የቪክቶሪያ ፕሪሚየር ዳንኤል አንድሩስ ዛሬ እሑድ ቪክቶሪያ ውስጥ 394 ሰዎች በኮሮናቫይረስ መጠቃታቸውንና 17 ሕይወታቸውን ማጣታቸውን አስታውቀዋል።
ሕይወታቸው ካለፉት ውስጥ ሁለት ወንዶች በ50ዎቹ፣ አራት ወንዶች በ70ዎቹ፣ አራት ሴቶችና ሁለት ወንዶች በ80ዎቹ፣ ሁለት ሴቶችና ሶስት ወንዶች በ90ዎቹ ዕድሜዎች የነበሩ ናቸው።
ከሟቾቹ ውስጥ አሥሩ የአረጋውያን መጦሪያ ነዋሪዎች የነበሩ ናቸው።
በዛሬው ዕለት አዲስ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ቅዳሜ 466፣ ዓርብ 450፣ ሐሙስ 471 እና ረቡዕ የቫይረሱ ተጠቂ ከሆኑት 725 ሰዎች ጋር ሲነጻጻር ዝቅተኛው ነው።
በአሁኑ ወቅት 634 ቪክቶሪያውያን ሆስፒታል ተኝተው እየታከሙ ሲሆን፤ 43ቱ በፅኑ ሕመምተኞች ክፍል የሕክምና እርዳታ እየተደረገላቸው ነው።
በቫይረሱ ተጠቅተው ካሉት ውስጥ 994ቱ የጤና ሠራተኞች ናቸው።
ባለፉት 24 ሰዓታት እምቢኝ ጭምብል አናጠልቅም ያሉትን 38 ሰዎች ጨምሮ የደረጃ አራት ገደብ ድንጋጌን ጥሰው በተገኙ 268 ሰዎች ላይ የቪክቶሪያ ፖሊስ መቀጮ ጥሏል።

Police are seen in front of Flinders Street Station during a 8PM-5AM curfew in Melbourne, Saturday, August 8, 2020. Source: AAP
ክወረርሽኙ ጋር በተያይዘ የአዕምሮ ጤና ግልጋሎት ሰጪዎች ላይ ጫናዎች መብዛታቸውን ተከትሎ የቪክቶሪያ መንግሥት ለአዕምሮ ጤና ግልጋሎት የሚውል $59.7 ሚሊየን ዶላርስ መመደቡን የቪክቶሪያ መንግሥት በዛሬው ዕለት አስታውቋል።
የሶስትዮሽ ድርድር
በሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ባለፈው ሳምንት ተቋርጦ የነበረው የሕዳሴ ግድብ ፕሮጄክት ድርድር እንዲቀጥል አደራዳሪና የወቅቱ የአፍሪካ ሕብረት መሪነትን የያዘችው ደቡብ አፍሪካ ለሶስቱ ተደራዳሪ አገራት ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን ጥሪ አስተላልፈዋል።
በዚሁም መሠረት በነገው ዕለት የሶስቱ ተደራዳሪ አገራት የውኃ ሚኒስትራት የሚመሩ የቴክኒክና የሕግ ባለሙያ ቡድናት አካትቶ ድርድሩ ይቀጥላል።
ባለፈው ሳምንት ሐምሌ 28 - 2012 የድርድሩን መቋረጥ ምክንያት አስመልክቶ በኢትዮጵያ በኩል የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ "ግብፅና ሱዳን ኢትዮጵያ ያቀረበችውን ደንብ ለመመልከት ጊዜ እንደሚፈልጉ ጠቅሰው ስብሰባው እንዲራዘም በጠየቁት መሠረት አገራቱ የውስጥ ምክክራቸውን ሲያጠናቅቁ ድርድሩን ለመቀጠል ስምምነት ተደርሷል" ሲል አስታውቋል።
ተጨማሪ ያንብቡ

የኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን የሕዳሴ ግድብ ድርድር ተራዘመ
የግብፅ የውኃና መስኖ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት በበኩሉ ወደ ስብሰባው ከመግባታቸው ጥቂት ቀደም ብሎ ከኢትዮጵያ የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ረቂቅ "የግድብ ሙሌት መመሪያዎችና ደንቦች" እንደደርሱት ጠቁሞ፤ ረቂቁ "ስምምነቱ ሕጋዊ አስገዳጅነት" እንዲኖረው አላከተተም በማለት ቅሬታውን ገልጧል።
የሱዳን የውኃ ሃብቶችና መስኖ ሚኒስቴርም በፊናው ረቂቁ ከኢትዮጵያ ወገን የደረሰው ወደ የሱዳን ተደራዳሪዎች ወደ ስብሰባ ከመግባታቸው ጥቂት ሰዓታት ቀደም ብሎ መሆኑን አስታውቋል።
በዕለቱም ደቡብ አፍሪካ፣ የአውሮፓ ሕብረትና የዩናይትድ ስቴትስ ታዛቢዎችና የአፍሪካ ሕብረት ባለ ሙያዎች ታድመዋል።
ሰኞ ዕለት ድርድሩ ሲጀምር የሶስቱ አገራት የሕግና የቴክኒክ ቡድናት የውኃ ሚኒስትሮች የመነጋገሪያ አጀንዳው ትኩረት አገራቱ ባልተስማሙባቸው ጉዳዮች ላይ ይሆናል።