፍሪካ በተለይ በደካማ የጤና መሠረተ ልማቷ፣ ከፍተኛ የድህነት መጠን፣ በርካታ ግጭቶችና ወረርሽኞችን የመጠራጠር የቀደምት ተሞክሮዎቿ ተደራርበው ለወረርሽኙ ተጋላጭነቷን እንደሚያጎላው አመላክተዋል።

Shoppers at a Nigerian fish market wear face masks to prevent the spread of COVID-19. Source: AP
የቫረሱ አፍሪካ ውስጥ ተዛማችነት ግና በአውሮፓ፣ ዩናይትድ ስቴትስና ሌሎች አገራት የተከሰተውን ያህል ያሻቀበ ሳይሆን ያዘገመ ነው።
የአፍሪካ የዓለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተር ማትሺዲሶ ሞቲ የቫይረሱን አፍሪካ ውስጥ ማዝገም አንስተው ሲናገሩ "ዝቅተኛ ተዛማችነቱ የሚያመለክተው ወረርሽኙ ለጥቂት ዓመታት የሚቆይ መሆኑን ነው። ምንም እንኳ አሁን 50 000 በቫይረሱ ተጠቅተዋል 2000 ሕይወታቸውን አጥተዋል ቢባልም፤ ቫይረሱን ለመመከት አገራት ዳታን መሠረት ያደረገ ተጨባጭ መረጃን መጠቀም ያሻቸዋል" ብለዋል።
ትናንሽ አገራትን አክሎ አልጄሪያ፣ ደቡብ አፍሪካና ካሜሩን በተለይ ለቫይረሱ በከፍተኛ ደረጃ ተጋላጭ በመሆናቸው ብርቱ የመከላከል እርምጃዎችን ሊወስዱ እንደሚገባ የዓለም ጤና ድርጅት አሳስቧል።
እስካሁን ድረስ አፍሪካ ውስጥ 53,334 በቫይረሱ የተጠቁና 2,065 ሕይወታቸው ያለፈ ሲሆን፤ በመላው ዓለም 267,000 ያህል ሰዎች ለሞት ተዳርገዋል።
በርካታ የአፍሪካ አገራት የተለያዩ ቅድመ መከላከል እርምጃዎችን ወስደዋል። የተወስኑቱ የጣሏቸው ገደቦች ጸንተው ያሉ ሲሆን ናይጄሪያና ደቡብ አፍሪካ ባለፈው ሳምንት ገደቦቻቸውን አላልተዋል።